የፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ ደጋፊዎች ከሁለት ጊዜ የመሪነት ዘመን በላይ ዕድል የማይሰጠው የሀገሪቱ ህገ መንግስት አንቀጽ 140 እንዲሻሻል መጠየቃቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ የፕሬዚዳንቱ የሥልጣን ዘመን የሚያበቃው በ2022 ቢሆንም ደጋፊዎቻቸው ግን ከወዲሁ አል ሲሲን በስልጣን ለማሰንበት መላ እያፈላለጉ ነው፡፡
የቀድሞው ወታደራዊ አዛዥ አል ሲሲ ደጋፊዎች በአገሪቱ ለሚታተመው አል አክበር ለተባለው ዕለታዊ ጋዜጣ እንደተናገሩት በአዲሱ የአውሮፓውያን ዘመን አል ሲሲን በስልጣን ለማቆየት ይሻሻላል ብለው ተስፋ የተጣሉበት ህግ እውን እንደሚሆን ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም አንድ ፕሬዚዳንት በአራት በአራት ዓመት ቆይታ ከሁለት ጊዜ በላይ መመረጥ አይችልም የሚለውን ህግ ፓርላማው እንዲሽረው የተለያዩ ግፊቶችን እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
ሮይተርስ በወርሃ ነሐሴ 2018 ባሰራጨው ዘገባ አንዳንድ የመንግሥት ሠራተኞችና ደጋፊዎቻቸው ሲሲ በቀጣይ የምርጫ ዘመን እንዳይወዳደሩ የሚደነግገው ህገ-መንግሥት እንዲሻሻል የሚጠይቅ ጽሁፍ በማዘጋጀት የድጋፍ ድምጽ የማሰባሰብ ሥራ እየሠሩ መሆኑ ታውቋል፡፡ ምን ያህል ሰው እንደተፈራረመና በምን ያህል ደረጃ በአገሪቱ እንደተሰራጨ ባይታወቅም በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 140 ላይ የተቀመጠው ድንጋጌ እንዲቀየር የሚደረገው ዘመቻ ግን እንደቀጠለ ነው፡፡
የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና የሙርሲ ደጋፊዎች ግን ይህን እንቅስቃሴ የሚከታተሉት በጥርጣሬ ነው፡፡ እንደውም ከነዚህ እንቅስቃሴዎች ጀርባ የመንግሥት እጅ እንዳለበት ያምናሉ፡፡ ‹‹የዘፈን ዳርዳሩ እስክስታ ነው›› እንዲሉ ሲሲ ፍላጎታቸውን በደጋፊዎቻቸው አማካኝነት እየገለጹ እንዳሉ እየተናገሩ ናቸው፡፡ ቅሬታቸውንም በማህበራዊ ሚዲያዎች እያሰሙ ይገኛሉ፡፡
ፕሬዚዳንት አል ሲሲ ዳግም ከመመረጣቸው በፊት በህዳር 2017 ከአሜሪካው የዜና መረብ ሲኤንቢሲ (CNBC) ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ለሦስተኛ ጊዜ መመረጥ እንደማይፈልጉ አሳውቀው ነበር፡፡ ይሁንና የምርጫው ውጤት ከተሰማ ከመጋቢት 2018 በኋላ ግን ሁኔታዎች መልካቸውን የቀየሩ ይመስላል፡፡ ምንም እንኳን በአንደበታቸው በስልጣን መቆየት እንደሚፈልጉ ባይናገሩም የደጋፊዎቻቸውን በስልጣን ይቆዩልን ጥያቄ አልቀበልም ሲሉ ግን አልተሰሙም፡፡
የአል አክበር ጋዜጣ ዋና ዳይሬክተር ያስር ሪዝኪ በአምዳቸው ላይ እንዳሰፈሩት አል ሲሲ ወደ ሥልጣን ከመጡ ከአምስት ዓመታት በኋላ አብዛኛው የሀገሪቱ የደህንነት ሁኔታ ፣ ምጣኔ ሀብትና የህብረተሰቡ አኗኗር መሻሻል እንደታየበት አትተዋል፡፡ አብዛኛዎች የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ግን በዚህ ሃሳብ አይስማሙም፡፡
በካይሮ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር የሆኑት ሙስጠፋ ከማል አል ሰይድ እንደሚሉት ‹‹ሪዝኪ በጋዜጣው ላይ የተነተነው ግላዊ እሳቤውን ነው ብዬ አላምንም፡፡ እርሱ ሊያንጸባርቅ የሞከረው በመንግሥት ተቋማትና በደጋፊዎች ውስጥ ያለውን አመለካከት ነው፡፡ ያም ሆነ ይህ ሲሲ በሕይወት እስካለ ድረስ ከስልጣን መልቀቅ አይፈልግም፤ ምክንያቱም ሥልጣኑን የሚለቅ ከሆነ ተጠያቂ እሆናለሁ የሚል ፍራቻ ስላለው ነው›› በማለት የሪዝኪን ሃሳብ አጣጥለውታል፡፡
