ዝቅ ማለት ከፍታ ላይ ያደርሳል እንዴ? አንድ ዓረፍተ ነገር ሰምተነው ግራ የሚያጋባን ጉዳይን ከመግለፅ በላይ የሆነን ቁም ነገር የጨበጠ ሆኖ ስናገኘው መመርመር እንጀምራለን። ከፍታ ላይ ለመገኘት ዝቅ ብሎ መጀመር የተሻለ ቦታ ላይ ለመገኘት ቀድሞ የሚያሽልን መጠጋት ግድ ይላል። በነገራችን ላይ ውዶቼ ለማትረፍ ተብሎ ካለ ላይ መቀነስ መሰጠትን ይጠይቃል።
ሁሉም እኮ የመስጠት ጣዕምን አይረዳም። እራስን አሸንፎ ከስግብግብነት መላቀቅን ከራስ ወዳድነት ስሜት መመንጨቅን ይጠይቃል። ይህ ደግሞ በመሰጠት ውስጥ ባለ መልካምና እራስን ከሌላው ቀጥሎ ማየትን ቀድሞ ከራስ ሌላ መኖርን ይፈጥራል። አቤት የዚህ ስሜትና ተግባር ጣዕሙ። እራሱን ለሌሎች ደስታ ምክንያት በመሆን ጣፋጭ የሆነን ደስታ ማግኘት ምንኛ መታደል ነው።
እኛ ጋር ያለ ውዳቂ ነገር ሌሎች ጋር የማይገኝና ውድ መሆኑ የማናውቅ ብዙ ነን። እኛ ተርፎን የምነደፋው ምግብ ብዙዎች ሽታው እንኳን እንደራቃቸው የማናስተውል በዝተናል። እያለን መስጠትን ካለመድን ስናጣ መቀበል እናውቅበት ይሆን እንዴ? የማይሰጡ እጆች መቀበል ይከብዳቸዋል። መስጠት ቁስን ብቻ አይደለም። በጎ ሐሳብ የሚለውጥ ሃሳብ አገር እና ሰውን ሊያቆም የሚችል ሁነኛ በጎ ተግባርም መስጠትን ይገልፃል።
በእርግጥ መስጠት ከመቀበል ቢልቅም በመስጠት ውስጥ የሚገኘው መንፈሳዊ ጠቀሜታ ተቀባይ ባልጠፋ ያሰኛል። እያለን መስጠትን የራቅነውን ያህል ስናጣ የምንቀበለው ይርቅብናል። መስጠት ለመልመድ ከሌለው የሚሰጥ ካጠረው ላይ ቆርጦ ለሌላ የሚለጥፍ ስናይ እራሳችንን እንድናይ እኔስ ምን ላይ ነኝ? ያለሁት የሚል ጥያቄ እንድናነሳ ያደርገናል።
ካለ ላይ መስጠት የሚቀለው ያህል ከሌላ ነገር ላይ ቀንሶ እንካችሁ ማለት ይገዝፋል። ከሌለ ላይ መስጠት ከባድ ነው፤ ነገር ግን መስጠት ያለው ፋይዳ ላወቀ ይገዝፍበታል። የበጎ ተግባር ያህል ውስጥን ሰላም የሚያስገኝ፤ የመልካም ሥራ ያህል ውስጥን የሚያድስ ተግባር ከወዴት ይገኝ ይሆን? አንዳንዱ ሰጥቶ የማይጠግብ፣ በጎ ምግብር አድርጎ የማይሰለች ለሰው ኖሮ የማይደክም የሆነው የመስጠትን ጣዕም በደንብ ስለገባው ነው።
እርግጥ መስጠት ወይም ደግነት እኛ ኢትዮጵያዊያን የማንታማበት ጉዳይ ሆኖ አብሮን ከርሞ አሁን ላይ ያረጀብን ቢመስልም የበጎነት እርጅና ወደ ሞት እንዳያመራ በአንዳንድ ተንከባካቢዎች ዛሬም ፈክቶ ይታያል። እዚህች አገር ላይ በበጎነት ስማቸው የናኘ በደግነት ትልልቅ ምግባሮችን የፈፀሙ ኢትጵያዊያን መርሳት ይከብዳል። ደጋግ ልቦች ደጋግ ነገሮች ሁሌም ያሳያሉ።
ሰሞኑን በማህበራዊ ገፆች አንድ ጉዳይ ብዙዎች ሲቀባበሉ አንዳንዶችንም ልብ የነካ ተግባር በአንድ ኬኒያዊ የጎዳና ተዳዳሪ ከሌለው ላይ በመቀነስ ለሰው ህይወት መትረፍ ምክንያት ስለሆነ ታደጊ የተሰራጨው መረጃ በእርግጥም የደግነት ጥግ የበጎነት ያልተገደበ ድንበር ያመላከተ ነበር። ጉዳዩ እንዲህ ነበር። ምስኪኑ የጎዳና ተዳዳሪ የሰራው ድንቅ ሥራ ይህ ነበር።
