አዲስ አበባ:- የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባሳለፍነው በጀት ዓመት ከ20ሺህ በላይ መዝገቦች ዕልባት መስጠቱን አስታወቀ፡፡
ፍርድ ቤት ትናንት የዳኝነት ዘርፉ ያለበትን ሁኔታ አስመልክቶ ለህዝብ ተወካዮች፤ ለአስፈጻሚው አካል፤ ለፌዴራል ዳኞች፣ ለልማት አጋር ድርጅቶችና ለሌሎች ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት “የዳኝነት ዘርፉ አሁናዊ ሁኔታና የወደፊት ዕይታ” በሚል መሪቃል በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን አዳራሻ በተዘጋጀው ጉባኤ ላይ ያለፈውን ዓመት የስራ አፈፃፀሙን ሪፖርት አቅርቧል ፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ዳኞች በሶስቱም ፍርድ ቤቶች ምቹ የስራ ቦታ እና ግብዓት ሳይኖራቸው በ2011 በጀት ዓመት ለሃያ ሺህ አንድ መቶ መዝገቦች እልባት ሰጥተዋል። ይህም የእቅዱን 85 ነጥብ 5 በመቶ ሲሆን እንደ ጅምር አበረታች መሆኑ ገልጸዋል፡፡
ፕሬዚዳንቷ የዳኝነት አካሉ ህዝባዊ አመኔታ ያተረፈ እንዲሆን ለማድረግ በ2011 ዓ.ም አዳዲስ አመራሮች መሾማቸውንና አመራሮቹ የዳኝነት አካሉን ለማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራትን ከፍርድ ቤት ማህበረሰብ ጋር እያከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ይህ ዓይነቱ መድረክ ዲሞክራሲ በአደገባቸውና የዳኝነት ነፃነት በተጠናከረባቸው ሃገራት ወይንም በዚህ ረገድ እርምጃ በመውሰድ ላይ ባሉ ሃገራት የተለመደ እንደሆነ የጠቀሱት ፕሬዚዳንቷ በዚህ ዓመት የተዘጋጀው መድረክ የመጀመሪያው ሆኖ በቀጣይነት በየዓመቱ ፍርድ ቤቶች ስራ ከመጀመራቸው በፊት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለህዝብ ስራውን የሚያስታውቅበት መድረክ ሆኖ የሚካሄድ መሆኑም ገልጸዋል፡፡
ይህም ስለ ፍርድ ቤቶች ተግባርና እቅድ ለህዝብ በማሳወቅ ግልፅነትን በፍርድ ቤቶችና በህዝብ መካከል ከመፍጠሩ በተጨማሪም የፌዴራል ፍርድ ቤቶችን የዓመቱን የትኩረት አቅጣጫዎች ለሌሎች የመንግስት አካላት በማሳወቅ በጋራ መስራት የሚቻልበትን ሁኔታ ለማሳየት መድረኩ ያግዛል ተብሏል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 12/2012
አብርሃም ተወልደ