ጎረቤቴ የአብራኩ ክፋይ የሆነው የ17 ዓመት ወንድ ልጁ ቁም ስቅሉን ያሳየዋል:: ቤታቸውንም ያምሰዋል ማለት ይቀላል:: አብረው የሚኖሩት የሰውዬው እናትና የልጁ አያት የሆኑት ሽማግሌም ያማርራሉ:: ልጃቸውንም ‹‹ጣትህን ቆርጠህ አትጥል እንግዲህ መቻሉን ይስጠኝ ብለህ መጸለይ ነው›› ሲሉ እንደ ማጽናናት ብለው ‹‹ ልጁ ምን ያርግህ ከአንተ እኩል ያወራል፣ ከአንተ ቀድሞ እፍታውን ይበላል፣ ፈሪሀ እግዚያብሔር እንዲኖረው እና ማፈርም ሆነ ማክበር እንዲለምድ በቤተ ቤተክርስቲያን አላሳደግከው›› በማለት ወቀሳ ያክሉለታል:: የዘመኑን ልጆችም ስነምግባር የሚጎድላቸው አድርገው በጅምላ ይወቅሳሉ::
እንዲህ አይነት ትችቶች በተደጋጋሚ የሚሰሙ የዘመኑ ጥያቄዎች ናቸው:: በተለይ የዘመኑ ትምህርት ግብረገብነትን ከማስረጽ አንፃር ፈዛዛ ነው የሚሉ ወገኖች የወጣቶችን ስነምግባርና የባህሎቻችንን መጣስ በዋቢነት ይጠቅሳሉ:: በሌላ በኩል የስነዜጋና ስነምግባር ትምህርት በየዘመኑ በተለያዩ ስያሜዎች ሲሰጥ እንደነበር ይታወቃል:: ለመሆኑ ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ተግባራዊ ሲደረግ የቆየው የስነዜጋና ስነምግባር ትምህርት ከዚህ አንጻር ምን ፋይዳ ነበረው? ያጋጠሙ ችግሮችና መፍትሄውስ? በሚለው ርዕሰጉዳይ ዙሪያ ጥናታዊ ስራዎችን መነሻ በማድረግ እንደሚከተለው አጠናቅረናል::
ስነ ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት ፋይዳ
‹‹በትምህርት ተቋማት የሥነዜጋና ሥነምግባር ግንባታና ዴሞክራሲያዊነት፣ ተግዳሮቶችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች›› በሚል ርዕሰ ጉዳይ የኢፌዴሪ የፖሊሲ ጥናት እና ምርምር ማዕከል እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ2009 ዓ.ም ለንባብ ያበቃው ጥናት እንዳመለከተው፤ የዜጎች የመልካም ዜግነት ባህሪያት፣ ክህሎት እና እውቀት መታነጽ ለአንድ አገር ሁለንተናዊ እድገትና መሻሻል ዋናው ጉዳይ ነው:: በዚህ መነሻነት የኢፌዴሪ መንግስት በሁሉም የትምህርት ደረጃዎች የስነዜጋና ሥነምግባር ትምህርት ስርዓተ ትምህርት ተቀርጾ ለዜጎች መሰጠት ከጀመረ በርካታ ዓመታት አሰቆጥሯል:: ይህ ደግሞ ዜጎች የስነዜጋ እውቀታቸው ከፍ እንዲል አስችሏል:: ጠያቂና ለመብታቸው የሚሟገቱ፣ ዋና ዋና ሕገመንግስታዊ ጉዳዮችን እና ብዝሃነትን የተረዱ ዜጎችንም ማፍራት ተችሏል::
የሥነ ዜጋና ሥነምግባር ትምህርት አስፈላጊነት መነሻው የዜጎችን የዜግነት እውቀት፣ክህሎት፣ዴሞክራሲያዊ አመለካከትና ባህሪ፣ መልካም ስነምግባር በመገንባት ለራሳቸው፣ለማህበረሰባቸው እና ለአገራቸው አስተዋጽኦ በማበርከት የአገራቸውን ልማትና ዴሞክራሲ ወደላቀ ደረጃ ማሸጋገር እንዲችሉ ስለመሆኑም ጥናታዊ ጽሑፉ በዝርዝር አስቀምጧል::
