የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ አልማዝ መርሻዬ ጎስቋላ ፊቷ ኑሮ ከእጅ ወደ አፍ እንደሆነባት ያሳብቃል። ችግሯን አስከፊ ያደረገባት ምንም አይነት የገቢ ምንጭ የሌላት፤ በኪራይ ቤት የምትኖር መሆኗ ብቻ አይደለም፤ ይልቁኑ አንድ ልጇን ያለአባት በማሳደጓና ለብቻዋ ችግሮችን መጋፈጧ ኑሮን እንድታማርር አስገድዷታል።
ልጇን በኮተቤ ብረሃነ ህይወት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የምታስተምረዋ ወይዘሮ አልማዝ ልጇ ለትምህርት ከደረሰችበት ጊዜ ጀምሮ ሌላ ፈተና ተባብሶ በመምጣቱ፤ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖ የሚያስጨንቋት ነገሮች ቁጥራቸው ጨምሯል።
ኑሮን ለማሸነፍ ጉልት ቁጭ ብላ በመቸርቸር፣ ልብስ በማጠብ፤ የተለያዩ ስራዎችን ስትሰራ ብትቆይም፤ ለእለት ጉርስ እንኳን መሸፈን አልተቻላትም። ለትምህርት ቤት የሚሆኑ የደንብ ልብስ፤ ደብተርና እስክብሪቶ መግዛቱ፤ ምሳ ማሰሩ የሁልጊዜ ጭንቀቷ ሆኖ ቆይቷል። እናት ሆና ልጇን በደንብ መመገብ አለመቻሏ የሁልጊዜ ቁጭቷ፣ ኀዘኗና ጭንቀቷ እንደነበር ትናገራለች።
‹‹ከዚህ ቀደም ምሳ የሌለ ጊዜ ልጄ በባዶ ሆዷ ተምራ ትመጣለች፤ አልፎ አልፎ የምትቀርበት ጊዜም ነበር። የሁል ጊዜ ሰቀቀኔና ጭንቀቴ ነው፤ ሳልመርጥ ያገኘሁት ስራ እሰራለሁ። ስራው ሁልጊዜ አይገኝም፤ አይዞሽ ባይ የሚረዳኝ ባለመኖሩ ከንቱ ልፋት እየሆነብኝ ተቸገርኩ እንጂ›› የምትለዋ ወይዘሮ አልማዝ፤ ልጇ የትምህርት ቤት ምገባ ተጠቃሚ ከሆነች በኋላ አንድ ሸክም እንደቀለለላት እየተሰማት መሆኑን ትገልፃለች።
‹‹የቁርስና ምሳ ጭንቀቴ ተቃሎልኛል፤ ምገባው ተጠቃሚ ያደረገው ልጄን ብቻ አይደለም፤ ለእኔም የስራ እድል በመፍጠር በኢኮኖሚ እየደገፈኝ ነው። ስራ አግኝቼ መስራቴ በራሱ ትልቅ ደስታ ፈጥሮልኛል›› ትላለች። ‹‹ምግብ ለልጄ ሰርቼ የምሰጣት እኔው ነኝ፤ እኔም ተመግቤ ልጄንም እመግባታለሁ፤ ይህ ትልቅ እድል ነው። እንዳይቋረጥ እንዲቀጥል ፈልጋለሁ፤ ለእስከአሁኑ መንግስትን አመሰግናለሁ›› በማለት ትገልጻለች።
‹‹ስራ የለኝ፤ የባለቤቴ ስራ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ልጄን ወደ ትምህርት ቤት የምልከው በቤተሰብ እርዳታ ነበር። አሁን ከብዙ ጭንቀት ተገላግያለሁ። ልጄ ቁርስና ምሳ መመገብ ብቻ ሳይሆን የትምህርት ቤት ቁሳቁስ ተሟልተውለት መማሩ ያስደስታል። እኔም ለራሴ ገቢ እንዲኖረኝና የስራ እድል እንዳገኝ ተመቻችቶልኛል›› የሚሉት ደግሞ ወይዘሮ ቤተልሔም ነጮ ናቸው።
