ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የመሬት ምልከታ ሳተላይት ከቻይና ዋና ከተማ ቤይጂንግ 400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኘው የቻይና ሳተላይት ማስወንጨፊያ ጣቢያ ትናንት ጠዋት 12፡21 ደቂቃ ላይ ምድርን እየቃኘች እና በፎቶ እየመዘገበች መረጃ የምትሰበስበውና ‹‹ETRSS-1›› የሚል ስያሜ ያላት ሳተላይት መላኳ ይታወቃል።
ወደታሰበላት ምህዋርም በጥሩ ሁኔታ ደርሳለች። ሳተላይቷ ለግብርና፣ ለማዕድን፣ ለአካባቢ ጥበቃ እና ለመሳሰሉት አገልግሎት መረጃ መስጠት የምትችል መሆኑም ታውቋል። በዚህች ሳተላይት ማምጠቅና ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።
በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር እንዳወቅ ጸጋው እንደሚሉት፤ ሳተላይት ማምጠቅ ብዙ ትርጉም እንዳለውና በሳይንስና ቴክኖሎጂ ያደጉ አገራት የዕድገት ሚስጥርም መነሻው ይህ ነው። ይህ ጅምር ለኢትዮጵያ ዕድገት ትልቅ ትርጉም አለው ይላሉ።
በዜጎችና ምሁራን ዘንድም አዲስ ነገር ለመፍጠር ትልቅ መነሳሳት ይፈጥራል። ሳተላይቷ ለከተማ እና ገጠር መሬት አስተዳደር፣ ማህበራዊ ጉዳዮች፣ ህዝብ አሰፋፈር፣ ምርጫና ህዝብ ቆጠራ፣ ለማህበረሰብ ልማቶችና ተያያዥ ጉዳዮች መረጃ ለመሰብሰብ ትልቅ ድርሻ ይኖራታል።
በድንበር አካባቢ የሚስተዋሉ ተላላፊ ወንጀሎች፣ ህገ ወጥ የመሣሪያ ዝውውርና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል በአገሪቱ የሚከናወኑ ታላላቅ የልማት አውታሮችን ለመጠበቅና ከጥቃት ለመከላከልም አበርክቶው የጎላ ነው።
ማዕድናት፣ መሬት፣ ውሃና ሌሎች የተፈጥሮ ሃብቶች አጠቃቀም፣ የገጠርና የከተማ መሬት አያያዝና አጠቃቀምና ፍትሃዊ አሠራርን መሠረት ለማስያዝ ብሎም አዳዲስ ፖሊሲዎችን ለማርቀቅም ከሳተላይ የሚገኘው መረጃ የላቀ ሚና አለው።
እንደ ምሁሩ ገለፃ፤ አሁን ባለው ጅምር ኢትዮጵያ የስፔስ ህግ ወይንም በስፔስ አስተዳደር ስርዓት ውስጥ ትገባለች። ይህም በዓለም አቀፍ ህግ ላይ የመወሰንና የመደራደር ሚና ይኖራታል። ኢትዮጵያ የሌሎች አገራት መረጃ ስለሚኖራት በመተባበርና በመከባበር እንድትሠራ ያግዛታል።
ሉዓላዊ አገራትን መብት እንዳይጣስም ሌሎች አገራትም በኢትዮጵያ ጉዳይ እንዳይገቡ የመደራደር አቅም ለሚፈጥርላት ተሰሚነቷ ይጨምራል። በዓለም ፖለቲካም የላቀ ሥፍራ የሚሰጠው ሲሆን ተቀባይነቷም ብሎም ዓለም አቀፋዊ እይታን ለማግኘት ይጠቅማል የሚለው የረዳት ፕሮፌሰር እንዳወቅ ሃሳብ ነው።
ዕጩ ዶክተር ጌታቸው ተስፋዬ በእንጦጦ ኦብዘርቫቶሪ ማዕከል ተማሪ ሲሆኑ፤ ኢትዮጵያ ሳተላይት ማምጠቋ በቀላሉ የሚታይ አይደለም ባይ ናቸው። የአገሪቱን ምጣኔ ሃብት እንዲመነደግ በመረጃ የታገዙ ተግባራት የሚያስፈልጉ ሲሆን፤ ለዚህም በሳተላይት የታገዘ ትክክለኛ መረጃ ማግኘት በራሱ የላቀ ሚና አለው።
በግብናው ሴክተር የአፈር እርጥበት ለማወቅ፣ የድርቅ ተጋላጭነትና የጎርፍ ተጠቂነት መረጃ ለመሰብሰብ በሳተላይት መታገዝ ያስፈልጋል። ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ መረጃ ታገኝ የነበረው ከአውሮፓና አሜሪካ በሚገኙ ሳተላይቶች ነበር። በአሁኑ ወቅት የራሷን ሳተላይት መጠቀም ያስችላታል። የአገሪቱ የጀርባ አጥንት የሆነውን ግብርና ለማዘመንና ለማገዝ ፋይዳው ብዙ ነው።
