አዲስ አበባ፡- በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ከተከሰቱት ግጭቶች ጀርባ የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮችና የጸጥታ መዋቅሩ እጅ እንደነበረበት የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አስታወቀ፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በኦሮሚያ ክልል ቡራዩ እና በአዲስ አበባ እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች የነበረውን ግጭቶች የምርመራ ውጤት፤ የገና በዓልን አስመልክቶ ለታራሚዎች ምህረት ስለመሰጠቱ እንዲሁም የምህረት አዋጁ ተጠቃሚ የሆኑ ታራሚዎችን ጉዳይ አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ቱኑ እንደተናገሩት፤ በኦሮሚያ ክልል በቡራዩና በአዲስ አበባ ከተማ የተከሰቱ ግጭቶችን ጨምሮ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች ዙሪያ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ከፌዴራል ፖሊስ እና ከሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ምርመራ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ በምርመራው ውጤት መሰረትም በሁሉም አካባቢዎች ከተከሰቱ ሁከቶችና ግጭቶች ጀርባ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትና የጸጥታው መዋቅር እጅ ነበረበት፡፡
እነዚህ አካላት ለውጡን ተከትሎ እየታዩ ያሉ መልካም ተግባራት እንዳይቀጥሉ ስለሚፈልጉት ከጀርባ ሆነው ግጭቶችን ከመቀስቀስ አልፈው፤ ለዘመናት ኢትዮጵያዊያን በጋራ ያፈሩት እሴቶች እንዳይቀጥሉ ለማድረግ ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር በምርመራው ለመለየት መቻሉን የገለጹት አቶ ዝናቡ፤ በእነዚህ ድርጊቶች ውስጥ የተሳተፉ ተጠርጣሪዎች ሁሉም ተለይተዋል ብለዋል፡፡
እነዚህ አካላት ከጀርባ ሆነው አመራር በመስጠት እና በገንዘብ ጭምር በመርዳት ሲመሩት የነበረውና በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱት ግጭቶች በርካቶችን ለሞት፣ ለአካል ጉዳት፣ ለመፈናቀል እና ለንብረት ውድመት እንደዳረጋቸውም አቶ ዝናቡ በመግለጫው ጠቁመዋል፡፡
እንደ አቶ ዝናቡ ማብራሪያ ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ላይ ክስ ተመስርቶባቸው በህግ ጥላ ስር ሆነው ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት እንዲከታተሉ ተደርጓል፡፡ በቁጥጥር ስር ያልዋሉትም በቁጥጥር ስር የማዋል ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
በመላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 25/2011