ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለያዩ አካባቢዎች በእምነት ተቋማት ላይ ጥቃት እየደረሰ ይገኛል። ጥቃት አድራሾቹ በክርስትና እና በእስልምና እምነት ተከታዮች መካከል ግጭት ለመቀስቀስ አስበው የተንቀሳቀሱ መሆናቸውን መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት በተከሰቱ ጥቃቶች ዙሪያ በሰጠው መግለጫ አሳውቋል። ሰሞኑንም በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እና በእስልምና እምነት ተቋማት ላይ ጥቃት ደርሷል።
በሞጣ ከተማ ቤተክርስቲያንና መስጂዶች መቃጠላቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት መግለጫ አውጥተዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ባወጣችው መግለጫ፣ የተፈጸመው ድርጊት ለሀገሪቱ ሰላምና እድገት የማይጠቅም መሆኑን አውግዛለች።
ለዘመናት የቆየ አብሮ የመኖር እሴቶችን የሚንድ በመሆኑም መላው ህዝብ ይህን ተረድቶ በተረጋጋና በሰከነ መንፈስ ጉዳዩ እስከሚጣራ በትእግስት እንዲጠባበቅም አሳስባለች። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በበኩሉ፣ በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ ያልተረጋገጠ ወሬ በመሰራጨቱ ምክንያት መስጂዶች ላይ እንዲሁም በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን አስታውቋል። ይህንን ተከትሎም የደረሰውን ጉዳት የመንግሥት አካላት፣ የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያወግዘው ተግባር መሆኑን አመልክቷል። ለደረሰው ጥቃትና ውድመትም አጥፊዎች በህግ ጥላ ስር ውለው ድርጊቱ ተጣርቶ ለፍርድ እንዲቀርቡም ምክር ቤቱ ጠይቋል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ በሞጣ ከተማ ቤተክርስቲያንና መስጂዶች መቃጠላቸውን ተከትሎ በፌስቡክ ገጻቸው ድርጊቱን አውግዘዋል። በብልጽግና ጎዳና ላይ በምትገኘው ኢትዮጵያ የቆየ የሃይማኖቶችን የመቻቻልና አብሮ የመኖር ባህል የሚፃረሩ ጽንፈኛ አካሄዶች ቦታ እንደሌላቸውም ጠቅሰው፤ እንዲህ ያሉ የፈሪ አካሄዶችን አጥብቀው እንደሚቃወሙ ገልፀዋል። ኢትዮጵያውያንም የመከባበርና አብሮ የመኖር ጥልቅ እውቀታቸውን እንዲያጋሩም ጥሪ አቅርበዋል። ከፋፋይ አጀንዳዎችን በመረዳትና በመጠየፍ የጋራ እድገት ለማምጣት ተባብሮ መስራት እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል።
የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በአወጣው መግለጫ በሞጣ ከተማ በእስልምና እና ኦርቶዶክስ እምነት ተቋማት ላይ የደረሰውን ጥቃት በጥብቅ እንደሚያወግዝ እና እምነት ያለው ሰው የሚፈፅመው ድርጊት አለመሆኑን ገልጿል።
የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ቦርድ ሰብሳቢ መልአከ ሠላም ኤፍሬም ሙሉዓለም፣ የሞጣ ከተማ ህዝብ የጋራ ኮሚቴ በማቋቋም ክርስቲያኖች የሙስሊም መስጂድ የመስራት በተመሳሳይ ሙስሊሞች ደግሞ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እየገነቡ በመተሳሰብ የሚኖሩ መሆናቸውን ይገልፃሉ። በፍቅር፣ በአንድነት፣ በመቻቻልና በመተባበር ተከባብሮ እየኖረ የሚገኝ ህዝብ እንደሆነም ይጠቅሳሉ።
በእምነት ተቋማቱ ላይ የተፈፀመው ጥቃት እምነት ባለው አካል ሊፈጸም የማይችል እኩይ ተግባር መሆኑን በመጥቀስ፤ ድርጊቱ በጥብቅ ሊወገዝ እንደሚገባ ይጠቁማሉ። ቤተ እምነቶች ሰዎች ችግራቸውንና ደስታቸውን ለፈጣሪያቸው የሚነግሩበት፣ ትምህርት የሚያገኙበት፣ ፍቅር እና ሠላም የሚሰበክበት፣ ሕሙማን የሚፈወሱበት እና የተለያዩ የአምልኮ ሥርዓቶች የሚከወኑበት ስፍራ እንደሆነም ያመለክታሉ። ስለሆነም እነዚህን ተቋማት በእሳት ማቃጠል በምድራዊና ሠማያዊ መንግሥት እንደሚያስጠይቅ ይገልፃሉ። መንግሥትም በድርጊቱ የተሳተፉ አካላትን አጣርቶ አስፈላጊ የሆነ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባውም ያሳስባሉ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 14/2012
መርድ ክፍሉ