ወይዘሮ የሰውልክ ግርማ ነዋሪነቷ ደብረማርቆስ ከተማ ነው። የመጀመሪያ ልጇ ሰባት ወር ሲሞላው ጉንፋን በተደጋጋሚ ስላጠቃው ወደ ጤና ጣቢያ ትወስደዋለች። ምርመራም ይደረግለትና የልብ ችግር እንዳለበት እንደተገለጸላት ትናገራለች፤ ለህክ ምናውም ወደ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል ሪፈር ይጻፍላታል።
ልጇ በሆስፒታሉ በተደረገለት ምርመራም የልብ ቧንቧ መጥበብ ህመም እንዳለበት ይነገራታል። የቀዶ ጥገና ህክምና ያስፈልገዋል በሚልም ከአንድ አመት ከአምስት ወር በፊት ቀጠሮ ይሰጣታል።ከቀዶ ጥገና ህክምና በፊትም ቀጠሮ እየተሰጣት ከደብረማርቆስ እየተመላለሰች አራት ጊዜ ታሳክመዋለች። ወይዘሮ የሰውልክ አንድ ቀን ግን ስልክ ይደወልላታል፤ ልጁ የልብ ቀዶ ህክምና እንደሚሰራለት፤ ይገልጹላታል የደም ምርመራ በድጋሚ አድርገው ከሳምንት በኋላ እንደሚጠሯት የነገሯት ቢሆንም፣ እስካሁን እንዳልጠሯት ትገልፃለች።
በአሁኑ ወቅት ሁለት አመት ከስምንት ወር የሞላው ልጇ በሚጫወትበት ጊዜ የድካም ስሜት ይሰማዋል፤ ጉንፋን ሲይዘውም ለመተንፈስ ይቸገራል፤ እንቅልፍ በደምብ አይተኛም፤ ልብስ ሲጫነውም ይጨንቀዋል። ወይዘሮ የሰውልክ እድሉ ገጥሞት የቀዶ ህክምናውን ማድረግ ከቻለ ልጇ ወደ ጤንነቱ እንዲሚመለስላት እና ከጭንቀቷ እንደምትገላገል ተስፋ ሰንቃለች።
በማእከሉ የልብ ቀዶ ህክምና በነፃ ተደርጎላቸው የዳኑ ህፃናት እንዳሉ መስማቷን ተናግራ፤ ማእከሉ ቢስፋፋ የእሷ ልጅ ጨምሮ ሌሎች ወረፋ የሚጠባበቁ ህፃናት ተስፋ እንደሚለመልምም ታመለክታለች። የሻሸመኔ ከተማ ነዋሪው አቶ ከማል ሁሴን ልጃቸው ከተወለደች ከሶስት ወራት በኋላ ልቧ ባልተለመደ ሁኔታ በፍጥነት እየመታ ይቸገራሉ። በዚህም ተደናግጠው ጤና ጣቢያ ቢወስዷትም፣ ልጅቷ ምንም አይነት የልብ ህመም እንደሌለባት ሃኪሞች ይገልጹላቸዋል።
አቶ ከማል የልጅቷ የልብ ምት ቶሎ ቶሎ መምታ ቱን ይቀጥልና በሀዋሳ አንድ ሆስፒታል ምርመራ እንደተደረገለት ይገልጻሉ።የልጅቷ ልብ ቧንቧ በተፈጥሮ ክፍተት እንዳለበት በምርመራ መረጋገጡን ጠቅሰው፣ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ወስደው እንዲያሳ ክሟት በተጻፈላቸው ሪፈር መሰረት ወደ ማእከሉ መምጣታቸውን ያስታውሳሉ።
ልጃቸው በየአንድና ሁለት ወሩ የህክምና ክትትል እያደረገችና መድኃኒትም እየወሰደች ትቆያለች ።በዚህ መካከል ክብደቷ እየቀነሰ ይመጣናም ሃኪሞች ወደ ውጭ ሀገር ሄዳ መታከም እንዳለባት ለአቶ ከማል ይገለጹላቸዋል። ሀኪሞቹ ይህን ቢሉም ጠንካራ ክትትል እና የተለያዩ እንክብካቤዎችን ለልጅቷ ማድረጋቸውን ይቀጥላሉ፤ በዚህም ክብደቷን ከፍ ማድረግ ይችላሉ፤ ከሁለት ሳምንት የቀጠሮ ቆይታ በኋላም ውጤታማ ቀዶ ህክምና ያደርጉላታል።
በቀዶ ህክምናው የተሰማቸውን ደስታ ቃላት ሊገልጹት እንደማይችሉ የሚናገሩት አቶ ከማል፣ የማእከሉን የህክምና እርዳታ ለማግኘት በርካታ ህፃናት እንደሚመጡ ይጠቁማሉ። በዚህ ማእከል ብቻ የህክምና አገልግሎቱን በበቂ ሁኔታ ለመስጠት እንደማይቻል የሚናገሩት አቶ ከማል፣ማእከሉን ለማስፋፋት ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል የበኩሉን አስተዋፅኦ ማበርከት ይጠበቅበታል ይላሉ።የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችም ማእከሉ እንዲስፋፋ ድጋፍ ማድረግ እንደሚኖርባቸው ያመለክታሉ።
የኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህፃናት መርጃ ማእከል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ሄለን በፍቃዱ እንደሚገልፁት፤ማእከሉ እስከ አሁን ከስምንት ሺ ለሚበልጡ የልብ ህሙማን በዋናነትም ለህፃናት ነፃ የልብ ቀዶ ህክምና አድርጓል። ላለፉት ሁለት አመታት ሁሉም የልብ ህክምና ባለሙያዎች በውጭ ሃገር ስልጠና ወስደው ከመጡ በኋላ አገልግሎቱ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያን ባለሙያዎች እየተሰጠ ሲሆን፣ይህም የማእከሉ ትልቁ ስኬት ሆኖ ይቆጠራል።
ዶክተር ሄለን ማእከሉ አገልግሎት የሚሰጠው በነፃ መሆኑን ጠቅሰው፣መንግስታዊ ያልሆነ የህዝብ ድርጅት መሆኑን ይናገራሉ፤የማእከሉ ዋና ተግዳሮት የራሱ በጀትና የፋይናንስ ገቢ የሌለው መሆኑ ላይ መሆኑን ይገልጻሉ።
እንደ ዶክተር ሄለን ገለጻ፤ህብረተሰቡ የማእከሉ ባለቤት እንደመሆኑ ላለፈው አንድ አመት ማእከሉ ያለበትን ችግር እንዲያውቅ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ። በዚሁ መሰረት ከነሃሴ ወር ጀምሮ ከኢትዮ ቴሌኮም በተሰጠ የ6710A የመልእክት መላኪያ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ማካተት በሚችል መልኩ ከአንድ ብር ጀምሮ በማዋጣት የራሱን ድርሻ እንዲወጣ፣ በተመሳሳይም ባለሃብቶችም ማእከሉ የሚሰራውን ስራ እየጎበኙ በማእከሉ የባንክ አካውንት ድጋፍ እንዲያደርጉ ለማድረግ ተሰርቷል። ከዚሁ በተጓዳኝ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በሚችሉት መልኩ በመሳሪያ፣ በመድሃኒትና በከፍተኛ የገንዘብ እርዳታ ድጋፍ እንዲያደርጉ ቅስቀሳ እየተደረገ ይገኛል።
ይህን የማእከሉን እንቅስቃሴ በመደገፍ በኩል ሚዲያው ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ጠቅሰው፣ጥቂት ባለሃብቶችም የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውንና ይህም ድጋፍ አሁንም ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚኖርበት ዶክተር ሄለን ያስገነዝባሉ።
እንደ ዶክተር ሄለን ለማሰባሰብ በተደረገው ጥረትም 11 ሚሊዮን ብር ተሰብስቧል፤ሁለት ባለሃ ብቶችና ጥቂት ግለሰቦች በራሳቸው ፍቃደኝነት ከሚሰጡት ድጋፍ በተጨማሪ በቁሳቁስ ደረጃ ከውጪ ሃገር የሚመጡ እርዳታዎች አሉ። ይሁን እንጂ ሁሉም በሚሳተፍበትና ከአንድ ብር ጀምሮ በ6710A የመልእክት መላኪያ የተገኘው ገቢ ዝቅተኛ ነው። ይህም ድጋፍ በማሰባሰብ ላይ አሁንም በከፍተኛ ሁኔታ መስራት እንደሚጠይቅ ያሳያል። ለዚህም ማእከሉ የራሱን የህዝብ ግንኙነት ክፍል በማደራጀት ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥረት እያደረገ ነው።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 14/2012
አስናቀ ፀጋዬ