የመማሪያ ክፍሎቹ ጥሩ መቀመጫ የላቸውም፡፡ መምህራንም ቋሚ ቢሮ የላቸውም፡፡ ንብረቶቻቸውንም በእነዚህ ክፍሎች ነው የሚያስቀምጡት፡፡ በክረምት ወቅት ትተውት የሄዱትን ንብረት መስከረም ሲጠባ ላያገኙት ይችላሉ፡፡ በክፍሎች ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎች በንፋስ ይታወካሉ፤ ጸሐይ ላይ ነጭ ወረቀት ለማንበብ ይቸገራሉ እንዲሁም ዝናብ በሚመጣበት ጊዜ ስለማያስጠልል ትምህርታቸውን አቋርጠው ይሄዳሉ – ይህ በአማራ ክልል ስለሚገኙ የዳስና የዛፍ ስር ትምህርት ቤቶች በክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ በዶክተር ይልቃል ከፍያለው የተነገረ ታሪክ ነው፡፡
በአማራ ክልል በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ትምህርት ከሚሰጥባቸው ስፍራዎች መካከል በዋግህምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ጻግብጂና አበርገሌ ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ የዳስ ትምህርት ቤቶች በትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ በኅዳር ወር አጋማሽ ተጎብኝተው ነበር፡፡
ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው ወቅት ያነጋገሯቸው የአካባቢው ተማሪዎች፣ መምህራንና ነዋሪዎች በዳሶችና በዛፍ ጥላ ስር የሚካሄደው መማር ማስተማር ለትራኮማ እንዲሁም ለተለያዩ ማህበራዊና ሥነልቦናዊ ችግሮች እንደዳረጋቸው ተናግረዋል፡፡
ዶክተር ጥላዬ በወቅቱ በሰጡት ምላሽ በዞኑ ትምህርት እየተሰጠባቸው በሚገኙ የዳስ ትምህርት ክፍሎች የተመለከቷቸው የከፉ ችግሮች እንዲወገዱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው የድርሻውን እንደሚወጣ አስታውቀው ነበር፡፡ ተማሪዎች አካባቢያዊ ችግርን ተቋቁመው ከሚያስቡት ደረጃ ለመድረስ እንዲጥሩ በመምከር በዳስ የሚካሄዱ የመማር ማስተማር ሥራዎችን በማስቀረት በተማሪዎችና በመምህራን ላይ የሚደርሱ ችግሮችን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ውጤታማ የሚሆነው የሁሉም ባለድርሻዎች ተሳትፎ ሲታከልበት በመሆኑ ህብረተሰቡ የበኩሉን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
የአማራ ክልል ት/ት ቢሮ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ቢያዝን እንደሚሉት፤ በዋግኽምራ ብሔረሰብ ዞን በስድስት ትምህርት ቤቶች 2 ሺ 547 ተማሪዎች በዛፍ እና በዳስ ስር ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ፡፡ በሰሜን ጎንደር አስተዳደር ዞን ደግሞ በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ሃምሳ አምስት የዛፍ እና የዳስ ስር መማሪያ ክፍሎች አሉ፡፡ የመማር ማስተማር ሂደቱ በዚህ መልክ እየተከናወነ በመሆኑም መምህራንና ተማሪዎች ጸሐይ፣ ብርድና ዝናብ እየተፈራረቁባቸው ለጤና ችግሮችም እየተጋለጡ ናቸው፡፡
አቶ ጌታቸው እንደሚሉት፤ ችግሩን ለመፍታት ‹‹ትምህርት ቤቶቻችንን ከዳስ ወደ ‘ክላስ’ ከጭቃ ወደ ብሎኬት እንቀይራለን›› በሚል መሪ መልዕክት ባለፈው የክረምት ወቅት ከትምህርት ባለድርሻ አካላት ጋር በየደረጃው ውይይት ተካሂዷል፡፡ በውይይቱም ህብረተሰቡ የመማሪያ ክፍሎችን ለመሥራት በጉልበትም ይሁን በገንዘብ የሚችለውን ሁሉ ለማድረግ ቃል በገባው መሰረት ከደረጃ በታች የሆኑ መማሪያ ክፍሎችን ለመለወጥ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
