አዲስ አበባ፡- የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በለውጥ ጎዳና ላይ እንደሚገኝ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ። ተቋሙ በበኩሉ በስድስት ወራት ውስጥ ጠንካራ የሪፎርም ሥራዎች ማከናወኑን ገልጿል።
ቋሚ ኮሚቴው በትናንትናው እለት የተቋሙን የስድስት ወራት የሥራ አፈፃፀም በገመገመበት ወቅት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ እንደገለፁት፣በተቋሙ በኩል እየተሰሩ ያሉ አጠቃላይ የሪፎርም ሥራዎች በህግ፣ በአሰራር፣ በመመሪያና በማንዋል ከማስደገፍ አኳያ የተሻለ ነው።ከደህንነት ሥራ አንፃር የሀገርን ሰላምና ፀጥታ በማስጠበቅ ረገድ ጥሩ የሚባሉና አገልግሎቱ በለውጥ ጎዳና ላይ እንደሚገኝ የሚያሳይ ነው።
የሀገርን ሰላም ከማስጠበቅ አኳያ በተቋሙ እየተሰሩ ባሉ ሥራዎች ዙሪያ ቋሚ ኮሚቴው ጥያቄ አንስቶ እንደነበርም ሰብሳቢው አስታውሰው፤ ከህገወጥ የጦር መሳሪያና የገንዘብ ዝውውር እንዲሁም የሽብር እንቅስቃሴዎች በስተጀርባ እስከመጨረሻው ድረስ ተቋሙ ከኋላ ሆኖ የሀገርን ጥቅም፣ ሰላምና ደህንነት የማስከበር ሥራ መስራቱን ጠቅሰዋል።
‹‹ይህም ተቋሙ ምን ያህል በለውጥ ጎዳና ውስጥ እንዳለና ከህዝብና ከፓርላማው ጋር ተቀራርቦ እየሰራ እንደሆነ የሚያረጋግጥ ነው›› ብለዋል። ቋሚ ኮሚቴውና ተቋሙ ተቀራርበው መስራታቸው የሪፎርም ሥራው በትክክለኛ መስመር እንዲሄድ ከማድረጉም በተጨማሪ ሀገራዊ ለውጡም ከፀጥታ፣ ደህንነትና ከህግ የበላይነት አኳያ ሥራዎች ምን ያህል እየተሰሩ እንደሆነ አመላካች መሆኑንም ሰብሳቢው ጠቁመዋል።
አገልግሎቱ ምንም አይነት የፖለቲካ ወገንተኝነት እንዲሁም ዘርና ሃይማኖት ሳይኖረው የኢትዮጵያን ህዝብ ጥቅም ብቻ ይዞ መንቀሳቀስ እንዳለበት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተሰጠው የሥራ አቅጣጫ መሰረት ራሱን አደራጅቶ እየሰራ ስለመሆኑም ቋሚ ኮሚቴው ማረጋገጡን ሰብሳቢው ገልፀዋል። የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጄነራል ኮሚሽነር ደምላሽ ገብረሚካኤል እንዳሉት፣ተቋሙ በስድስት ወራት ውስጥ የሀገሪቱን ሰላምና ደህንነት ከማረጋገጥ አኳያ በርካታ ሥራዎችን አከናውኗል።
በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ የሽብር ጥቃት ለማድረስ አልሻባብና የአይ.ኤስ ቡድን አደጋ ለማድረስ ያቀዱትን እቅድ በማክሸፍ ተቋሙ ትልቅ ሥራ መስራቱንም አስታውሰው፤በዚህ ኦፕሬሽን 17 የሚጠጉ የሽብር ቡድኖች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አስታውቀዋል። በዚህ ኦፕሬሽን የተገኙ መረጃዎችን ለአሥራ ስድስት ሀገራት በመስጠት በሀገራቸው ላይ ተመሳሳይ ኦፕሬሽን በማካሄድ በጣልያን 15 የሚሆኑ የአልሻባብ ቡድን አባላትም እንደተያዙ ተናግረዋል። ኦፕሬሽኑ የተሳካ መሆኑን በማመንም የአሜሪካው የስለላ ድርጅት ሲ.አይ.ኤ ለተቋሙ ምስጋና መቸሩንም ገልፀዋል።
በሀገሪቱ የሚደረጉ የተለያዩ የገንዘብና የህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውሮችን ለመቆጣጠር በተለይም ከጎረቤት ሀገራት ከሶማሊያ፣ከሱዳን ኬኒያና ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር በቅንጅት በመስራት በርካታ ቁጥር ያለው ህገወጥ የጦር መሳሪያ መያዙንና ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የተለያዩ ሀገራት የውጪ ገንዘቦች መያዛቸውንም ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
ሙስናን ለመከላከል ሰፊ ሥራዎች እንደተሰሩና ከግብር ማጭበርበር ጋር በተያያዘም ከስድስት ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ገንዘብ ለማስቀረት መቻሉንም ያወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ብሄርንና ሃይማኖትን እንዲሁም ዩኒቨርሲቲዎችን ተገን በማድረግ የሚከሰቱ ግጭቶችን ለማስቀረትም ሰፋፊ ጥናቶችን አስቀድሞ በማከናወን ችግሮች እንዲፈቱ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በሀገሪቱ የብሄራዊ ደህንነት እቅድ እንዲዘጋጅ ተደርጎ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣የመከላከያ ሚኒስቴር፣የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የሰላም ሚኒስቴርና የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ በጋራ እቅድ አዘጋጅተው ክልሎችን፣ የክልል ፖሊስ ኮሚሽነሮችን፣ የሁለቱ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽነሮችንና የአስተዳደርና ፀጥታ ኃላፊዎችን በማሳተፍ እቅዱን ተግባራዊ በማድረግ ሰፊ ሥራ መሰራቱንም አመልክተዋል።
ተቋሙን ወደተሻለ ደረጃ መድረስ የሚያስችል አዋጅ ተጠናቆ በአዋጁ መሰረት የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ስያሜና ሎጎ እንደሚቀየርም ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመው፣በቅርቡ አዋጁ የሚፀድቅ ከሆነ የብሄራዊ መረጃ ማእከል የሚል ስያሜ እንደሚይዝም አስታውቀዋል።
የጥላቻ ንግግር አዋጅ በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚፀድቅ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፣አዋጁ ከፀደቀ በኋላም ተቋሙ የማህበራዊ ሚዲያዎችን ለመቆጣጠር የሚያግዙና አጥፊዎችን ለህግ ለማቅረብ የሚያስችል ቴክኖሎጂ በመጠቀምና ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ጋር በመሆን ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንም አያይዘው ገልፀዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 14/2012
አስናቀ ፀጋዬ