. በሙስና የተመዘበረ ከ50 ሚሊየን ብር በላይ ተመላሽ ተደርጓል
አዲስ አበባ፡- ባለፉት ሶስት ወራት በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎችና በፌዴራል ዪኒቨርሲቲዎች ማንነትንና ብሄርን መሰረት አድርገው ተቀስቅሰው በነበሩት ግጭቶች የተጠረጠሩ ከ250 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታወቀ። በሙስና የተመዘበረ ከሀምሳ ሚሊየን ብር በላይም ወደ መንግስት ካዝና ማስመለስ መቻሉን ተናግሯል።
የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ቱኑ ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተናገሩት በአንዳንድ አካባቢዎች ተቀስቅሰው በነበሩት ግጭቶች ኢሰብአዊ በሆነ መንገድ የሰው ህይወት ጠፍቷል። በርካታ ዜጎችም ከፍተኛና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል ፤ በግጭቱ የመንግስትና የግል ንብረት ለውድመት የተዳረገ ሲሆን ዝርፊያም ተፈጽሟል።
ጠቅላይ አቃቤ ህግ ከፌዴራል ፖሊስ ከክልል የጸጥታ ሀይልና ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር ወንጀለኞችን ለፍርድ ለማቅረብ እየሰራ ይገኛል። በዚህም በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን፣ አዳማ፣ በሰበታና በአዲስ አበባ ዙሪያ በተፈጸመው ወንጀል ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ 337 ሰዎች የተለዩ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 250ቱ በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ነው። በሌሉበት ክስ የተመሰረተባቸውም ያሉ ሲሆን በቁጥጥር ስር ለማዋል አስፈላጊው ክትትል እየተደረገባቸው ነው።
በተመሳሳይ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዲፈናቀሉ ብሎም ተረጋግተው እንዳይማሩ በጀት በመመደብ ሁከት ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ያስረዱት የኮሚኒኬሽን ኃላፊው በዚህም ከህይወት መጥፋት እስከ ንብረት መውደም የደረሱ ወንጀሎች የተፈጸሙ ሲሆን በወልድያ፤ በወሎና ደብረ ብርሀን ዩኒቨርሲቲዎች ከ16 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ተናግረዋል፡፡
ለውጡን ተከትሎ ጥቅማችን ይነካብናል ብለው ያሰቡና ከብጥብጡ ጥቅም ለማግኘት የሚፈልጉ ሆን ብለው ግጭት የሚጭሩ አካላት አሉ ያሉት ዳይሬክተሩ እነዚህን ለህግ ለማቅረብም እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል። ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ ወንጀሉ በቡድን መፈጸሙ፤ ፈጻሚዎች ብሄራቸው ውስጥ የመደበቅ፤ የመንግስት መዋቅር ያለበት ክፍተትና ህብረተሰቡ አሳልፎ ለመስጠት ማመንታት ማሳየቱ ለመዘግየቱ ምክንያት መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
ዳይሬክተሩ ጨምረው እንደተናገሩት ሙስናን ለመከላከልም በተሰራው ስራ ባለፉት አምስት ወራት ከሀምሳ ሚሊየን ብር በላይ በጥሬ ወደ መንግስት ካዝና እንዲገባ የተደረገ ሲሆን በኦዲት ግኝት መነሻነት ከ312 ሚሊየን ብር በላይም ከብክነትና ከሙስና ለመታደግ ተችሏል። በቀጣይም በፌዴራል የመንግስት መስሪያ ቤቶችና በመንግስት የልማት ድርጅቶች ከ300 ሚሊየን ብር በላይ ለማስመለስ የተጀመረ ስራ መኖሩንም ጠቁመዋል።
ከሀገር የሸሸ ገንዘብ ለማስመለስ በተሰራውም ስራ በየት ሀገር ምን ያህል ንብረት በማን እንደተቀመጠ የመለየት ስራ የተጠናቀቀ ሲሆን ከሀገራቱ ጋር በተደረገ ውይይትም የጋራ ስምምነት ላይ ተደርሷል። በቀጣይም ይህንን እንዲከታተል በተዋቀረው ዳይሬክቶሬት በኩል የማስመለሱ ስራ የሚሰራ ሲሆን ሀገራቱንና የሸሸውን የሀብት መጠን ለጥንቃቄ ሲባል ለግዜው መግለጽ አስፈላጊ አለመሆኑንም አስረድተዋል።
በህግ ማሻሻያም ረገድ የጥላቻ ንግግር፤ የሀሰተኛ መረጃና ህገወጥ ገንዘብ ዝውውርን ለመቆጣጠር እንዲሁም የፌዴራል ተቋማት የአስተዳደር ስነ ስርዓትን ህጋዊ ለማድረግ አዋጆች ተዘጋጅተው ለማጸደቅ በሂደት ላይ መሆኑን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 11/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