የአገሪቱ ካዳስተርና መሬት ይዞታ በግራውንድ ሰርቬይ እየተሰራ ነው። ይህ ስራ በሰው አቅም ብቻ ሲሰራ በርካታ ጊዜ ከመውሰዱ ባሻገር ወጪውም ከፍተኛ ነው። ሳተላይ በመጠቀም ሲሠራ ግን በአየር ላይ መረጃ ሲሰበሰብ በአጭር ጊዜና በተወሰነ የሰው ኃይል ሊከናወን ይችላል።
በአሁኑ ወቅት የመጠቀችው ሳተላይት ሰፊ ሥራ የተሰራው በውጭ ባለሙያዎች ነው። ይህ በሂደት ተቀይሮ በኢትዮጵያ ሙሉ አቅም መሠራት አለበት። ለዚህም ዩኒቨርሲቲዎች የማስተርስና እና ዶክትሬት ተማሪዎቻቸው ልምድ ልውውጥና ጥናት እንዲያደርጉ ማገዝ ይገባል። ኢትዮጵም ለዘርፉ ከዚህ የላቀ ትኩረት መስጠት ይገባታል።
የሳተላይት ማምጠቂያ ስፍራዎች በዓለም ላይ የተወሰኑ አገራት ብቻ የሚገኝ ሲሆን፤ ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ከቻይና መምጠቋ ብዙም ችግር እንደሌለው በመጠቆም፤ ዋናው ሥራ ሳተላይትን የማሳደግና በራስ አቅም ሳተላይቷ ማምረት መሆን አለበት። በሂደት ግን ማምጠቂያ ስፍራ ያስፈልጋል።
ሳተላይትን በራስ አቅም እና ዜጋ ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር ሲቻል መረጃዎችን ለመሸጥና ለመለዋወጥ ብሎም ሚስጥራዊ መረጃዎችን በራስ አቅም ለመያዝ፤ ለመተንተንና ለሚፈለገው ዓላማ በተገቢ ጊዜ ለመጠቀም ሰፊ ዕድል ይሰጣል ባይ ናቸው። በሳተላይት ጥቅምና ተያያዥ ጉዳዮችን ሰፊ የግንዛቤ ስራ አለመሰራቱን ጠቁመው መገናኛ ብዙሃን በዚህ ላይ እንዲያተኩሩ ያሳስባሉ።
የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሽፈራ ፈይሳ፤ ኢትዮጵያ ሳተላይት ማምጠቋ ያላትን ሃብት ለመቆጣጠር፣ ማዕድናትን ያሉበትን ሥፍራ ለማወቅና መረጃ በአግባቡ ለመያዝ የሚያግዝ በመሆኑ የላቀ ሥፍራና ትርጉም ይሰጠዋል።
አገሪቱ ካላት የዕድገት ፍላጎት አኳያም የሳታላይት ቴክኖሎጂን ተግባራዊ ማድረጓ በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑንና እስካሁን ድረስ በመቆየቷም ብዙ ነገር አምልጧል፤ ሃብትም አጥታለች ባይ ናቸው።
ይህ ሳተላይት በአገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ ትልቅ ሚና እንዳለው የሚናገሩት ዶክተር ሽፈራ፤ የኢትዮጵያን ክብር በእጅ ከፍ የሚያደርግ ነው። በአሁኑ ወቅት ውድድሩ የቴክኖሎጂ በመሆኑ ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት በዘርፉ ላይ ሌሎች ምርምሮችንና ተያያዥ ተግባራትን ማከናወን እንደሚገባ ያሳስባሉ።
ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በተገኘው መረጃ 21 ኢትዮጵያውያን ኢንጅነሮችና ሳይንቲስቶች በፕሮጀክቱ የተሳተፉ ሲሆን ቻይና ውስጥ ባካበቱት እውቀት ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ሳተላይት ሠርተው ለማምጠቅ እቅድ አላቸው። ከዚህ በኋላ ያለው ሙሉ ክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም እንቅስቃሴዋን የመምራት ሥራ በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች እዚሁ በእንጦጦ ኦብዘርቫቶሪ ማዕከል የሚከናወን ይሆናል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 11/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር