አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ የራሷ ንብረት በሆነችው ETRSS-1 የመሬት ምልከታ የሳተላይት ዓይኖች ከትናንት ጀምሮ ከህዋ ላይ ምድርን መቃኘት ጀምራለች።
የመጀመሪያዋ የስፑትኒክ ሳተላይት በ1957 እ.ኤ.አ ወደ ህዋ መወንጨፍን ተከትሎ በአሁኑ ወቅት 70 የአለማችን ሀገራት በሺዎች የሚቆጠሩ ሳተላይቶች ያሏቸው ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 9ኙ ከአፍሪካ አህጉር ናቸው፤ ኢትዮጵያም በETRSS-1 ከእነዚህ ሀገራት አንዷ መሆን ችላለች።
ለሙከራ ሳይሆን ለተልእኮ የተገነባችው የመሬት ምልከታ ሳተላይት ኢትዮጵያን ከአፍሪካ በአምስተኛ ደረጃ ላይ ማስቀመጥ ችላለች፡፡ የሳተላይት ማልማትና እንጦጦ ላይ መቆጣጠሪያ፣ ትእዛዝ መስጫና የመረጃ መቀበያ ስራ በ2010 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ተጀምሮ በህዳር ወር 2012 ሙሉ በሙሉ ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡
ለሳተላይቷ እና እንጦጦ ላይ ለተገነባው መቆጣጠሪያ፣ ትእዛዝ መስጫና መረጃ መቀበያ ጣቢያ ከቻይና መንግስት 6 ሚሊዮን ዶላር፣ ከኢትዮጵያ መንግስት 20 ሚሊዮን ብር እንዲሁም ከተለያዩ አካላት ድጋፍ 10 ሚሊዮን ብር የተገኘ ሲሆን በአጠቃላይ 210 ሚሊዮን ብር ወጭ ተደርጓል፡፡
72 ኪ.ግ የምትመዝነው ሪሞት ሴንሲንግ ሳተላይት ወደ ህዋ በተላከች በግማሽ ሰዓት ውስጥ የታሰበላትን ስፍራ በመያዝ ከ700 ኪ.ሜ ርቀት ላይ መረጃ ወደ መሬት መላክ ጀምራለች፡፡ ይህቺ ሳተላይት በእንጦጦ የሳተላይት መቆጣጠሪያ እና መረጃ መቀበያ ጣቢያ የደህንነት ክትትል የሚደረግላት ሲሆን ከሳተላይቷ የሚገኙ መረጃዎችም በዚሁ ማዕከል እየተሰበሰቡ ይተነተናሉ፡፡
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በተሳካ ሁኔታ ወደ ህዋ ደርሳ መረጃዎችን ማቀበል የጀመረችውን ETRSS-1 ሳተላይት በተመለከተ የኢትዮጵያን ህዝብ እንኳን ደስ አላችሁ ባሉበት የተንቀሳቃሽ ምስል መልዕክት ሳተላይቷ ኢትዮጵያውያን በአፍሪካና በአለም ገበያ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ውድድር እንዲያደርጉ እንደምታግዝ ተናግረዋል፡፡
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለፃ እስከአሁን የኛ የሆነ ሳተላይት ባለመኖሩ ምክንያት ምስሎች ከተለያዩ ሀገራት በግዢ ይገኙ እንደነበር በመግለፅ ETRSS-1 በድንበር አካባቢዎች ያሉ እንቅስቃሴዎችን፣ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ለመከታተል፣ የአየር ሁኔታን ለማየት፣ የግብርናን ሁኔታ ለማዘመን፣ በቂ መረጃ ሰብስቦ በመተንተን ስራችንን እንድንሰራና ለውድድር እንድንበቃ መሰረት ሆና የምታገለግል ይሆናል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዚህች ሳተላይት ወጪ በአብዛኛው በቻይና መንግስት የተሸፈነ መሆኑን በመግለፅ ወደፊት ከተለያዩ ሀገራት ጋር በጋራ በመሆን አዳዲስ ሳተላይቶች የሚመረት መሆኑን አስታውቀው በዚህችኛዋም ላይ ኢትዮጵያውያን ምሁራንም ከዲዛይን ጀምሮ እስከ ምርት የተሳተፉ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
