ከአንድ ዓመት በኋላ ‹‹ሊትል ኢትዮጵያ›› ሳተላይት ትመጥቃለች
አዲስ አበባ፣ የመጀመሪያዋ የኢትዮጵያ ሳተላይት ETRSS-1 ምድርን መቃኘት መጀመሯንና ወደ እንጦጦ ኦቭዘርቫቶሪ ማዕከልም መረጃ መላክ መጀመሯን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።ከአንድ አመት በኋላ ‹‹ሊትል ኢትዮጵያ›› በሚል የተሰየመችው ሳተላይት እንደምትመጥቅ ተገለጸ።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ጀማል በከር ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት ትላንት ከሌሊቱ 12፡21 ደቂቃ ወደ ህዋ የመጠቀችው ETRSS-1 ወደ ህዋ በተላከች በግማሽ ሰአት ውስጥ የታሰበላትን ስፍራ በመያዝ ከ700 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በመሆን ምድርን መቃኘት ጀምራለች።
የሳተላይት ማልማትና የመቆጣ ጠር ስራው በ2010 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ተጀምሮ በህዳር ወር 2012 ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁንና ከትላንትም ጀምሮ ወደ ህዋ የተላከችው ሳተላይት እንጦጦ ከሚገኘው ኦቭዘርቫቶሪ ማዕከል ጋር ግንኙነት በማድረግ መረጃ መላክ መጀመሯን ሚኒስትር ዴኤታው አስታውቀዋል።
ሳተላይቷ 14 የሚጠጉ መረጃዎችን የማስተላለፍ አቅም ቢኖራትም ለተወሰ ጊዜ በአራት ዘርፎች ማለትም ድንገተኛ አደጋዎችን፤ ግብርናን፤የአካባቢ ጥበቃንና የማዕድን ሃብትን የተመለከቱ መረጃዎች ብቻ ትኩረት እንደሚደረግባቸው አቶ ጀማል በከር ገልጸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም ኢትዮጵያ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጨማሪ ‹‹ሊትል ኢትዮጵያ›› በሚል የተሠየመች ሳተላይት ለማምጠቅ ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደምትገኝ የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ አስታውቋል።
የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሽፈራ ፈይሳ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል እንደገለፁት፤ ለዓመታት በእቅድ ደረጃ የነበረው ሳተላይት የማምጠቅ ተግባርን ወደ ተግባር ለማሸጋገር የሚያስችሉ ዝግጅቶች እየተከናወኑ ሲሆን በሚቀጥለው ዓመትም ሳተላይት ለማምጠቅ መወሰኑንም ተናግረዋል።
ሳተላይቱ ከመሬት ሆኖ ለመቆጣጠር የሚያስችል ጣቢያ ግንባታም በአዳማ ሳይንስና ቴክሎጂ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ የተገነባ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም ሥራው በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን አስገንዝበዋል። ቀደም ሲል የኮሪያ ኤሮ ስፔስ ኤጀንሲ ኃላፊ የነበሩ ኮሪያዊ ፕሮፌሰር በአሁኑ ወቅት ፕሮጀክቱን ወደ ተግባር ለማሸጋገር ከፍተኛ ዕገዛ እያደረጉ ይገኛሉ። በዚሁ ሂደትም አምስት ኢትዮጵያዊ ተመራማሪዎች የሳተላይቱን ሲስትም እያሳደጉ ሲሆን ጎን ለጎን የሦስተኛ ዲግሪያቸውን በሳተላይት ቴክኖሎጂ እየተማሩ ይገኛሉ።
እንደ ዶክተር ሽፈራው ገለፃ፤ ሥራውና ምርመሩ በጥንቃቄ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው በአሁኑ ወቅት ስፔስ ውስጥ ነፃ የሆኑ ሳተላይችን ሰብሮ የመግባት አቅምና እውቀት ላይ መድረስ መቻላቸውን አስገንዝበዋል።
ቀደም ሲል ዩኒቨርሲቲው በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሥር የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ለሳንይስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ስር እንዲተዳደር የተወሰነ
ሲሆን፤ ሚኒስቴሩም አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል። መንግስትም ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት እንደሰጠው አረጋግጠዋል። ምንም እንኳ ምርምሩ በጥሩ ሁኔታ ላይ ቢሆንም ችግሮችም መኖራቸውም ጠቁመዋል።
እንደ ዶክተር ሽፈራ ገለፃ፤ ለመሰል ተግባራት የምርምር ግብዓትና መሠረተ ልማት አስፈላጊ ነው። ይሁንና አንዳንዶቹ ግብዓቶች ከአገር ውስጥ አይገኙም። ግብዓቶቹን ለማግኘትም የግዥ ህግን መጠበቅ ግዴታ ነው። በዚህ ወቅት ደግሞ ተመራማሪዎች ሥራ ላይ ጫና እንደሚፈጥር አረጋግጠዋል።
ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በተገኘው መረጃ መሰረት ወደ ህዋ የምትላከው ሳተላይት ወታደራዊ መረጃዎችን ለማደራጀት፣ ግብርናን መዘመን፣ የመሬት ፎቶዎችን ለማንሳትና መረጃ ለመተንተን፣ የሜትሮሎጂ መረጃዎችን ለማወቅና በአስፈላጊው ሁኔታ ለመጠቀም፣ ብሎም ወደ ስፔስ የሚደረጉ ጉዞዎች ለማቀላጠፍ ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖራታል ተብሎ ይታመናል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 11/2012
ክፍለዮሃንስ አንበርብር