አዲስ አበባ፡- በ2012 በጀት አመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 95 ነጥብ 4 ሄክታር ከይገባኛል የፀዳና የለማ መሬትን ማዘጋጀቱን የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ኤጀንሲ አስታወቀ።
የኤጀንሲው የኮሙኒኬሽን ባለሙያ አቶ አብዮት ታዬ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት ፤የከተማ አስተዳደሩ ሊገነባ ላሰበው አምስት መቶ ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶችና በአስሩም ክፍለ ከተሞች ለተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት የሚውል ከይገባኛል የፀዳ 95 ነጥብ አራት ሄክታር የለማ መሬት አዘጋጅቷል፡፡
ኤጀንሲው፤ እጅግ የተጎሳቆሉና ወደ ኋላ የቀሩ የከተማዋን አካባቢዎች መልሶ ለማልማት፤ የልማት ተነሺዎችን ፍላጎት መሰረት በማድረግ ምትክ ቦታ፣ የጋራ መኖሪያ ቤት፣ እንዲሁም የቀበሌ ቤትና የካሳ ክፍያ በመክፈል ቦታዎቹን ነጻ ማድረጉንም ጠቁመዋል።
መንገዶች በሚሰሩበት ወቅት በግራና በቀኝ የሚገኙ ቦታዎችን ከይገባኛል ነፃ በማድረግ የወሰን ማስከበር ስራ ተሰርቷል፤ ለአብነትም ለኢትዮ ቴሌኮምና ለኤሌክትሪክ ሀይል አገልግሎት የዋሉ ምሰሶዎችን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የማንሳትና መንግስታዊና መንግስታዊ ላልሆኑ ተቋማት ለማህበራዊ አገልግሎት፣ ለሊዝ ወዘተ… የለማ መሬትን እያዘጋጀ ያስተላልፋል።
ኤጀንሲው በከተማዋ በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ አምስት ፕሮጀክቶችንም ወደ ስራ ለማስገባት በአካባቢው ለሚገኙ ነዋሪዎችና ተቋማት ለባለ ይዞታዎች ምትክ ቦታ የመስጠትና ካሳ የመክፈል ስራ እየሰራ ይገኛል። ከነዚህም ውስጥ የለገሀር መልሶ ማልማትና ፑሽኪን አደባባይ ወደ ስራ የገቡ ሲሆን፤ ሂልተን ጀርባ የሚገኘው የቤተመንግስት ማስፋፋያ ፕሮጀክትም ወሰን የማስከበር ስራው ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ቦታው ለልማት ክፍት ሆኗል።
ከዚህ በተጨማሪም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥረት የተጀመረውና ጎተራ አካባቢ የሚገኘው ሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ በይዞታ ላይ የሚገኘውን ንብረት ሙሉ ለሙሉ አንስቶ ቦታው ለመልሶ ማልማቱ ዝግጁ ሆኗል። ከዚህም በላይ የዲዛይን ስራው የተጠናቀቀና የግንባታው ወጪም ሙሉ በሙሉ የሚከናወነው በቻይናው ኤግዚን ባንክ በተገኘ ድጋፍ መሆኑን አቶ አብዮት ጨምረው ገልፀዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 13/2012
ፍሬህይወት አወቀ