እ.ኤ.አ. በ2018 ዓ.ም በአለም አቀፍ ተግባር ተኮር ትምህርታዊ መጽሔት (Journal of Education and practice) ላይ ‹‹የሥነዜጋና ሥነምግባር ትምህርት ተግዳሮቶች በኢትዮጵያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች›› በሚል ርዕስ የአርሲ ዩኒቨርሲቲው ጎሳ ሰጡ ታፈሰ( ረዳት ፕሮፌሰር) ለንባብ ባበቁት ጥናታዊ ምርምር እንደተመላከተው፤ የሥነዜጋና ምግባር ትምህርት በትምህርት ቤቶች ሲሰጥ ኃላፊነት የሚሰማቸውና ሰናይ ምግባርን የተላበሱ ዜጎች ያፈራል የሚል እምነት ተጥሎበት እንደነበረ ጠቅሰው በዚያ ደረጃ ውጤታማ አለመሆኑን ያስረዳል::
የሚስተዋሉ ችግሮች/ እንደ እንከን ከሚነሱት
የኢፌዴሪ የፖሊሲ ጥናት እና ምርምር ማዕከል ጥናት ውጤትም የሥነዜጋና ስነምግባር ትምህርት በርካታ ሊቀረፉ የሚገባቸው እጥረቶች እንዳሉበት በግልፅ አመላክቷል:: ጥናታዊ ጽሁፉ በችግርነት ከሚያነሳቸው ጉዳዮች መካከል ከይዘትና አቀራረብ አንጻር ትምህርቱ ሊያሳካ የሚገባቸውን ወይም ደግሞ የተፈለገውን ዓላማ ማሳካት የሚችል እንዳልሆነ መለየት ችሏል:: በመሆኑም በሁሉም የትምህርት ደረጃዎች ተማሪዎች በመማሪያነት የሚጠቀሙባቸው መጽሐፍት በይዘታቸው ወደ ሥነዜጋ ያጋደሉ መሆናቸውን በመግለጽ ለሥነምግባር ትምህርት የተሰጠው ትኩረትና ሽፋን ከሚገመተው በላይ ያነሰና ሥነምግባርን ከማስረጽ አንጻር ዋና ተግዳሮት መሆኑ ተጠቅሷል::
ከአምስተኛ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ያሉ የመማሪያ መጽሐፍት ተመሳሳይና ድግግሞሽ እንደሆኑ የሚያነሳው የማዕከሉ ጥናት፣ በመሆኑም ተማሪዎቹ ትኩረት ሰጥተው እንዳይማሩና መምህራኑም በተነሳሽነትና በትጋት እንዳያስተምሩ አድርጓቸዋል ይላል:: የሥነምግባርና የዜግነት ግንባታ ጉዳይን ታሳቢ ያላደረገና አብዛኛዎቹ መምህራንም ትምህርቱን በዚያ ደረጃ እንደማይገነዘቡት በጥናቱ መረጋገጡን ያትታል::
በመምህራን ትምህርት ማሰልጠኛ ተቋማት የሚሰጠው የሥነዜጋና ሥነምግባር ትምህርት ወጥነት እንደሌለው የሚያነሳው ጥናቱ፤ አንዳንዶቹም ሕገመንግስትና ሕገመንግስታዊ ጉዳዮችን አለማካተታቸውን በመግለጽ በሥነዜጋና ሥነምግባር አስተማሪነት የሚያስመርቋቸው ተማሪዎች የሕገ መንግስቱን መርሆች እንኳን ማስተማር የማይችሉ ይሆናሉ ሲል የችግሩን ምንጭ አመላክቷል::
አንዳንድ የሥነ ዜጋና ሥነምግባር ትምህርት መምህራን በስርዓተ ትምህርቱ ላይ ያለውን ይዘት በመተው የራሳቸውን ፖለቲካዊ አመለካከትና ፍልስፍና በተማሪዎች ላይ ለመጫን እንደሚሰሩ ያመላከተው ጥናቱ ተማሪዎች ትምህርቱን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት ማሳለጫ አድርገው ከመቀበል ይልቅ በሌላ መንገድ በመረዳት ለትምህርቱ የተዛባ አመለካከት እንዲይዙ አድርጓል ይላል:: በእነዚህና በሌሎች በርካታ ምክንያቶች የተነሳ የሥነዜጋና ሥነምግባር ትምህርት ዜጎችን በአመለካከትና በተግባር አገር ወዳድና ተቆርቋሪ እንዳይሆኑ በማድረግ የራሱን አሉታዊ ሚና እንዳሳደረ የማዕከሉ ጥናታዊ ጽሑፍ ያብራራል::
