የሚሰማው ወሬ ሁሉ ይረብሻል። የበርካቶች ጨዋታ ተመሳስሏል። የብዙዎች ስሜት ተጋግሏል። አንዱ ከሌላው የሚያመጣው መረጃ ዓይነቱ ብዙ ነው። አገር ተወራለች፣ ዳር ድንበር ተደፍሯል፤ ይሉት እውነት ለጆሮ አይመችም። በየቦታው ፉከራና ቀረርቶ ይሰማል። ሙዚቃው በጀግንነት ዜማ ተተክቷል። የኢትዮ-ኤርትራ ግጭት ከቃላት ምልልስ አልፎ ጦርነት ሊታወጅበት ክተት ሰራዊት እየተባለ ነው። በወርሀ ግንቦት 1990 ዓ.ም. አገር ምድሩ ለአይቀሬው ዘመቻ መዘጋጀት ይዟል። አሁን የወጣቶች፣ የእናቶች፣ የአባቶች፣ የወታደሩና የመንግሥት ስሜት በአንድ ተጣምሯል። «እንዘምታለን! እንዋጋለን! እናሸንፋለን!» የሚለው ድምጽ እየተበራከተ ነው። ይህን ተከትሎ በየስፍራው የደረሰው መነሳሳት በመላው ኢትዮጵያ መቀጣጠል ጀምሯል።
በደብረማርቆስ ከተማ በቀበሌ 05 ውስጥ የሚኖሩ ኤርትራዊያን ቤተሰቦች የጦርነቱን ክተት ሰምተዋል። በየቀኑ ስላለው ለውጥም በእጅጉ እየተጨነቁ ነው። እነርሱ በዚህ ሰፈር በርካታ ዓመታትን ሲያሳልፉ ልጆች ወልደው ስመዋል። ከጎረቤትና ከአገሬው ዝምድና ፈጥረው በአንድ ውለው አድረዋል። እስከዛሬ እነርሱነታቸውን ከሌላው የሚያርቅ ክፍተት አልነበረም። ባህልና ወጋቸው፣ ቋንቋና ሃይማኖታቸው፣ ኑሮና ጓዳቸው ሁሉ ያለ ልዩነት የተጣመረ ነው።
የሰሞኑ ድንገተኛ ዜና ያሳሰባቸው ኤርትራዊው አቦይ ተወልደ ጠዋት ማታ በሀሳብ መቆዘም ይዘዋል። በርካታ ዓመታት በዚህ ከተማ ሲኖሩ ከሁሉም ተግባብተውና ተከባብረው ነው። አምስት ልጆቻቸው ከእኩዮቻቸው ጋር በአንድ ሜዳ ቦርቀው አድገዋል። እርሳቸውም ቢሆኑ ከጎረቤቶቻቸው ጋር ደስታና ሀዘን ተጋርተዋል። በዕድር ከማህበሩ አይለዩም። ቤት ሰርተው፣ ኑሮ መስርተው በኖሩበት ሰፈርም «አንቱ» ተብለው ሲከበሩ ቆይተዋል። አሁን ግን ይህ ሁሉ እውነት ስጋት እያጠላበት ነው።
አቦይን ጠዋት ማታ በሀሳብ ሲያዋልላቸው የቆየው ጉዳይ እውን መሆኑ አልቀረም። በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ ኤርትራዊያን ከሀገር እንዲወጡ ተወስኗል።ጥቂቶች ሀብት ንብረታቸውን ሸጠው ጓዛቸውን ሸክፈዋል። በርካቶች የሚይዙት የሚጨ ብጡት ጠፍቷቸው ግራ ተጋብተዋል።
አሁን አቦይ ከነመላ ቤተሰባቸው አገሩን ሊለቁ ነው። ይህ ማለት ግን ለእርሳቸው በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም። ስሜቱ በእጅጉ ይከብዳል። ከተማዋ የታሪካቸው ማድመቂያ ቀለም ናት። የልጆቻቸው፣ የትዳራቸው አሻራ፤ የማንነትና የሁለንተናቸው መሰረት፤ እንጀራ ያገኙባት፣ ወግ ማዕረግ ያዩባት፣ ክፉ ደግ ያሳላፉባት ድንቅ ሀገር፤ ደብረ ማርቆስ፤ ጓዛቸው ታስሮ ተሰናድቷል። ሌቱ ሲነጋ መንገደኞችን የሚያሳፍሩ አውቶቡሶች ተደርድረዋል። ተጓዦቹን የሚሸኘው ነዋሪ በዕንባ እየተራጨ ነው። የቀን ክፉ፣ የትናንት ወገኑን ሊለየው ነውና አገሬው ሀዘኑ በርትቷል።
