በመንደሩ ብዙ ታዋቂ ሰዎች አሉ:: መገናኛቸው ሰፊ ነው:: በዝክር፣ በአርባ ፣በድግስ በሰርግ፣ በልደት ወዘተ:: ወጋቸው ይደራል:: በተለያየ ዘርፍ ባለሙያዎች አሉ:: ሲደብራቸው እንዴት ነህ እግዜሩ የሚሉም ፈላስፎች አሉበት:: እነሱ ለሕይወት ቅመማ ቅመም ናቸው:: ያጣፍጡልሃል:: እኔ ጥያቄዬ ለእግዜሩ ነው:: እንደው ምን ስትል ፈጠርካቸው አንተዬ ብለው አያገባህም እንደው ሰው በምን ይደበር በምን ያልቅስ በምን ይጩህ በምን ይንከትከት በምን ይትከን ያለኝ መሰለኝ በጆሮዬ:: የባሰ አታምጣ ::ለካስ አንተም የባሰብህ ነህና በል በል ተወኝማ ብዬ በዚያ ቅጥ አምባሩ በጠፋ የመንደር መንገድ ቆዝሜ መራመድ ቀጠልኩ::
ብርቱ የማሪቱ ሽታ ያንን ጥርጊያ የአፈር መንገዱንና ሰፈሩን ያምሰዋል:: በነፋስ እየተሞላ ሽው ይላል:: አንድ አዛውንት ከዘራቸውን ይዘው ወገባቸው ጎብደድ ብሎአል በቀስታ እየተራመዱ ከበራፉ ሰደርሱ አየሁ:: የማያባራ ጫጫታ:: ሁካታ:: ህብረ ብሄር ጫጫታ:: ብርቱ ጫጫታ:: የማሪቱ ቤት መሆኑ ገባኝ:: ነጋሪም አያሻው:: የሀገሬ ሕዝብ ትልቁ መዝናኛ ማእከል እሱ ነው:: ፊልም ቤት፣ትያትር፣ መዋኛ ፣ባር፣ ሬስቶራንት ብትለው አይሰማህም:: አሀ እንዴት ብሎ የማያውቀውን ማን ሊሰማህ:: የሰፊው ሕዝብ መድረክ እዛ ነው:: እዛ ነው ፍልስፍናው ለዛና ቁምነገሩ ጨዋታው ያለው::
አለም የሚቀልጠው፣ነፍስ በሀሴት የምትሞላው ማሪቱ ቤት ነው:: ነፍሱን ይማረውና አንድ መሪጌታ አጎት ነበረኝ :: ጋይንቴ:: በዚያ ዠርጋዳ ቁመቱ ካባውን ለብሶ ጭራውን እየነሰነሰ ሰበር ሰካ እያለ ሲራመድ ሲረገረግ ለአፍታ በአይኔ አስታወስኩትና እንባዬ አቀረረ:: መሪጌታ አፈወርቅ ወግ ይችል ነበር:: አንዳንዴ ሞቅ ብሎት ይመጣል:: አንተ ጠጅቤት ምን ታደርጋለህ መሪጌታ ስለው –ጅሎ ስንቱ ሊቅ ሊቃውንት የተማረው የተመራመረው የሚገኝበትን ቦታ መናቅህ ነው ይልና በጥያቄ መልሶ ያየኛል:: ገና ከንቢቱ ደጃፍ ስደርስ መሪጌታ መጡ መሪጌታ መጡ ይልና ያ ሁሉ ሰው ብድግ ይላል፤ መቀመጫው ላይ ሳልቀመጥ በል ንሳ ቀጂ ፤እኔ ለመሪጌታ አንድ፣ እኔ ሁለት፣ አረ እኔ ሶስት ይላል የተቀመጠው ጋባዥ:: ወግ ይጀመራል፤ ማውካካት ነው:: መሳቅ ነው:: መጫወት ነው አለሜ:: ምኑ ይጠገብ ብለህ የሚለኝ ትዝ ሲለኝ ዳግም እምባ ከጀለኝ::
