. 14 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ በመስኖ እየለማ ነው::
አዲስ አበባ፡- የሕዝቡን ፍላጎት ለማሟላትና በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከውጭ የሚገባውን ስንዴ በሃገር ውስጥ ምርት ለመተካት በቆላማ አካባቢዎች ስንዴን በ14 ሺህ አንድ መቶ ሄክታር መሬት በመስኖ የማልማት ተግባር እየተከናወነ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን በቆላ ስንዴ ልማትና በሌሎች የግብርና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ትናንት በመስሪያ ቤታቸው በሰጡት መግለጫ እንደገለፁት፤ ሚኒስቴሩ የሕዝቡን ፍላጎት ለማሟላት ከውጭ የሚያስገባውን ስንዴ ማስቀረት ብቻ ሳይሆን ስንዴን በብዛትና በጥራት በማምረት ወደ ውጭ ለመላክ ራዕይ ይዟል፡፡ ለዚህም በቆላማ አካባቢዎች ስንዴን በዘመናዊ መስኖ ታግዞ የማልማት ስራ እየሰራ ይገኛል፡፡
ይህን ራዕይ ለማሳካትና ከባለድርሻ አካላት ጋር በባለቤትነት ስሜትና በጠንካራ ቅንጅት ዘንድሮ 32 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ እየተሠራ ነው፡፡ እስካሁን ባለው ሂደትም 14 ሺህ አንድ መቶ ሄክታር መሬት የቆላ ስንዴ በመስኖ እየለማ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ ከእነዚህ ውስጥ 11 ሺህ አንድ መቶ ሄክታር የሚሆነው ለምግብነትና ለፋብሪክ፣ ሶስት ሺህ ሄክታር የሚሆነው ደግሞ ለዘር መዘጋጀቱን አብራርተዋል።
በአተገባበሩ የቦታ ዝግጅትና አቅርቦት እንዲሁም የዘር ብዜት ችግሮች መሰናክል መሆናቸውን ያስገነዘቡት ሚኒስትሩ፣ ይሁንና አፈፃፀሙ በሁለትና ሶስት አመታት ውስጥ ስንዴን ከውጭ ማስገባትን ለማስቀረት መሰረት በመጣል ረገድ ስኬታማ መደላድል እንደሚፈጠር አመላካች ስለመሆኑንም አብራርተዋል። በመስኖ ልማቱ ላይ የሚስተዋለውን የሃይል አቅርቦት ለማቃለልም ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
‹‹በመኸር ምርት አሰባሰብ ረገድም ዘንድሮ በምርት ከተሸፈነው ከ13 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ የደረሰው 12 ነጥብ 5 ሚሊዮን ወይንም 93 በመቶ ነው›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ ከዚህም ውስጥ ምንም እንኳን ከክልል ክልል ልዩነት ቢኖርም 9 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታሩ ወይንም 78 በመቶው ምርት መሰብሰቡንም አብራርተዋል።
ቀሪው በቀጣይ ሁለት ሳምንታት እንዲሰበሰብ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ርብርብ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል። ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው በበርሃ አንበጣና ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ በምርት ብክነት ላይ የደረሰው ጉዳት ዳሰሳዊ ጥናት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። የጥናቱ ውጤትም ወደፊት እንደሚገለጽ አስታውቀዋል።
የምርት ብክነትን በመከላከል ረገድ በአሰባሰብ ወቅት እስከ 20 በመቶ ምርት እንደሚባክን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ ይህን በመከላከል ረገድም የሜካናይዜሽን አሰራርን የማጎልበት፣ ለአርሶ አደሮች ስልጠና የመስጠትና የምርት ማከማቻ ቦታዎችን የማስፋት ስራዎች በመከናወን ላይ ስለመሆኑ አብራርተዋል። መንግስት የሜካናይዜሽን መሳሪያዎችን ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ መወሰኑ የምርት ብክነትን ለመቀነስና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ትልቅ መነሳሳትን እየፈጠረ መሆኑንም ገልፀዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 14/2012
ታምራት ተስፋዬ