እንደወይዘሮዋ ገለፃ፤ ይህ እድል ለብዙ እናቶች እሮሮ ምላሽ በመስጠት እፎይታ የፈጠረ ነው። እዚህ ተደራጅተው መስራት መቻላቸው፤ በራሳቸው እንዲተማመኑ ሞራል ሰጥቷቸዋል። የተፈጠረው የስራ እድል ክፍያው ዝቅተኛና የጊዜውን ሁኔታ ያላገናዘበ መሆኑ፤ ክፍያው በወቅቱ አለመለቀቁ እንቅፋት ቢሆንም አሁንም ደስተኞች ናቸው።
እጹብ ድንቅ ጥሩነህ ትባላለች። የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ናት። ምግብ ሳትይዝ ወደ ትምህርት ቤት የምትሄድባቸው ጊዜያት በርካታ ነበሩ። ለዚህ እናቴ በብቸኝነት በማሳደጓ፤ የገቢ ምንጭ የሌላት መሆን ምግብ ከምትይዝበት የማትይዝበት ጊዜያት ይበልጡ እንደነበር ትናገራለች።
‹‹ሳልበላ የዋልኩ ቀን ትምህርቴን በመከታተል ያቅተኛል፤ ጓደኞቼ ሲበሉ ይከፋኛል፤ የበታችነት ስሜት ይሰማኝ ነበር። ምገባ ከተጀመረ በኋላ ግን ይህ ሁሉ ተለውጧል የተሻለ ተስፋ አለ›› በማለት ትናገራለች። የእዚሁ ትምህርት ቤት መምህርቷ ወይዘሮ ገነት እንግዳ የተማሪዎች ምገባ ለወላጆች እረፍት፤ ለተማሪዎችም ጸባይ መሻሻል ምክንያት ነው። ከዚህ በፊት የምግብ ችግር የነበረባቸው ተማሪዎች በትምህርታቸው ዝቅተኛ ውጤት ያመጡ ነበር ይላሉ።
‹‹ለትምህርት ፍላጎት ያልነበራቸውና የሚያቋ ርጡ በርካታዎች ነበሩ። አሁን ግን ትምህርታቸውን ያቋረጡ ተማሪዎች ሳይቀር ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው›› የሚሉት መምህርቷ፤ ከማጣታቸው የተነሳ ከሌሎች ተማሪዎች ነጥቆ እስከ መብላት ይደርሱ እንደነበር ይናገራሉ። ከምገባ በኋላ ግን ነጥቆ መብላት ቀርቷል። የትምህርት አቀባበል የተሻሻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል ካሉ በኋላ፤ ወደፊትም ከዚህም በላይ እንደሚሆን እምነታቸው መሆኑን ይናገራሉ።
የስድስተኛ ክፍል ተማሪው አቤል አበራ ከሁለት ዓመት በፊት በምግብ እጦት ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ከተገደዱ ተማሪዎች መካከል አንዱ ነው። ‹‹እናቴ እኔን ለማስተማርም ሆነ ለመመገብ አቅም የሌላት በመሆኑ፤ ገጠር ወደሚገኙ ዘመዶቼ ተልኬ ነበር። ነገር ግን በመምህራኖቼ ጥረት ልመለስ ችያለሁ። የምገባ ተጠቃሚ መሆኔ ከእናቴ ጋር እንድኖር አግዞኛል›› በማለት ይናገራል ።
‹‹እናቴ ለምሳና ለቁርሴ የምትጨነቀው ጭንቀት ብዙ ጊዜ ይጋባብኝ ነበር፤ ስለሚርበኝ ትምህርቴን እየተማርኩ ሆዴን አስብ ነበር። ምግብ ሳልበላ ብዙ ጊዜ አሞኝ ያውቃል። አሁን ግን ደስ ብሎኛ ትምህርቴንም በአግባብ እየተከታተልኩ ነው።›› ይላል።