ዛሬ ሁሉም የሉም::እኒያ ሽማግሌ ጎበጥ ብለው ከዘራቸውን ይዘው ወደ ጠጅ ቤቱ ሲገቡ ሳይ ነው የኋሊት ወስደው መሪጌታን ያስታወሱኝ:: ደሞስ በእዛ እድሜ ሙሉ ቀን ስንት ወር ከቤት ተቀምጦ እንዴት ይገፋል፤ እንደው ሰው ወዳለበት ሄደው ይጫወቱ እንጂ ምነው ምነው ታስሮ ወደ መቃብር መውረድ አለ እንዴ አልኩ ለራሴ::
አይ መሪ:: አባ ግርግር:: እሱ ብቻ አይደለም ቤቱ በሙሉ ይሞቀዋል::ሁሉም በሞቅታ ፈረስ ይጋልባል:: ማንም ማንንም አይሰማም:: ሁሉም ተናጋሪ ነው:: ሰሚ፣ አድማጭም የለም:: ኧረ ተደማመጡ ያልክ እንደሁ፤ ኧረ ዲሞክራሲ መብታችን እኮ ነው ይልሀል አባ ደፋሩ:: መከረኛው ዲሞክራሲም እየተንቀባረረ ጠጅ ቤት ገባ:: ዲሞክራሲ ሕግና ስርአትን አይጠላም::
የጠጅ ቤቱ ታዳሚዎች ስለዲሞክራሲ ብቻ ሳይሆን ስለ ፓርቲም ደግመው ደጋግመው ሰምተዋል:: ተደምመው እነሱም ማቋቋም አለብን ብለዋል:: 137 ፓርቲ በአገር ውስጥ አለ ሲባል እኛስ ለማቋቋም ምን ያንሰናል ብለው ወስነዋል::መጀመሪያ ስም እናውጣ አሉ በመንጫጫት:: ዝም በሉ ደሞ ስም ለማውጣት ከእኛ ሞልቶ የተረፈ አይደለም እንዴ ምን ትላላችሁ አለ ከጠጅ ቤቱ እድምተኛ አንዱ:: እህሳ ደሞ የእድራችንን አይነት መተዳደሪያ ደንብ የፓርቲ ደንብ መጻፍ አለብን ያለሱ አይሆንም ሲባል ሰምተናል አሉና አውካኩ:: ተሰብሳቢው የጠጅ ቤቱ እድምተኛ በጠጅኛ ተኝጫጫ::
ዝም በሉ እስቲ :: ደሞ ይሄን ለመጻፍ ጡረታ የወጡት መምህር ቢራራ ይኸው መሀላችን አሉ አይደለም እንዴ:: ደግሞም ፍርድ ቤት ማመልከቻ የሚጽፈው አቶ አጎናፍር ደባልቄ አለ አይደለም ወይ ለዚህ አያንስም::ሌሎችም መምህሮች አሉ እዚሁ:: መምሬ አለምም ስለቤተክርስቲያን ደንቡ ላይ አንዳንድ ሀሳብ እንዲሰፍር ያደርጋሉ አሉና ዞር ብለው የተወሰኑ ሰዎች አይደለም እንዴ መምሬ ይሄ ይከብድዎታል አሏቸው:: መምሬ ጭራቸውን ያሉበት ሁነው በሞቅታ እየነሰነሱ አልቦ ነገር ዘይሰአኖ ለእግዚአብሄር አይሉም:: ጉደኛዋ ሀገሬ::ሳቅሽና ፈገግታሽ ሁሌም አይጉደል::