ባልንጀራ ህጻናት ሲለያዩ ይላቀሳሉ። የአብሮነቱ አይረሴ ቀን ዕንባ በሸፈነው ትዝታ ተከልሎ በአዲስ ሊተካ ነው። መንገዶች ሁሉ ወደ ኤርትራ፤ አስመራ ያመራሉ። «ደህና ሁኑ ወገኖች! ደህና ሁኚ ማርቆስ!»ይህ ሁሉ ሲሆን አቦይ ተወልደ በመጀመሪያው ዙር አልተካተቱም። እርሳቸው ለጊዜው ባይጓዙም መላ ቤተሰባቸውን ልከው በቀጣዩ ለመሄድ ተዘጋጅተዋል። ለአሁኑ መዘግየታቸው ደግሞ በቂ ምክንያት አላቸው። አቦይ በደብረ ማርቆስ ከተማ የሰሩትን መኖሪያ ቤት በአደራ ሊሰጡ አስበዋል። ማን ያውቃል!? ምንአልባትም አንድ ቀን ተመልሰው ይመጡ ይሆናል።
ተወልደ ይህን አደራ ስለሚሰጡት ሰው ደጋግመው አሰቡ፡፡ አንዱን ከአንዱ ለይተውም ሚዛን ላይ አስቀመጡ። በመጨረሻ መለኪያቸው ወደ አቶ ሀጎስ ተስፋዬ አጋደለ። ቀለም ቀቢው ሀጎስና ሾፌሩ ተወልደ በጉርብትና ክፉ ደግ አሳልፈዋል። እናም ቤታቸውን በአደራ ለማስረከብ አመኔታ ሲጥሉባቸው አልተጠራጠሩም። ዕምነት ተቀባዩም የባልንጀራቸውን መኖሪያ ቤት ሲረከቡ ከቃል ዕዳ በቀር ምንም አልጠየቁም።
እነሆ! ይህ ከሆነ ድፍን ሃያ ዓመታት ተቆጠሩ። አዎን! መሬት ተለይቶ ድንበር ተከልሏል። መንገዱ ተዘግቶ መተያየት ቀርቷል። ሕዝብ ተራርቆ ወዳጅነት ደብዝዟል። በእነዚህ ጊዚያት ውስጥ ባልንጀሮቹ ደብዳቤም ሆነ የቃል መልዕክት አልተለዋወጡም። እነዚህ ዓመታት ለሁለቱ አገራት ህዝቦች እንደ ጥቁር መጋረጃ ነበሩ። አንዱ ሌላውን የማያይበት ግዙፍ የጨለማ ዘመን፤ ከጥቂት ጊዚያት በፊት ደግሞ ከኤርትራ ተራሮች ተሻግሮ፤ ከኢትዮዽያ ድንበር ማዶ አንድ ብስራት ተሰማ። በሀገሪቱ የተፈጠረውን ፖለቲካዊ ለውጥ ተከትሎ የኢትዮ-ኤርትራ ጉዳይ በእርቅ ስምምነት ሊቋጭ መሆኑ ተረጋገጠ። ይህኔ ታሪኩን የሰሙ ጆሮዎች ነቁ። ዕንባ የሸፈናቸው አይኖች ብርሃን ፈነጠቁ። ውስጣቸው ደስታ ተላበሰ፣ አንደበት በእልልታ ተላወሰ። ሁለቱ ሀገራት ቂምና በደላቸውን በይቅርታ ሽረው በአዲስ የሰላም ምዕራፍ ታሪካቸውን ቀየሩ።
ወይዘሮ ጤና መኮንን የአደራ ተቀባዩ የአቶ ሀጎስ ተስፋዬ ባለቤት ናቸው። ከዛሬ ሃያ ዓመታት በፊት የትዳር አጋራቸው አንድ የግል መኖሪያ ቤት በአደራ ስለመረከባቸው ጠንቅቀው ያውቃሉ። የዛኔ ኤርትራዊያን ወደሀገራቸው ሲገቡ እሳቸውን ጨምሮ በርካቶች በሃዘኔታ እንደሸኟቸውም ትዝ ይላቸዋል። በወቅቱ አደራ ሰጪና ተቀባይ ቤቱን ሲረካከቡ በመሃከላቸው ካጸኑት ዕምነት በቀር መተማመኛ አልተለዋወጡም ።
