የቤተመንግስትን የአንድነት ፓርክ ግንባታ ወቅት ያጋጠመንን አንድ ጉዳይ ላጫውታችሁ ብለው ይተርኩ ጀመር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ። በግቢው ከሚገኙ ዛፎች መካከል ሁለት የባህር ዛፎቹ ሌሎቹን ተክሎች ውሃ ይሻማሉ ተብሎ እንዲቆረጡ ተደረገ። በቀጣይ ጊዜያት ግን ሌሎቹም ዛፎች ደርቀው አገኘናቸው።
ጉዳዩን ከዕጽዋት ባለሙዎች ስንጠይቅ ግን የተባልነው ዛፎች በጋራ የመኖር ተፈጥሮ ስላላቸው ነው አንዱ ሲቆረጥ ሌላው የሚደርቀው። እናም አሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንኳን ሰው ዛፎችም በጋራ የመኖር ልምድ አላቸው ። ይህንን አውነተኛ ታሪክ ያነሱት ደግሞ ትላትና በሚሊኒም አዳራሽ በተካሄደው የባለሃቶች ሰላም ኮንፈረንስ ላይ ነው።
ዶክተር ዐብይ በዚሁ ኮንፈረንስ ላይ እንዳብራሩት እግርና እግር ቢጋጩ ግራ እግርን ቆርጠው እንደማይጥሉት ሁሉ አብረን ስንኖር የሚያጋጭ እና የሚያቃቅር ነገር ይኖራል። በቅራኔ ውስጥ ግን ከመነጋገር አልፎ ደም መፋሰስ ድረስ መሄዱ ተገቢ እንዳልሆነ ማሰብ ያስፈልጋል።
በተለይ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሰላምን መጠበቅ እንጂ ስለመገዳደል ማሰብ የለባቸውም። ኦሮሞና አማራም በጋራ የተፈጠሩት በጋራ እንዲለሙ እንጂ ከተለያዩ በቀላሉ እንደሚደኸዩ ማወቅ ይገባል። ሁል ጊዜ ብርሃን ሁልጊዜ ደግሞ ጨለማ ቢሆን እንደማያምር ሁሉ ኢትዮጵያንም በባህል፤በቋንቋ ፤በሃይማኖት መለያየታቸው ውበት ነው።
ኢኮኖሚም እንኳን ብዝሃነት ያለው ሲሆን ነው የሚዋጣው ያሉትዶክተር ዐብይ፣ ከዚህ መረዳት የሚቻለው ደግሞ የተለያየ ማንነት እና ቋንቋ ቢኖርም የሚዋጣው አብሮ መብላት እና ልብ ለልብ ተዋውቆ በሰላም መኖር መሆኑን ለባለሃብቶች አስረድተዋል። አብሮ የመኖርን ጥቅም መገንዘብ፣ የሌላውን እሴት ማወቅ፣ አብሮ በመሆን ሳይጠፋፉ መኖር ይቻላል የሚለውን መገንዘብ መሰረታዊ ጉዳዮች መሆቸውንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከፖለቲካም ከፖለቲከኞችም በላይ ናት ያሉት ደግሞ የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ናቸው። እንደእርሳቸው እናት ለልጆቿ ሁሌም ሙሉ እና በቂ እንደሆነች ሁሉ ኢትዮጵም ለልጆቿ ሁሌም በቂ እና ሙሉ ነች።
የሚጠበን የሚመስለን አብሮን የቆየው ደካማ የፖለቲካ ባህላችን ያመጣው ተጽዕኖ ስላለ ነው። እያንዳንዳችን የውስጥ ሰላማችንን ለመጠበቅ ካሰብን፣ ከአካባቢያችንና ከተፈጥሮአችን እንዲሁም ከፈጣሪያችን ጋር ያለንን ሰላም መጠበቅ ከቻልን ዘላቂ ሰላማችንን ማምጣት እንችላለን።
እንደ ወይዘሮ ሙፈሪት ከሆነ፣ ሰላም በውስጣችን የሚኖር ልንኮተኩተው እና ልናበለጽገው የሚገባ ፀጋ ነው። አሁን ላይ ካለፉት ወራት የተሻለ ሰላም ቢኖርም መዋቅራዊ ችግሮቻችንን በየደረጃው መፍታት ስንችል ደግሞ አንጻራዊ ብቻ ሳይሆን ዘላቂ ሰላማችንን የማናረጋግጥበት ምክንያት የለም።
በንግድ ማህበረሰቡ የተሰናዳውን የሰላም ኮንፈረንስ ያስተባበሩት ወይዘሮ ፍሬአለም ሽባባው በበኩላቸው፣ የንግድ ስራ ብሄር እና ሃይማኖት እንደሌለው ይናገራሉ። በመሆኑም ባለሃብቱ ለሁሉም የምትመች ኢትዮጵያ እንድትኖር አልሞ ከህጻን እስከአዋቂ፣ ከደሃው እስከባለሃብቱ በሰላም የሚኖርባት አገር ዕውን እንድትሆን ይሰራል ይላሉ። በጋራ ሰርተን በጋራ ለማደግ እና ሰላምን ለማረጋገጥ የሁሉም ዜጋ ጥረት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 11/2012
ጌትነት ተስፋማርያም