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ አበበ ቸርነትም የተማሪዎች ምገባ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ሰጥቷል። የተወሰኑ ተማሪዎች ምግብ ሳይበሉ ትምህርታቸውን የሚከታተሉበት የነበረ ሂደት በመቀየር በአግባቡ እንዲከታተሉ ትልቅ አስተዋፅኦ እያደረገ ይገኛል። ከዚህም ባለፈ ለወላጆች ስለልጆቻቸው ቁርስና ምሳ እንዳያሰቡ ያደረገ፤ በወላጅ ላይ የሚያመጣውን ኢኮኖሚ ጫና የቀነሰ ነው ይላሉ።
‹‹ከ10 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ለከተማዋ ነዋሪዎችና የተማሪ ወላጆች የስራ እድል የፈጠረ ነው። የኢኮኖሚ ተጠቃሚ አድርጓቸዋል፤ ወላጆች ለልጆቻቸው ትምህርት ቤት ምግብ የሚያወጡትን ወጪ ቀንሶላቸዋል። ይህንን ስራ የሚሰሩ አነስተኛ ገቢ ያላቸው አካላት የተማሪ ወላጆች ሲሆኑ፤ የገቢ ምንጭ በማግኘት ላይ ናቸው›› ይላሉ።
ጨምረውም በዋናነት ተማሪዎች ለትምህርታ ቸው ትኩረት እንዲሰጡ አድርጓቸዋል። እየራባቸው የሚማሩም ሆነ ባዶ ምሳ እቃ ይዘው መጥተው ከጓደኞቻቸው ጋር ተቀምጠው የሚሳቀቁ ተማሪዎች የሉም ይላሉ። ስለዚህ ተማሪዎች በለጋ እድሜያቸው የሚሰማቸውን የበታች ስሜት ለማስወገድ ያስቻለ መሆኑ መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑንም ነው አቶ አበበ ያብራሩት።
በከተማ አስተዳደሩ በተዘጋጀው መመሪያ መሰረት በትምህርት ቢሮ ውስጥ ምገባውን የሚቆጣጠር አካል አለ። ይህን ይበልጥ ለማጠናከር ራሱን የቻለ ኤጀንሲ ለማቋቋም ውሳኔ መተላለፉን አቶ አበበ ይናገራሉ።
‹‹በምገባ ሂደት ላይ በርካታ ችግሮች አሉ። ተደራጀተው የምገባ አገልግሎት የሚሰጡት እናቶች ታክስ ይከፍላሉ። ይህ ደግሞ በስራው ላይ እንቅፋት እየፊጠረ ይገኛል። ‹ታክሱ ይቅርልን› የሚል ጥያቄም እየቀረበ ነው። ይህ ችግር እስካአሁን አልተፈታም። በሂደት የሚታይ ይሆናል ብለዋል።
ሌላው በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች ላይ የመብራት አለመኖር፤ በመጋቢ እናቶች መካከል ተቀናጅቶ ያለመስራት፤ አልፎ አልፎ የሚታዩ ችግሮች አሉ። የመመገቢያ ቦታዎች፤ የማብሰያ አዳራሾች በቀጣይ ለማቋቋም ኤጀንሲው ክትትል እየተደረገ የሚሰራ መሆኑንም ያብራራሉ።
በአዲስ አበባ የተማሪዎች ምገባ ከጥቅምት ወር ጀምሮ በሁሉም የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ከመዋዕለ ሕፃናት እስከ ስምንተኛ ክፍል ለሚማሩ 300 ሺህ በላይ ተማሪዎች ተግባራዊ ማድረጉ ይታወሳል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 13/2012
ወርቅነሽ ደምሰው