በምንገኝበት 21ኛው ክፍለዘመን ቴክኖሎጂ የህልውና ጉዳይ ነው። እያንዳንዱ አገር ቴክኖሎጂን አንድም በማልማት አልያም በመከራየት ለህልውናው ይገለገልበታል። ኢትዮጵያም በተለያዩ ስራዎቿ ውስጥ የቴክኖሎጂ ተጽዕኖ ውስጥ ብትሆንም አብዛኞቹ ቴክኖሎጂዎች ከውጭው ዓለም የተቀዱና አንዳንዶቹም በኪራይ የምንገለገልባቸው ናቸው። ከነዚህ ቴክኖሎጂዎች ውስጥ ደግሞ የሳተላይት ቴክኖሎጂ ተጠቃሽ ነው።
ይህ የሳተላይት ቴክኖሎጂ ግን በኢትዮጵያ እጅ ሊገባ ከጫፍ ደርሷል። ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ከቻይና ጋር በተደረሰው ስምምነት መሰረት የሳተላይት ቴክኖሎጂን ተግባራዊ ለማድረግ የጀመረችው ውጥን ተጠናቆ እነሆ ዛሬ ፍሬ አፍርቷል።
ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሳተላይት ማምጠቅ መቻሏ በቴክኖሎጂው ዘርፍ እያሳየች ያለውን ለውጥ የሚያሳይ ነው። በሳተላይት መገንባቱ ሂደት 22 የዘርፉ ኢንጅነሮች ከቻይና ባለሙያዎች ጋር አብረው የተሳተፉ ሲሆን ይህ የቴክኖሎጂ ሽግግርም ኢትዮጵያ በራሷ አቅም ሳተላይት ለመገንባት ያስችላታል ሲል የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገልጿል። ኢትዮጵያ ሳተላይት ማምጠቋ ጥራት ያለው የአየር ሁኔታ መረጃ ለማግኘት፣ የማዕድን ሀብትን ለማወቅና ለመጠቀም የሚያስችል መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ይገልጻሉ።
በዓለም ላይ ወደ ህዋ የመጠቁ ከአምስት ሺህ በላይ የሚሆኑ የተለያዩ አይነት ሳተላይቶች እንዳሉ የሚገልጹት የኢንተርናሽናል አይሲቲ ሶሊሽን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጋሻው ሽባባው፤ ከእነዚህ መካከል የኮሙኒኬሽን፣ የወታደራዊ፣ የተፈጥሮ ሀብትን ለማወቅና ለመጠቀም የሚያስችሉ መረጃዎችን የሚሰበስቡ ሳተላይቶች ተጠቃሽ ናቸው ይላሉ።
ኢትዮጵያ የምታመጥቀው ሳተላይት የመሬት ምልከታ (ሪሞት ሴንሲንግ) ሳተላይት ሲሆን ይህም ለተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ፣ለደን ልማት፣ ለግብርና ለማዕድን ፍለጋ የሚያገለግሉ መረጃዎችን ለመላ እንደሚያገለግልም ገልፀዋል። በቀጣይም ወደ ሌሎች የሳተላይት አይነቶች ማምጠቅ ላይ ማተኮር እንደሚጠበቅባት ጠቁመዋል።
በታዳጊ ሀገራት የሳተላይት ቴክኖሎጂ ፈጽሞ የማይታሰብ ሆኖ ቢቆጠርም፤ ከሚሰጠው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አንጻር ለበለጸጉ አገራት ብቻ ሳይሆን ታዳጊ አገራትም ሊኖራቸው የሚገባ መሳሪያ መሆኑን ይናገራሉ።
“በአሁኑ ዘመን ሳተላይቶች ልክ እንደ የዓይን ብሌን ናቸው” የሚሉት አቶ ጋሻው ኢትዮጵያ የምታመጥቃት ሳተላይት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ያሉትን እንደ ነዳጅ፣ ወርቅ፣ አልማዝና የመሳሰሉ ማዕድናትን በተመለከተ መረጃ ለማወቅ፣ ለመጠቀምና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ መረጃዎችን ሰብስባ የምትልክ በመሆኑ ጉልህ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አመልክተዋል። ይህም የተፈጥሮ ሀብትን በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋልና ውሳኔ በመስጠት ከድህነት ለማውጣት ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን ነው ያብራሩት።
ሳተላይት በአገር ደረጃ የማምጥቅ አቅም መፍጠራችን ትልቅ ጉዳይ እንደሆነ የሚገልጹት የብሄራዊ ሜቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አህመዲን አብዱልከሪም፤ ከሳተላይት ብዙ ጥቅሞች እንደሚገኝም ይገልፃሉ።
ለምሳሌ ያደጉ አገራት የሚያመጥቋቸው ሳተላይቶች አሉ። ኢትዮጵያ እስካሁን ሳተላይት የማምጠቅ ደረጃ ላይ ባለመድረሷ ከሌሎች አገራት ነው የአየር ሁኔታ መረጃ የምትወስደው። አሁን በአገር ደረጃ ሳተላይት ማምጠቃችን የአየር ሁኔታ መረጃ ለማግኘትና የመረጃውን ጥራት ለማረጋገጥ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።
እንደ አገር የዓለም የሜቲዎሮሎጂ አባል እንደመሆናችን የአባልነት ክፍያ እንከፍላለን እንጂ መረጃውን ስንለዋወጥ የምንከፍለው ክፍያ የለም የሚሉት አቶ አህምዲን የአየር ሁኔታ በድንበር የሚወሰን ባለመሆኑ ኢትዮጵያ የአየር ሁኔታ ትንበያ ለመስጠት የምትጠቀመው የአውሮፓ ሳተላይትና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ያሉ የአየር ሁኔታ መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች የሚገኙትን መረጃዎች በማጣመር እንደሆነ ነግረውናል ።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ ሳተላይት እንደ አገር መኖሩ በኢትዮጵያ ብቻ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ስለሚሆን የመረጃው ጥራት ይጨምራል። ይህም የአየር ሁኔታ ትንበያ ለመስጠት የሚያስችል አስተማማኝ መረጃ ለማግኝት ያስችላል። ለኤጀንሲውም ትልቅ አቅም ይፈጥራል። የአየር ትንበያውን ተዓማኒነት ያሳድጋል።
በአፍሪካ ስምንት አገራት ሳተላይታቸውን ወደ ህዋ አምጥቀዋል። ኢትዮጵያም ከነዚህ አገራት ተርታ የተቀላቀለች ሲሆን ለዚህም ከስምንት ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ አድርጋለች። ሳተላይቷ ሰብስባ የምትልካቸውን መረጃዎች በእንጦጦ የምርምር ማእከል በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ተተንትኖ ለተለያዩ የመንግስት ተቋማት የሚላክ መሆኑም ታውቋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 10/2012
ጌትነት ምህረቴ