የአጋጣሚ ጉዳይ ሆኖ ዛሬ ሁለቱ ባልንጀሮች በህይወት የሉም። አቦይ ተወልደ አገራቸው ኤርትራ በገቡ በሰባተኛው ዓመት አርፈዋል። አቶ ሀጎስም ከአስራ አንድ ዓመታት በፊት በሞት ተለይተዋል። የአደራ ሰጪና ተቀባይ ዕምነት ግን ዛሬም ውሉን ሳይስት እንደተጠበቀ ዘልቋል። ለዚህ እውነታ ታላቁን ድርሻ የተወጣው የወይዘሮ ጤና ቤተሰብ ንብረቱ በአግባቡ ይጠበቅ ዘንድ በብዙ ፈተናዎች መሃከል ሊያልፍ ግድ ብሎታል። ያለፉትን ዓመታት በድንበር ይገባኛል፣ በወሰን ማስከበርና በሌላም ከጎረቤት ጋር መጣላትና መካሰሱ ቀላል አልነበረም።
ከሁሉም በላይ ግን የሙት ባለቤታቸውን አደራ የተረከቡት እመት ጤና ቃላቸውን መጠበቅ ነበረባቸው። ለእርሳቸው ይህ ማለት ከቃል በላይ ቃል፣ ከሸክምም የከበደ ጫና ነውና። ቤቱ በእርጅና ብዛት እንዳይወድቅ ከማደስ ጀምሮ ዕምነትን ጠብቆ አደራን መወጣት ቀላል አይደለም። «ሽጡት፣ በስማችሁ አዛውሩት» ይሉት መካሪም ፈተና ነበር። አሁን ግን ታሪክ ተቀይሯል። ድንበሮች ተከፍተው፤ ሁለቱ ሀገራት እርቀ-ሰላም አውርደዋል። የተለያየው ሊገናኝ፤ የተራራቀው ሊቀራረብ ጊዜው ደርሷልና መልካም ዜናዎች እየተሰሙ ነው።
አንድ ቀን ረፋድ የወይዘሮ ጤና መዝጊያ በስሱ ተንኳኳ። ይህ እንደተሰማም ከደጅ ለቆመው እንግዳ በሩ ተከፈተለት። ቀይ መልከመልካም ወጣት ከበር ቆሟል። ሁኔታው ጸጉረ ልውጥ ቢመስልም መልኩ አዲስ አልነበረም። ማንነቱን መናገር እንደጀመረ ወደውስጥ እንዲገባ ተጋበዘ። ይህ ወጣት ከሃያ ዓመታት በፊት ቤቱን በአደራ ያስረከቡት ሰው የአቶ ተወልደ የመጀመሪያ ልጅ ሙሴ ተወልደ ነው።
ሙሴ የዛኔ ማርቆስን ለቆ ሲወጣ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ነበር። ዛሬ ደግሞ በዕድሜ ገፍቶ አዋቂ ሆኖ መመለሱ ሁሉንም አስገርሟል። በፍቅር ተቀብለው ያስተናገዱት ቤተሰቦች የአባቱን ማረፍ ባወቁ ጊዜ በእጅጉ አዘኑ። የመጣበትን ጉዳይ እንደተረዱም ወላጅ እናቱን ይዞ እንዲመለስ ነግረው አሰናብተውታል። አዎን! ዛሬ ሙሴና ቤተሰቦቹ በሁለቱ አባወራዎች መሃከል የቆየውን ንብረት መረከብ ይሻሉ። የአደራ ተቀባዩ የአቶ ሀጎስ ቤተሰቦችም በሀሳባቸው አልተከፉም። የሚሉትን ሊፈጽሙ፤ የጠየቁትን ሊከውኑ ተዘጋጅተዋል። አደራን ጠብቀውና ቃል አክብረው ለዚህ ቀን መብቃታቸው ደግሞ በእጅጉ አኩርቷቸዋል።
ኤልሳቤጥ ሀጎስ ከሃያ ዓመት በፊት አባቷ ቤቱን በዕምነት ስለመረከባቸው ታውቃለች። ታመው በደከሙ ጊዜም በመጨረሻ እስትንፋሳቸው ቤተሰቡ አደራቸውን እንዲወጣ ቃል አስገብተዋል። አሁን እሳቸው ካለፉ አስራ አንድ ዓመታት ተቆጥረዋል። ኤልሳም በእነዚህ ዓመታት መሃከል በአካባቢው ስለተፈጠረው የቦታ ውዝግብ አትረሳም። ይህ ሁሉ በትዕግስት ታልፎ የሙት አባቷን አደራ በማክበሯ ግን ደስተኛ ነች።
