• ከ30 ሺ በላይ የሚሆኑት ተጨማሪ የገቢ ማስገኛ ፈጥረዋል
አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ ከተማ በዓለም ባንክና በመንግስት ቅንጅታዊ ድጋፍ 415ሺህ 923 የልማታዊ ሴፍትኔት ተጠቃሚ እማዎራዎችና አባዎራዎች 323 ሚሊዮን 815 ሺህ 420 ብር መቆጠባቸውን የምግብ ዋስትናና ልማታዊ ሴፍትኔት ጽሕፈት ቤት ገለጸ:: ከ30 ሺህ በላይ ተጠቃሚዎችም ተጨማሪ የገቢ ማስገኛ መፍጠራቸው ታውቋል፡፡
የከተማ ምግብ ዋስትናና ኑሮ ማሻሻያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰብሃዲን ሱልጣን በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳሉት፤ ባለፉት ሶስት ዓመታት በአዲስ አበባ በ121 ወረዳዎች እና በ781 ቀጠናዎች በሶስት ዙሮች የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ተግባራዊ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
በነዚህ ፕሮግራሞችም በመጀመሪያው ዙር በ35 ወረዳዎች፣ በ227 ቀጠናዎች፣ 123 ሺህ 918 ተጠቃሚዎች፣ በሁለተኛው ዓመት በ55 ወረዳዎች፣ 386 ቀጠናዎች፣ 200 ሺህ ተጠቃሚዎች እና በሶስተኛ ዙር ደግሞ በ26 ወረዳዎች፣ 169 ቀጠናዎች፣ 92 ሺህ 05 ሰዎች ተጠቃሚዎች እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡
ድጋፉ የሚደረገው በሁለት መንገድ መሆኑን የሚናገሩት ዳይሬክተሩ በማህበረሰብ አቀፍ ልማት 349ሺህ 375 እንዲሁም በቀጥታ ድጋፍ ደግሞ 66ሺህ 548 አባዎራዎችና እማዎራዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ከ30ሺህ በላይ የሚሆኑት እማወራዎች እና አባወራዎች ተጨማሪ የገቢ ማስገኛ መፍጠራቸውንም አቶ ሰብሃዲን ገልጸዋል፡፡ ከነዚህም መካከል አንዷ የሆነችው ወይዘሮ ፈቲያ ጩመቱ አሊ እንደምትለው በዚህ ፕሮግራም በመሳተፏ የቁጠባ ባህሏ እየተሻሻለ እና እያደገ እንደመጣ ትናገራለች፡፡
በመሆኑም አሁን ላይ በዶሮ ማርባት፣ በሰፈር ሸቀጣሸቀጥ ሱቅ እና አልፎ አልፎም በሻይ ቡና ንግድ በመሰማራት አራት መቶ ሺህ ብር ቆጥባ በአሸዋ ሜዳ አካባቢ ቤት መግዛት መቻሏን ትገልፃለች፡፡ በተጨማሪም በወር 1600 ብር እየከፈለች ልጆቿን በማስተማር ላይ እንደሆነችም ጠቁማለች፡፡
አቶ ተሾመ ደምሴ በበኩላቸው ለበርካታ ጊዜ በሕገወጥ መንገድ ከአገር ለመውጣት ጥረት በማድረግ በሕይወታቸው ያልከፈሉት መከራ እንደሌለ ገልጸው አሁን ግን ሕይወታቸውን በጥሩ ሁኔታ መምራት መቻላቸውን ይናገራሉ፡፡ የሁለት ልጆች አባት የሆኑት አቶ ተሾመ በሻይ ቡና እና በመኪና ጥበቃ ሥራ (ፓርኪንግ) ላይ ተሰማርተዋል፡፡ በመሆኑም የቤተሰባቸውን ወጪ ከመሸፈናቸውም አልፎ በሴፍቲኔት ከሚቆጥቡት በተጨማሪ 80 ሺህ ብር በባንክ መቆጠባቸውን ተናግረዋል፡፡ የሰው ልጅ በሕይወቱ ተስፋ ካልቆረጠ የፈለገበት ቦታ መድረስ እንደሚችልም ከእኔ ሕይወት ወጣቶች ትምህርት ሊቀስሙ ይገባቸዋል ሲሉ መክረዋል::
አቶ መሐመድ አሊ ሌላው ከሴፍትኔት ተጠቃሚነት ባለፈ በሌሎች የገቢ ማስገኛ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ናቸው:: አዲስ አበባ በተለምዶ እሪ በከንቱ በሚባለው አካባቢ በወንዝ ዳርቻዎች አትክልቶችን በማምረት ይተዳደሩ እንደነበረ የሚገልጹት አቶ መሐመድ አሁን ላይ አካባቢው በመልሶ ማልማት ቢፈርስም ሥራ ፈትተው መቀመጥን አልመረጡም፡፡
በመሆኑም ሸቀጣሸቀጥ በመሸጥ ስድስት ልጆቻቸውን በተገቢው ሁኔታ በማሳደግ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ተደራጅቶ በመስራት ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል አምናለሁ የሚሉት አቶ መሐመድ አሁንም ተደራጅተን በመቆጠብ ላይ ስንሆን ከ30 ሺ ብር በላይ ተሰብስቦ በእኔ እጅ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
በልማታዊ ሴፍትኔት የታቀፉት የማህበረሰብ ክፍሎች በአምስት የሥራ አይነቶች የመሳተፍ እድሎች እንዳሏቸው የሚገልጹት ዳይሬክተሩ፤ በደረቅ ቆሻሻ፣ በተፋሰስ፣ በመሰረተ ልማት እና በከተማ ግብርና ከምረቃ በኋላ በዘላቂነት እንደሚሰማሩ ገልጸዋል፡፡
አቶ ሰብሃዲን ሱልጣን አያይዘው እንዳነሱት፤ ዓላማው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙና ምንም የገቢ ምንጭ ያልነበራቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች በዘላቂነት እንዲሻሻሉ መንገድ ማሳየት፣ የቁጠባ ባህላቸውን እንዲያሳድጉ ማድረግና የሥራ ባህላቸውን መለወጥ እንደሆነ ጠቅሰው ፣ በርካታ ለውጦች በመታየታቸው ዓላማው ግቡን መትቷል ማለት እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 10/2012
ሙሐመድ ሁሴን