ሲሲ በ2013 ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው አስቀድሞ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት የነበሩት ሞሀመድ ሙርሲ የመጀመሪያውን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አሸንፈው መንበረ ሥልጣን ቢይዙም በግብጽ እስላማዊ ጽንፈኝነትና ሁከት እየገነነ በመምጣቱ በመፈንቅለ መንግሥት ከስልጣናቸው ተነስተው ዘብጥያ መወርወራቸው ይታወሳል፡፡
በዚህም የተነሳ የሙስሊም ወንድማማቾች ህብረት ደጋፊዎች በሲሲ አስተዳደር ላይ ጥርሳቸውን በመንከስ የተለያዩ ጥቃቶችን ሲሰነዝሩ ከርመዋል፡፡ በሀገሪቱ የሚገኙ አንዳንድ የመብት ተሟጋቾችና ፓርቲዎችም እንዲሁ የሲሲን መንግሥት ከመተቸት አልቦዘኑም፡፡
የሲሲ መንግሥት በሲና በረሀ መሽገው እያደፈጡ ጥቃት በሚሰነዝሩ ጽንፈኛ ቡድኖች ላይ ተደጋጋሚ እርምጃ በመውሰድ ለመደምሰስ ቢሞክርም ዛሬም ድረስ በደቡባዊው የሀገሪቱ ክፍል ስጋት መሆናቸው አልቀረም፡፡ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ እንኳን በጉብኝት ላይ ባሉ የቬትናም ዜጎች ላይ ጥቃት በማድረስ አራት ንጹሃንን በመግደል ከአሥር በላይ የሚሆኑትን አቁስለዋል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ መጥፎ ክስተት በግብጽ የቱሪስት ኢንዱስትሪ ላይ አደገኛ ተጽዕኖ የሚያሳድር መሆኑንም ልብ ይሏል፡፡
ሲሲ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ እነዚህን መሰል ፈታኝ ችግሮች ቢገጥሟቸውም መንግሥታቸው ለህዝቡ ኢኮኖሚያዊ ድጎማ በማድረግም ሆነ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራ በማስቻል ይበል የሚያሰኝ ሥራ መሥራቱ ይነገራል፡፡
ከመንግሥት ጋር ጥብቅ ቁርኝት አለው የሚባለው የዋፍድ /WAFD/ ፓርቲና የፓርላማው አባል የሆኑት ሞሀመድ ፎአድ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደገለጹት፤ ሰሞኑን አብዛኛዎቹ ግብጻውያን ሪዝኪ በአል አክበር ጋዜጣ ላይ ስለ ሲሲ በጎ በጎ ነገር የጻፉትን ሀተታ ደግፈው በማስተጋባት ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህም አል ሲሲ በአብዛኛው ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዳላቸው ማሳያ ነው ይላሉ፡፡
እንደ ፎአድ አባባል አሁን በግብጽ እየታየ ያለው የፖለቲካ መረጋጋትና የህዝቡም እፎይታ ሲታይ አል ሲሲ ለሦስተኛ ጊዜ ይመረጡ የሚለው የፓርላማ ሰዎች ሀሳብ እምብዛም አስገራሚ ላይሆን ይችላል፡፡ ህዝቡም ቢሆን የሲሲ የሥልጣን ዘመን እንዲራዘም የፈለገበት ምክንያት በቀጣዩ ምርጫ የሚመረጠው ሰው እንደ አል ሲሲ ግብጽን ከህዝባዊ አመጽ አላቆና ከጽንፈኞች ሴራ ጠብቆ መምራት አይችልም የሚል ስጋት በመያዝ ነው፡፡
የግብጽን ፖለቲካዊ ሁኔታ የሚከታተሉ ነዋሪነታቸው በለንደን የሆነ ንጉሳውያን ቤተሰቦችና ታዋቂ ሰዎች እንደሚሉት ደግሞ ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው ፓርላማው ህገ መንግሥቱን ለመቀየር መዘጋጀቱን የሚያመላክቱ ነገሮች እየተስተዋሉ ነው ይላሉ፡፡ ሁኔታዎች ሲታዩ በእርግጥም የሲሲ በሥልጣን መቆየት አስፈላጊ ሊሆን ይችላል የሚል አስተያየትም ሰጥተዋል፡፡
ቀደም ሲል ከአል-ሲሲ ጋር ለፕሬዚዳንትነት የተወዳደሩት የተፎካካሪ ፓርቲ አባል ሀመዲን ሳባሂ እንደሚሉት፤ ፓርላማው ይህንን ህገ መንግሥት በሚፈልገው መንገድ ሊያሻሽል ቢሞክር ትልቅ ተቃውሞ ሊነሳ እንደሚችል አሳስበዋል፡፡
ግብጽ ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት በተቀሰቀሰው ህዝባዊ አመጽ ለወራት በቆየ ቀውስ ውስጥ እንደነበረች የሚታወስ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 25/2011
ኢያሱ መሰለ