ጎሬ ማሻ፡- የደቡብ ብሔር ብሔረሰብ፣ የጋንቤላ እና የኦሮሚያ ክልሎችን በአቋራጭ የሚያገናኘው የጎሬ -ማሻ የአስፓልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ተጀመረ፡፡
140 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚሸፍነው የአስፓልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ የጅማ፣ ሚዛን ቴፒ፣ ቦንጋ፣ ጋንቤላ፣ ጎሬ፣ መቱና አዲስ አበባ ከተማን በአጭር ርቀት ያገናኛል ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የኮሚኒኬሽን ዳይሬክቶሬት፤ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ የመንገድ ፕሮጀክቱ በ4 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ለመገንባት ጨረታውን ያሸነፈው የደቡብ ኮርያ ሀይወንዳይ ዴቨሎፕመንት ካምፓኒ ሲሆን፤ ሱሶንግ ኢንጅነሪንግ አገር በቀሉ ኔት ኮንሰልቲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በጋራ ይሠራሉ፡፡ የግንባታው ወጪ በኢትዮጵያ መንግስትና በኮርያው ኢድቫይዚንግ ባንክ ይሸፈናል፡፡
የሥራ ተቋራጩ የካምፕ ግንባታውን አጠናቆ የመንገድ ግንባታውን የጀመረ ሲሆን፤ የቆረጣና የአፈር ጠረጋ ሥራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡ በዚህም ከጅማ- ቦንጋ- ሚዛን ቴፒ እና ከጋንቤላ- ጎሬ መቱ -አዲስ አበባ የሚያገናኘው መንገድ ከዚህ በፊት አስቸጋሪ የነበረውን ጉዞ ይፈታል ተብሎ ታምኖበታል፡፡
በአካባቢው የተሻለ መንገድ ባለመኖሩ የገበያ ትስስር እንዳይፈጠርና እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል፡፡ በአካባቢው የማር፣ የቡናና ቅመማቅመም የሚመረት ቢሆንም ምርቱ ተጠቃሚዎች በመንገድ ችግር ምክንያት መድረስ እንዳልቻሉ ተገልጿል፡፡ በመሆኑም የመንገድ ግንባታ አገሪቱን ከግብርናው ወደ ኢንዱስትሪ መር ለማሸጋገር የራሱ አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል ተብሏል፡፡
የጎሬ-ማሻ-ቴፒ የአስፓልት መንገድ ግንባታ በ2015 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ ታውቋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 11/2012
ዋለልኝ አየለ