አዲስ አበባ፡- የወጪ ንግድና የገቢ ንግድ ተቀላቅለው በመሰራታቸው አስመጪና ላኪዎች ኪሳራቸውን በተለያየ መልክ እያስመዘገቡ ያቀርቡ የነበረውን የውሸት ሪፖርት ለመከላከል ሁለቱም ለየብቻ ኦዲት ሊደረጉ መሆኑን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሚኒስትር ዴኤታው አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ ሚኒስትር ዴኤታው አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ በመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ ቀድሞ አስመጪ ብቻ የነበሩ በሙሉ ወደ ላኪነት ገብተዋል። እነዚህ የውጪ ነጋዴዎች የውሸት የኪሳራ ሪፖርት እያቀረቡ በመሆኑ፤ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከአሁን በኋላ የወጪ ንግድ ራሱን ችሎ ኦዲት መደረግ ያለበት መሆኑን ለገቢዎች አመልክተዋል።
የወጪ ንግድና የገቢ ንግድ (ኤክስፖርትና ኢምፖርት) ተቀላቅሎ ይሰራ ስለነበር የውጭ ነጋዴዎች ኪሳራቸው በገቢ ተካክሶ ወጪና ገቢን ማመጣጠናቸው ብቻ እንደትርፍ ተቆጥሮ ፈቃዳቸው ሲታደስ መቆየቱን አስታውሰው፤ ከአሁን በኋላ ግን የውጭ ንግድ እንደማንኛውም ንግድ ትርፋማ ሆኖ እንዲቀጥል የንግድ ፈቃድም ሲሰጥ ለወጪ ንግድም ሆነ ለገቢ ንግድ ለየብቻ ኦዲት በማድረግ እንደሚከወን አመልክተዋል።
‹‹ከሰርኩ እየተባለ በተደጋጋሚ የሚወጣው የውሸት ሪፖርት እንዲቆም ይህንን አሰራር ገቢዎችም እንዲከተለው መመሪያ አስተላልፈናል።›› ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ የወጪ ንግድ በገቢ ንግድ የሚካካስበት ሁኔታ ሊቆም መሆኑን ጠቁመዋል።
አስመጪዎች የውጭ ምንዛሬውን ለማግኘት ብቻ የሚላኩ ምርቶችን ከዓለም አቀፍ ዋጋው ውጪ እየሸጡ መሆኑን በማስታወስ፤ ይህ በመንግስት በኩል ለረዥም ጊዜ ያልተሰራበት የዋጋ ቁጥጥር ያልተደረገበት እና በአገር ውስጥም የዋጋ ግሽበትን ያባባሰ ተግባር በመሆኑ ችግሩን ለመፍታት በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 13/2012
ምህረት ሞገስ