ደምቢ ዶሎ፡- የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አቋርጠው ወደነበረው መደበኛ ትምህርታቸው መመለሳቸውን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ለታ ተስፋዬ ገለፁ።
ዶክተር ለታ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ ከሌላ አካባቢ ካለው የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን አቋርጠው የመጡ ተማሪዎች በደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ገብተው ካልተማሩ በሚል ለተወሰኑ ቀናት ትምህርት ተቋርጦ ቢቆይም መግባባት ላይ በመደረሱ መደበኛ ትምህርት ተጀምሯል።
ዶክተር ለታ እንዳሉት፤ በአማራ ክልል ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ የኦሮሞ ተማሪዎች ወደጊቢው ገብተን ትምህርት ካልተማርን በሚል ጥያቄ አንስተው ነበር፣ በግቢው ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎች ደግሞ ከሌላ ቦታ የመጡ ተማሪዎችን ተቀብላችሁ ካላስተማራችኋቸው አንማርም የሚል ጥያቄ ሲያነሱ ቆይተዋል።
‹‹በወቅቱ የእኛ ምላሽ የነበረው፣ ተቋሙ የፌዴ ራል እንደመሆኑ ተቀብለን ማስተማር የምንችለው የተመደበልንን ብቻ እንደሆነ ነው። ለዚህም ምክንያቱ ዩኒቨርሲቲ የራሱ የሆነ ህግና ደንብ ያለው በመሆኑ ነው።›› ሲሉ ጠቅሰው፤ተማሪዎችንም ሰብስበው ጉዳዩን በአግባቡ እንዳስረዷቸው ገልፀዋል።
ጥያቄውንም ላቀረቡ ተማሪዎች መርዳት የሚገባቸው ነገር ካለ በፋይናንስም በኩል ቢሆን ለመርዳት እንደሚቻል ተናግረው፤ እነርሱን ተቀብሎ ለማስተማር ግን የተመደበላቸው በጀት በግቢው ላሉ ተማሪዎች ብቻ መሆኑን በመግለፅ እንደማይችሉ አሳውቀዋቸዋል። ወደ ነበሩበት ዩኒቨርሲቲ እስኪ መለሱ ድረስ ሊያግዟቸው እንደሚችሉም የነገሯቸው በመሆኑም ለአንድ ሳምንት ያህል ተቋርጦ የነበረው ትምህርት መጀመሩን አመልክተዋል።
እንደ ዶክተሩ ገለፃ፤ የደምቢ ደሎ ዩኒቨርሲቲ ሰላሙን የበለጠ ለማረጋገጥ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከሃይማኖት አባቶች እንዲሁም ከአባገዳዎች ከተውጣጡ ወደ 18 የሚሆኑ አባላትን የያዘ ቡድን አቋቁሟል። ቡድኑ ተማሪዎችን ይመክራል። ተማሪዎችን እንደልጆቻቸው በመቁጠርም ወደቤት በመውሰድ ቤተሰብ ያደርጓቸዋል። ስለከተማውም እውነታውን በማሳወቅ ውጪ ላይ የሚወራው ነገር ሐቅ እንዳልሆነም ያስረዷቸዋል።
በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት የፀጥታውን ሁኔታ የፌዴራል ፖሊስ በመቆጣጠር ላይ ነው። ምንም አይነት ስጋት እንዳይኖርም በየጊዜው ፍተሻውን በማጠናከር ላይ ይገኛል። ከዩኒቨርሲቲው መኝታ አስተዳደር ጋር በመሆንም ተማሪዎች የተሻለ የደህንነት ስሜት እንዲሰማቸው የተለያዩ ተግባራትን እንደሚያከናውንም ተናግረዋል።
የዩኒቨርሲቲው የጥናትና ምርምር ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ረዳት ፕሮፌሰር ዮሴፍ ሽፈራው በበኩላቸው፣ ‹‹ዩኒቨርሲቲው በመንግሥት የተሰጠው ሶስት ተልዕኮ ውስጥ አንዱ የመማርና ማስተማር ሂደት ሲሆን፣ ብቁ የሆነና የአገሪቱን ችግር መፍታት የሚችል ዜጋን በማስመረቅ ወደህብረተሰቡ መላክ ነው።›› ሲሉ ጠቅሰው፣ የምርምርና ልማት እንዲሁም የማህበረሰብም አገልግሎት በማዋቀር ሥራ በመሰራት ላይ እንደሆነ ተናግረዋል።ለዚህ ሁሉ ግን ሰላም ዋና መሰረት መሆኑን አስታውሰው፤አሁን በዩኒቨርሲቲው ይኸው ሰላም መስፈኑን አስረድተዋል።
‹‹እኛ አካባቢ ሰላም የጠፋ የሚመስላቸው ቢኖሩም፤ ሰላም ግን አለ። እኔ ዩኒቨርሲቲውን የተቀላቀልኩት በዚህ ዓመት መስከረም ወር ላይ ሲሆን፣ብዙዎች በህይወትህ ፈርደህ ሂድ ነበር ያሉኝ።ነገር ግን የተነገረውና ወደ አካባቢው ስመጣ መሬት ላይ ያለው እውነት በእጅጉ የተራራቀ ነው። ስለዚህ አካባቢው ሰላም ነውና ይህንኑ የሚዲያ አካላት ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል ባይ ነኝ።›› ብለዋል።
ዘንድሮ ወደ አንድ ሺህ 200 አካባቢ የሚጠጉ ተማሪዎች ያስመርቃል ተብሎ የሚታሰበው የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ የተመሰረተው በ2009 ዓ.ም ሲሆን፣ በዚህ ዓመት ተማሪዎችን የተቀበለው ለሶስተኛ ጊዜ ነው። ዩኒቨርሲቲው በ36 የትምህርት ዘርፎች ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ እንደሚገኝም ለማወቅ ተችሏል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 14/2012
አስቴር ኤልያስ