በደብረ ማርቆስ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ የሥነዜጋና ሥነምግባር ትምህርት መምህሩ አቶ አበበ አወቀ እንደሚሉት፤የሥነዜጋና ስነምግባር ትምህርት በሚፈለገው መንገድ አልተመራም:: ዜጎች በተገቢው ታንጸው እንዲያድጉ ሰፊ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ጠቁመው፤ ይህ ሲሆን አልነበረም ብለዋል:: ማሳያው ደግሞ በቴክኒክና ሙያ ትምህርት ተቋማት ይሰጥ የነበረው የሥነዜጋና ሥነምግባር ትምህርት እንዲቋረጥ ተደርጓል:: በሁለተኛና በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም የአገር ፍቅር ስሜትን በሚያሳድግ መንገድ እየተሰጠ እንዳልሆነ ተናግረዋል::
ረዳት ፕሮፌሰር ጎሳ ሰጡ ታፈሰ ጥናታዊ ጽሁፉ እንደሚለው፤ በኢትዮጵያ በየትኛውም የትምህርት እርከን የሥነዜጋና ሥነምግባር ትምህርት የሚሰጥ ቢሆንም በተለይ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከሚስተዋሉት ችግሮች መካከል የማስተማር ስነዘዴ ክፍተቶች፣ የሙያው ምሩቃን እጥረቶች፣ ተማሪዎቹ ተገቢውን ክህሎት ስለመጨበጣቸው ትኩረት አለመስጠት፣ በትምህርት ቤቶች በመማር ማስተማሩ ሂደት ዴሞክራሲያዊ ድርጊቶችን በተግባር ማድረግ አለመቻል፣ የማስተማር ስነ ዘዴው አለመሻሻል፣ የመርጃ መሳሪያዎች እጥረት፣ ተማሪዎች የተማሩትን በተግባር ማድረግ የሚችሉበት እድል አለመኖር እና የትምህርቱ ይዘቶች ስነዜጋና ስነ ምግባር አለመጣጣም፣ በተለያዩ የክፍል ደረጃዎች ይዘቶች መደጋገም የሚሉት ተዘርዝረዋል::
በዚህ የተነሳም ተማሪዎቹ በሚፈለገው ደረጃ በሥነ ምግባር የታነጹ እንዲሆኑ በማድረግ በኩልና የላቀ ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎን በብቃት ተላብሰው ተግባራዊ ማድረግ አለመቻላቸውን ያስረዳል:: በተማሪዎቹ ባህሪም ሆነ ድርጊት ላይ የሰረጸ ለውጥ ከማምጣት ይልቅ የለብለብ በመሆኑ በራስ መተማመናቸውን ያሳጣል:: ተማሪዎች መብትና ግዴታቸውን በተገቢው አውቀው መቼ ምን መተግበር እንዳለባቸው የሚያሳውቅ ሳይሆን ግርታን የሚፈጥር እንደሚሆን የጎሳ ሰጡ(ረዳት ፕሮፌሰር)ጥናት ያትታል::
በመፍትሔነት
የኢፌዴሪ ጥናትና ምርምር ማዕከል ጥናታዊ ጽሁፍ እንደጠቆመው፤ የአንድ አገር ትምህርት ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርት ጎን ለጎን ዜጎች የማህበረሰባቸውን እና የዴሞክራሲ እሴቶችን እንዲረዱ፣በማህበረሰባቸው ውስጥ ስለሚኖራቸው ሚናና ሚናቸውን በአግባቡ መወጣት የሚያስችላቸው ክህሎት እንዲያገኙ እና አገር ወዳድ እንዲሆኑ የሚያስችል መሆን እንዳለበት በመፍትሄነት አንስቷል::
ከዚህ በተጨማሪ ሥርዓተ ትምህርቶቹና ትምህርት ቤቶች በየወቅቱ ስለሚቀያየሩ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እውነታዎች ተገቢውን ግንዛቤ የሚያስጨብጡና ለለውጡ የተዘጋጁ ዜጎችን የማፍራ ሀላፊነት እንዳለባቸውም አመላክቷል:: የመምህራን ስልጠና እና የትምህርት ዝግጅት፣ የማስተማሪያ ግብዓቶች ጥራትና ብዛት፣ የመምህራኑን እና የተማሪዎችን ችግር ሊፈታ የሚችል ሙያዊና አስተዳደራዊ ስርዓት ትኩረት ሊደረግባቸው እንደሚገባ አመላክቷል::
አዲስ ዘመን አርብ ታህሳስ 10/2012
ሙሐመድ ሁሴን