ስሙ ጆን ይባላል። የዕለት ጉርሱን ለምኖ በረንዳ የሚያድር ምስኪን ህፃን ነው። ታዲያ ጆን አንድ ዕለት እንደለመደው ትራፊክ መብራት ላይ መኪኖች ሲቆሙ በመስኮት ሄዶ መለመኑን ተያያዘው። ከበርካታ መኪኖች ገንዘብ ተቀብሎ ወደ አንዱ መኪና በመስኮት እጁን ይዘረጋል።ለዚህ ታሪክ መከሰት ዋንኛ ጉዳይም ይሄው ለዕርዳታ የዘረጋው እጁ ያስከተለው ጉዳይ ነበር።
ህፃኑ ጆን እጁን ሲዘረጋ የመኪናው መስኮት ሲከፈት ግላዲ ካማዳ ከተባለች ሴት ጋር ፊት ለፊት ይተያያል። ህፃኑ አንድ ነገር ያያል እናም ግላዲ ካማዳ ያረገችውን የኦክስጅን መተንፈሻ “ምንድነው?” ብሎ ይጠይቃታል። እሷም በሰው ሰራሽ መተንፈሻ ኦክስጅን የምትተነፍስ አይኗም በቅጡ የማያይ በእግሯ መንቀሳቀስ የማትችል በየዕለቱ ጤና ፍለጋ ሆስፒታል የምትንከራተት መታከሚያ ገንዘብ ያጣች 7 ዓመት ሙሉ በዚህ በሽታ የምትሰቃይ ምስኪን ሴት መሆኗን ትነግረዋለች።
ይህንን ያየው የጎዳናው ህፃን ጆን እንባውን መቆጣጠር አቅቶት ለልመና የዘረጋውን እጁን ሰብስቦ እጁን ዘርግቶ ከሌሎች ያገኘውን ጥቂት ገንዘብ ታከሚበት ብሎ ይሰጣታል። እንባውና ሁኔታው የገረማቸው መንገደኞችም በሁኔታው ተደንቀው የልጁን የሃዘን ገፅታ በምስል አስቀሩት። በዚህም አላበቃም የህፃኑ ምስል በፌስቡክ ይለቁታል። ከፎቶው ጋር አብረው ልጁ ምን አይቶ እንዳነባ በምን ልቡ እንደተነካ ጽፈው ፎቶውን ያጅቡታል።
ድፍን ኬንያ ይህንን ምስል ተቀባበለው። ሁሉም የልጁ ሐዘን አሳዘነው። ይህ ልጅ ምንም ሳይኖረው የዳቦ መግዣውን ከሰጠ እኛስ? የሁሉም ጥያቄ ሆነ። ስለ ጉዳዩ ተወራ፤ ስለ ችግርና መፍትሄው ተመከረ፤ በመጨረሻም ለህክምና የተጠየቀችውን 4 ሚሊዮን ሽልንግ ለመሙላት ሁሉም ያለውን እንካችሁ አለ።
ግላዲ በዚህ በጎዳና ህፃኑ ጆን ምክንያት ለህክምና የሚሆናት ገንዘብ በህዝብ መዋጮ ተሟልቶ ወደ ህንድ ተጉዛ ታክማ ኦክስጅኗን ጥላ ዛሬ በነፃነት፤ በመታገዣ ሳይሆን ተፈጥሮ በሰጣት ትተነፍሳለች፤ ትንቀሳቀሳለች። እንግዲህ እንዲህ ነው፤ ለመስጠት የግድ ሀብታም መሆን አይጠበቅብንም። ልስጥ ብሎ የተነሳም የሚሰጠው ፈፅሞ አያጣም። በጎ ሐሳብም ቢሆን ሌላን የሚያንፅ ሌላውን የሚያቆም ነውና።
እኛ መልካምነትን ተላምደን ወደ ሌሎች ማስረፅና ለሌሎች መልካም ገጠመኝ ምክንያት እንሆን ዘንድ፤ መልካምን ነገር አቅማችን በፈቀደው መልኩ እንተግብር። ምን አልባት አቅማችን ለመተግበር ካላበቃን፤ መልካም ነገርን ማዘዝና በበጎ ሐሳብ ጉዳዮች መግለፅ እንልመድ። ለመልካም ተግባር ማነሳሳት ካልቻልን ቢያንስ መልካም ነገር መመኘት የምናዘወትረው ተግባር ቢሆን ዓለም ምንኛ በቀናች ነበር። ደጋግ ዘመኖች እንዲመጡ በጎዎችን ያብዛልን አበቃሁ። ቸር ይግጠመን።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 13/2012
ተገኝ ብሩ