አዲስ አበባ፡- ወደ ውጭ የሚላከው የሰሊጥ ምርት መጠን ሳይጨምር ላኪዎች ቁጥር ከ30 ወደ አንድ ሺ 300 ማደጉን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስትር ዴኤታው አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ በመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ በሰጡበት ወቅት እንደገለጹት፤ የወጪ ንግዱ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈፃፀም መሰረት 14 ቢሊዮን መድረስ ቢኖርበትም ጭራሽ አሽቆልቁሏል። በ2003 ከነበረበት አራት ቢሊዮን ባለፈው በጀት ዓመት እጅግ ቀንሶ ሁለት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ደርሷል። ለዚህ ዋነኛው ቁልፍ ችግር ምርት አለመጨመሩ ሲሆን፤ በተቃራኒው የላኪዎች ቁጥር ግን እጅግ እያሻቀበ ይገኛል።
‹‹350ሺ ቶን ያህል የሰሊጥ የውጭ ንግድ በሃያ ላኪዎች ብቻ ይፈፀም ነበር።›› ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ አሁን ግን በሰሊጥ ላኪነት ብቻ ተመዝግቦ ያለው ሰው ቁጥር ከአንድ ሺ 300 በላይ ሆኗል ብለዋል። ምርቱ ሳያድግ ቀድሞ የነበረው የምርት መጠን ለእነዚሁ ላኪዎች ተበትኖ በሽሚያ ለዓለም ገበያ እየቀረበ መሆኑ ተጠቁሟል።
በዓለም አቀፍ ገበያ የሰሊጥ ምርት ጥሩ ገቢ የሚያስገኝ መሆኑን አመልክተው፤ ኢትዮጵያ ለዘመናት ሰሊጥ በማምረት የቆየች ቢሆንም አሁንም ድረስ በሄክታር የሚሰበሰበው ከሶስት ኩንታል እንደማያልፍ ተናግረዋል። ይህ የምርት መጠን አለማደግ ከሰሊጥ የምታገኘው ገቢ እንዳያድግ እንቅፋት የፈጠረ ሲሆን፤ በቅርቡ ዘሩን ከኢትዮጵያ በመውሰድ ወደ ምርት የገባችዋ ሱዳን ግን በሄክታር እስከ ሰባት ኩንታል ማምረት መጀመሯንን ጠቁመዋል። ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ኮትዲቭዋርና ናይጄሪያ እንዲሁም ታንዛኒያ በሰሊጥ ንግድ ከኢትዮጵያ በኋላ ወደ ዓለም ገበያ የተቀላቀሉ ቢሆንም በሄክታር ከሰባት እስከ አስር ኩንታል በመሰብሰብ ለገበያው የሚያቀርቡት የምርት መጠን በማደግ ላይ ይገኛል ብለዋል።
በጥራትም ሆነ በብዛት ምርትን የማሳደግ ጉዳይ እጅግ በጣም ወሳኝ ስትራቴጂ ሊሆን እንደሚገባ የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ነገር ግን የግብይት ሥርዓት ሰንሰለት ለዓለም የሚቀርበውን ምርት እንዲወደድ በማድረጉና የላኪዎች ቁጥር መጨመርም በላኪዎች መካከል ያለውን ውድድር መጨመሩ እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 13/2012
ምህረት ሞገስ