በዚህ መሀል ታዳሚው በሙሉ በጫጫታና ሁካታ ሀሳቡን ከደገፈ በኋላ በሰብሳቢው አማካኝነት ወጉ አልቀረም የምትደግፉ፣ የምትቃወሙ ብሎ ሲል የጠጅ ቤቱ አጥር እስኪነቃነቅ ድረስ ጭብጨባው አስተጋባ::ከውጭ ቆማ የነበረች የመምሬ በቅሎ በጭብጨባውና በጫጫታው ብዛት የታሰረችበትን ችካል እያስካካች ነቀነቀችው:: በራ ልትሄድ:: ማጨብጨብና መጮህ እንወድ የለ ? ምን ይደረጋል ብለህ ::
ተረጋጉ ተረጋጉ አንዴ አንዴ አለ በአግዳሚው ወንበር መሀል ላይ የተኮፈሰው ሰብሳቢ:: ምንድነው ተረጋጉ የምትለው አሉት ሰዎቹ:: አሁን ለምንመሰርተው ፓርቲ ስም እናውጣ በፍጥነት አሉት:: ምን ገዶን አሉና ቀጠሉልሀ:: ደሞ ስም ለማውጣት ስም ለመስጠት ማን ብሎን አለ ጀማው እያውካካ:: አንዱ በሞቅታ ብድግ ይልና አንድ ስም ይሰጣል:: ሌላው ይቀጥላል:: ሌላው ይነሳል:: ሌሎችም ባሉበት ሁነው ስም በመስጠት ይጮሀሉ:: አቤት የስሙ መብዛት አቤት የስም ጋጋታ:: ለፓርቲ የሚያስፈልገን እኮ አንድ ብቻ ስም ነው አለ አንዱ ቆፍጠን ብሎ:: ተው ተው ተው ስንልህ:: አይበቃንም ሁላችንም አንድ አንድ ፓርቲ መፍጠር አለብን አለና አረፈው:: ሀ ሀ ሀ ሀ ሀ የሚል ድምጽና ሳቅ ቤቱን አናጋው:: ድንገተኛ የደስታ ጭብጨባ አስተጋባ:: ማን ፓርቲ መስርቶ ማን ይቀራል:: በቃ እያንዳንድሽ ፓርቲ ትመሰርቺያለሽ ማለት ነው:: ነገ እንደተለመደው ከምንጣላ መቼም ባሕሪያችን ክፉ ነውና በግላችን አንድ አንድ ፓርቲ መስርተን እንገላገል በሚለው ተስማሙ::
በሞቅታ ስሜት ሲጽፍ የነበረው ጉርሜሳ ድምጹን ከፍ አድርጎ ሁሉም እንዲሰማ የተሰጡትን ስሞች አንብብ አሉት:: እናም የታጩት ስሞች በንባብ ተደረደሩ:: ተናካሽ ፓርቲ ፣ ተንኳሽ ፓርቲ፣ ሰርሳሪ ፓርቲ ፣ ቀምቅም ፓርቲ ፣ ጨልጤ ፓርቲ፣ ጎንጤ ፓርቲ ፣ ፈላጭ ፓርቲ፣ ፈንካች ፓርቲ ፣ አውልቅ ፓርቲ ፣ አስርግ ፓርቲ፣ አስማጭ ፓርቲ፣ አዝግ ፓርቲ ፣ ድፎ ፓርቲ፣ ድፍድፍ ፓርቲ፣ እያለ ሰውየው በሞቅታ ሲያነብ ተሰብሳቢው እድምተኛ በከፍተኛ ድምጽና ጭብጨባ አድናቆቱና ደስታውን ገለጸ:: ነገ ማታ ሁልሽም ተገኝተሽ በፊርማሽ ታጸድቂያለሽ አለ ጸሀፊው:: ለነገ ማታ ያድርሰን እያለ የነገን ጠጅ እየናፈቀ ሁሉም ወደየቤቱ ተፈተለከ:: ጉደኛዋ ሀገሬ ኑሪልኝ !!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 9/2012
ወንድወሰን መኮንን