አደይ ዕቁባይ ገብረአብ ደብረማርቆስን የተወለዱባት ያህል ያውቋታል። ከኤርትራ ትዳር ይዘው እንደወጡ አምስት ልጆች ወልደው ያሳደጉት በዚህች ከተማ ነበር። የዛኔ ከጎረቤቶቻቸው ጋር በተለየ ፍቅር ኖረዋል። ሾፌሩ ባለቤታቸው ቤትና ጓዳቸውን ለመሙላትና ልጆቻቸውን ለማሳደግ ብርቱ ነበሩ። አደይ በሁለቱ ሀገራት መሃከል በተከሰተው ችግር ከነቤተሰባቸው እርቀው ቆይተዋል። ዛሬም ግን የሀገሬው የለቅሶ አሸኛኘት ትዝታቸው ነው። አስመራ ደርሰው ህይወትን እንደአዲስ መጀመር ፈተና እንደነበር የሚናገሩት እናት፤ ዛሬ ሁሉ ተቀይሮ ቤታቸውን በመረከባቸው ደስተኛ ሆነዋል። ይህን ላደረጉ ባለአደራ ቤተሰቦችና ዛሬ በህይወት ለሌሉት አባወራም ምስጋናቸው ከልብ ነው።
ወጣት ሙሴ ተወልደ ዳግመኛ ስለረገጣት ደብረማርቆስ የተለየ ትዝታ አለው። የዛኔ ወደ ሀገረ ኤርትራ ሲያቀና አብሮ አደጎቹ ባልንጀሮቻቸውን አልጋ ስር ደብቀው ለማስቀረት መሞከራቸውን ያስታውሳል። አስመራ በገባ ጊዜም ቋንቋ ለማወቅና ከሌሎች ለመግባባት ተቸግሮ ቆይቷል። የሃያ ዓመት ቆይታው አፈር ፈጭቶ ካደገበት ቀዬና ከአብሮ አደጎቹ ትውስታ ያራቀው አልነበረም። ዛሬ በሌላ ታሪክ የመመለሱን እውነታም ከማርቆስ ህዝብ ፍቅርና ታማኝነት ጋር ያጣምረዋል።
አቶ ንጉሴ ብናልፈው የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር የፍትህ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ናቸው። የሁለቱን ቤተሰቦች ታሪክም በቅርበት ያውቁታል። እሳቸው እንደ ኃላፊነታቸው ቤቱን በማረካከብ ሂደት ተሳትፈዋል። እንደ አቶ ንጉሴ አባባል፤ የአደራ ተቀባዮቹ ማንነት በቅንነት የተቃኘ ነው። እነሱ ክፋት ቢያስቡ ለሶስተኛ ወገን ማሳለፍ ይችሉ ነበር። ይሁን እንጂ፤ የሟችን አደራ ጠብቀው ቤቱን ለባለቤቱ ማስረከባቸው ለብዙዎች ተምሳሌት አድርጓቸዋል።
እንደእሳቸው አባባል እንዲህ አይነቱ መልካምነት ለከተማው ህዝብ አዲስ አይደለም። ቀደም ሲልም የሌሎች ኤርትራዊያን ቤትና ንብረት ለባለቤቶቹ ተመልሷል። ቤቱ ታሽጎና ሙሉ ንብረቱ ተጠብቆ ሲቆይም ነዋሪው ደግሶና ድንኳን ጥሎ በእልልታ ተቀብሏቸዋል።
አቶ ንጉሴ እንደሚሉት፤ ይህ በጎነት ከሕዝቡ ጨዋነት ይመነጫል። አብዛኛው ማርቆሴ ለባህልና ለዕምነቱ ሟች ነው። ማርቆስ አደራ አይበላም። መካድ መካካድንም አያውቅም። እነሆ ዛሬ ይህ እውነት የሙት አደራ ሳይቀር አስጠብቋል። የቃሉ ግዝፈትም ከማርቆስ ዘልሎ፤ ከኢትዮጵያ ድንበር አልፎ ኤርትራ ባህርን እንዲህ ተሻግሯል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 24/2011