የቁጥጥር ማዕከሉ ሙሉ በሙሉ አዲስ አበባ ላይ የተሰራ መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ወደ ምህዋር በሚደረገው እንቅስቃሴ የመረጃና የእውቀት ፍለጋ ጅማሮዋን ‘ሀ’ ብላ የጀመረችና በፍጥነት የምታስቀጥል ሲሆን ወደ ብልፅግና የምታደርገው ጉዞ መጀመሩንም የምናረጋግጥበት እድል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በቻይና የሳተላይት ማስወንጨፊያ ጣቢያ የተከናወነውን የሳተላይት ማምጠቅ ስነ ስርዓት ለመከታተል በእንጦጦ ኦብዘርቫቶሪና ምርምር ማዕከል በተገኙበት ወቅት ባደረጉት ንግግር ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ህዋ የተወነጨፈችው ETRSS-1 የመሬት ምልከታ ሳተላይት ለኢትዮጵያ የብልፅግና ጉዞ ታሪካዊ መሰረት የምትጥል መሆኗን ተናግረዋል፡፡
አቶ ደመቀ በንግግራቸው ኢትዮጵያ ዓለምን በተወዳዳሪነትና በፍጥነት መቀላቀል እንዳለባት በማመልከት ይህ የሳተላይት ማምጠቅ ጅምር ጉዞ አንዱ ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል። ኢትዮጵያውያን ጨለማን እየፈራን ብርሃን የምንናፍቅ ህዝቦች እንዳልሆንን በተግባር ያረጋገጥንበት ታሪካዊ ውጤት ነውም ያሉት አቶ ደመቀ ሀገራችን ከየብስ ተሻግራ በህዋ ሳይንስ ሊኖራት የሚገባትን የተወዳዳሪነት አቅም ከወዲሁ መገንባት እንደሚያስፈልግ በአፅንኦት አሳስበዋል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አህመዲን መሀመድ በበኩላቸው ይህ ሳተላይት የማምጠቅ ስራ ኢትዮጵያውያን ኩሩ ህዝቦች እንዲሆኑና ሀገሪቱን ከድህነት ለማላቀቅ እየተሰሩ ካሉ ስራዎች አንዱ መሆኑን ጠቅሰው ለህዋ ሳይንስ መንግስት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያውያንን ከግምት ወደ እርግጠኝነት፣ ከተውሶ መረጃ ወደ ባለቤትነት እና ከሩቅ ተመልካችነት የራስ ወደማድረግ ያሸጋገረችው ይህቺ ሳተላይት ወደፊት በእድገት ጎዳና ለመስፈንጠር የምናደርገውን ጉዞ ለተተኪ ትውልድ የምናሳይባት እንደሆነችም ሚኒስትር ዴኤታው ገልፀዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዘርፉ የተግባቦት ሳተላይት ልማትና የሳተላይት መገጣጠሚያ ፍብረካና ፍተሻ ማእከል ግንባታን ለመጀመር አቅዳ እየተንቀሳቀሰች እንደሆነም ዶክተር አህመዲን ጨምረው ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ታን ጂአን ሀገራቸው የኢትዮጵያን ሳተላይት በስኬት ማምጠቅ በመቻሏ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው የቻይና ህዝብና መንግስት ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ዘርፈ ብዙ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
በዝግጅቱ ላይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የሁለቱ ምክር ቤቶች አባላት፣ የመከላከያ አመራሮች፣ ዲፕሎማቶች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
የህዋ ሳይንስ ፕሮግራም በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ስር ሆኖ ተጠሪነቱ ለኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሲሆን በስፔስ ሳይንስ፣ በስፔስ ቴክኖሎጂ፣ በስፔስ አፕሊኬሽን፣ በሰው ሀይል አቅም ግንባታ፣ በስፔስ ጥናትና ምርምር እንዲሁም በሳተላይት ልማትና ሌሎች ተዛማጅ ዘርፎች ጉልህ አስተዋፅዖ እያበረከተ ይገኛል፡፡
ትናንት ወደ ህዋ የተላከችውና ስራዋን የጀመረችው ሳተላይት ለሰፊው የኢትዮጵያ አርሶአደር ከግብርና ጋር የተያያዙ መረጃዎችን በማድረስ ይበልጥ ተጠቃሚ እንደምታደርግ ተነግሯል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 11/2012
ድልነሳ ምንውየለት