በክልሉ የዛፍ ስር እና የዳስ ስር ትምህርት ቤቶችን ለማስቀረት የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ ትምህርት ቢሮው ከህብረተሰቡ በሚደረግለት ድጋፍ በመታገዝ በዋግኽምራ ብሔረሰብ ዞን ሁለት ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ወደሙሉ ትግበራ ገብቷል፡፡ በቀጣይም የዛፍ እና የዳስ ስር መማሪያ ክፍሎችን መሉ ለሙሉ አመችነት ባላቸው የመማሪያ ክፍሎች ለመቀየር እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው፡፡
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ይልቃል ከፍያለው በበኩላቸው እንዳስረዱት በአማራ ክልል ውስጥ ትምህርትን ለማስፋፋት የአቅም ውስንነት በመኖሩ ባለፉት አስራ አምስት ዓመታት ‹‹በዛፍ ስርም ይሁን በዳስ ስር ትምህርትን እናስፋፋ›› የሚል አቅጣጫ ተቀምጦ ሲሠራበት መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ቅድመ መደበኛን ጨምሮ በአሁኑ ሰዓት ከአምስት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች የትምህርት ተቋዳሽ መሆናቸውን በመግለጽ ‹‹ይህን ዕድል ማግኘት ቀላል ነገር አይደለም፤ ተማሪዎች በእንዲህ አይነት ሁኔታ ተምረውም ውጤት ተገኝቷል ነገር ግን ዘመኑ ስለማይፈቅድ አሁን መቀየር አለበት›› ብለዋል፡፡
እየተደረገ ያለው ጥረት እና የችግሩ ስፋት ባለመጣጣሙ የተጀመሩት የዳስ ስር እና የዛፍ ስር ትምህርት ቤቶች ባሉበት ሊቀጥሉ መቻላቸውን የገለጹት ዶክተሩ፤ እነዚህ ትምህርት ቤቶች በዋናነት የሚገኙት በዋግኽምራ እና ሰሜን ጎንደር ዞን ይሁን እንጂ በሌሎች አካባቢዎችም አልፎ አልፎ ያገለግላሉ ብለዋል፡፡ አሁን እየተጠናከረ በመጣው የህብረተሰቡ ተሳትፎም በቀጣይ ችግሮቹ ሊፈቱ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡
እንደ ዶክተር ይልቃል ማብራሪያ፤ አብዘኞቹ በህብረተሰቡ ተሳትፎ የተሠሩ ትምህርት ቤቶች ደረጃቸውን የጠበቁ ባለመሆናቸው በየጊዜው ይፈርሳሉ፡፡ ህብረተሰቡም የፈረሱትን ትምህርት ቤቶች መልሶ መገንባት ባለመቻሉ በዳስ ይተካሉ፡፡ በተጨማሪም ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል የሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶች በአካባቢያቸው እስከ 8ኛ ክፍል የሚያስተምር ሌላ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ እስከ ስምንት ያሉትን ክፍሎች በዳስ ይመሰርታሉ፡፡ በእነዚህ ሁለት ምክንያቶች ሲመሰረቱ ጀምሮ የዳስ ትምህርት ቤቶች ከሆኑት ውጪ ተጨማሪ የዳስ መማሪያ ክፍሎች በተለያዩ አካባቢዎች በስፋት ይገኛሉ፡፡
«በክልሉ ትምህርት ቤቶች በህብረተሰብ ተሳትፎና በወረዳ በጀት በጋራ ትብብር ነው የሚሠሩት» ያሉት የትምህርት ቢሮ ኃላፊው፣ ችግሩ እስካሁን ድረስ ሊዘልቅ የቻለው በዋናነት የአቅም ውስንነት በመኖሩና አመራሩ ትኩረት ባለመስጠቱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ዶክተር ይልቃል ችግሩን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመቅረፍ እየተደረገ ያለውን ጥረት ሲገልጹ «ከክልል ጀምሮ በዞንና ወረዳ ካሉ ከሚመለከታቸው አመራሮች ጋር በተቀናጀ መንገድ እክሉን ለመፍታት ተስማምተናል፡፡ በዚህ ዓመት የተለየ በጀት መድበን ከሰላሳ ሺ በላይ ቆርቆሮዎች ገዝተን ለተለያዩ ትምህርት ቤቶች ለማከፋፈል ጥረት እያደረግን ነው፡፡ ትምህርት ሚኒስቴርም ለማገዝ ቃል ገብቷል፡፡ ህብረተሰቡም በጉልበቱና በገንዘቡ ሊያግዝ ተዘጋጅቷል፡፡ ለምሳሌ ዋግኽምራ አካባቢ ህብረተሰቡ ድንጋይና እንጨት፤ የክልሉ መንግሥት ደግሞ ቆርቆሮና ሚስማር ያቀርባል» ብለዋል፡፡ ህዝቡ ድጋፉን አጠናክሮ ከቀጠለና አመራሩ በቁርጠኝነት ከተንቀሳቀሰ የዳስ ትምህርት ቤቶችን በ2012 ዓ.ም ከክልሉ ማጥፋት እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 25/2011
የትናየት ፈሩ