አዲስ አበባ፡- ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ህዋ የተወነጨፈችው የኢትዮጵያ የመሬት ምልከታ ሳተላይት የምትሰበስባቸው መረጃዎች ለልማት እንቅስቃሴዎች አጋዥ ከመሆኑም ሌላ ለኢትዮጵያውያን ታጊዎች መነቃቃት እንደሚፈጥር የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስና የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ ገለፁ።
የየፓርቲዎቹ ሊቀመናብርት በየበኩላቸው በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ወደ ህዋ የተላከችው ሳተላይት መረጃዎችን በማቀበል የተለያዩ የልማት ስራዎችን ለማከናወን ጥቅም የምትሰጥ ናት።በተጨማሪም ኢትዮጵያ ልክ እንደሌሎች አገራት ሁሉ ሳተላይት ማምጠቅ መቻሏ ታዳጊዎቿን የሚያነቃቃና በዘርፉም ለመሰማራት ለሚፈልጉ እድል የሚከፍት ነው።
እንደ ፕሮፌሰር በየነ ገለፃ፤ ኢትዮጵያ ትልቅ አገር እንደመሆኗ ሳተላይት ማምጠቅ የነበረባት ቀደም ሲል የነበረ ቢሆንም ዛሬም ቢሆን አይረፍድባትም። ቀደም ሲል የጀመሩት ራዕይ ያላቸው ሰዎች እንደ እነ ዶክተር ለገሰ ወትሮ አይነት ሰዎች ናቸውና ህልሙ እውን ሆኖ መሳካቱ በጣም መልካም ነው።
አገሪቱ ለምታካሂደውም ልማት ጥቅሙ ከፍ ያለ ነው። ቀደም ሲል መረጃ የሚገኘው ከሌሎች ሀገራት በግዢ ሲሆን አሁን ግን የተላከችው ሳተላይት ኢትዮጵያ በምትፈልገው ሁኔታ የመሬት ምልከታዋን መቆጣጠር ያስችላታል። ስለዚህም የተሻለ መረጃ ማግኘት ስለሚቻል መልካም ክንዋኔ ነው።
‹‹ይህ ጅማሬ ነው፤ በቀጣይ ደግሞ የተሻለ እንደሚሆን አምናለሁ።›› ያሉት ፕሮፌሰር በየነ፣ ‹‹ወጣቱም ሆነ ታዳጊው ይህን በማየቱ መነሳሳትን ያገኛል።በተለይም ታዳጊዎችም የተሻለ ህልም እንዲኖራቸው ያደርጋል። በተጨማሪም በመስኩ ለመሰማራት የሚፈልጉትን ይበልጥ የሚያበረታታ ነው።›› ብለዋል።
ቀደም ሲል እንዲህ አይነቱን ሙከራ በሚያደርጉ አካላት ላይ ይሰነዘር የነበረው ‹ዳቦ ላልጠገበ ህዝብ ይህን ማሰብ ቅዠት ነው› የሚል እንደነበር ፕሮፌሰር በየነ አስታውሰው፤ ዛሬ ግን እውን ሆኖ ማየት መቻሉ የሚያስደስት ሆኖ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
በብዙዎቹም ዘንድ በድህነት ውስጥ ላለች አገርና ድህነትም ያስመረራት አገር ለሳተላይት ቅድሚያ መስጠቷ ምን ያደርጋል የሚሉም ወገኖች ዛሬ ኢትዮጵያ መልካም ጅማሬ ላይ መሆኗን እና ይህም ቀጣይነት እንደሚኖረው ተስፋ ማድረግ እንደሚገባም አመልክተዋል።
‹‹ጥንስሱ ለረጅም ዓመታት የቆየ ቢሆንም ዛሬ ላይ ውጤት ማየት በመጀመሩ ይበል የሚያሰኝ ነው። ስለዚህም በወቅቱ ጉዳዩን የጀመሩ አካላት አለመሳሳታቸውን መናገር እፈልጋለሁ። በመሆኑም አገሪቱ በተለያዩ አቅጣጫዎች ብሩህ ተስፋ እንዳላት ማስተዋል ይቻላል፤ አፍራሽ የሆኑ ነገሮችን ታግለን እስካሸነፍን ድረስ ብሩህ ተስፋችን ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም።›› ሲሉም ፕሮፌሰሩ ገልፀዋል።
ዶክተር ደሳለኝ በበኩላቸው፤ የተላከችው ሳተላይት ያላት ጠቀሜታ ብዙ መሆኑን ጠቅሰው ምንም እንኳ ሳተላይቷ በመጠን ትንሽ ብትሆንም መረጃዎችን በመሰብሰብ ለልማት እንቅስቃሴዎች እንደምትጠቅም አመልክተዋል። ህፃናት አገሪቱ ሳተላይት ማምጠቅ ትችላለች ብለው እንዲያስቡና የሳተላይት ፕሮግራሞችን እንዲያጤኑ ማነቃቂያ እንደሚሆንም እምነታቸውን ተናግረዋል።
እንደ ዶክተር ደሳኝ ገለፃ፤ በሳተላይት የሚገኘው መረጃ ዛሬ ላይ ለሁሉም የልማት እንቅስቃሴዎች ጥቅም የሚሰጥ ነው። ለአብነትም የከተማ ፕላን ለማውጣት፣ የእርሻ ስራን ለማዘመን፣ የአየር ፀባይ ለውጥን ለመከታተልና የእያንዳንዱን እንቅስቃሴ መረጃ ለማስተሳሰር እንዲሁም የጎርፍና የእሳት አደጋን መከሰት አስቀድሞ ለማወቅና ሌሎችንም ጉዳዮች ለመተንበይ ፋይዳው ጎልህ ነው። ጅማሬውም መልካም ነው።
ከቻይና የሳተላይት ማምጠቂያ ጣቢያ ትናንት ማለዳ ላይ ወደ ህዋ የተላከችው ሳተላይት መረጃዎችን መሰብሰብ መጀመሯ ታውቋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 11/2012
አስቴር ኤልያስ