ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርሶች መዝገብ የተመዘገቡ የማይንቀሳቀሱ ቅርሶች አሏት፡፡ በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ ከሚገኘው ከራስ ዳሸን ተራራ ጀምሮ እስከዳሎል ዝቅተኛ ስፍራ ድረስ በአስደናቂ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ እና የአየር ንብረት፣ የብርቅዬ የዱር እንስሳት መገኛ፣ የራሷ የዘመን አቆጣጠርና ፊደል፣ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት ጭምር ናት፡፡ ይህም ኢትዮጵያን በእርግጠኝነት አስገራሚ የቱሪዝም ሀብቶች መገኛ ምድር አድርጓታል፡፡
ኢትዮጵያ የቅድመ ሰው ዘር መገኛ ሀገርም ናት፡፡ የኢትዮጵያዊያን ቅድመ አያት የሆነችው የ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዓመት እድሜ ባለቤት ድንቅነሽ(ሉሲ)፣ የአራት ነጥብ 4 ሚሊዮን ዓመት እድሜ ባለቤት አርዲ እና ሶስት ነጥብ 3 ሚሊዮን ዓመት እድሜ ያስቆጠረችው ሰላም የቅድመ ሰው ዘር፤ የቅድመ ታሪክ ቅርሶች ባለቤት ናት፡፡
ኢትዮጵያ የ3000 ዘመን ታሪክም ያላት ናት፡፡ የአክሱም የነገስታት ሥርወ መንግሥት የጥንታዊ ስልጣኔዋ መነሻ እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ይናገራሉ፡፡ ለአብነት በአክሱም ከተማ የሚገኙ የነገሥታት የመቃብር ሥፍራዎችና ሐውልቶችን፤ በመካከለኛው ክፍለ ዘመን ከሐይማኖታዊ ሥልጣኔዎች መስፋፋት ጋር ተያይዞ የታነፁትን የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ ከአንድ ሺህ ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረውን የሐረር ጀጎል ግንብ፤ በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አካባቢ የታነፀውንና በኢትዮጵያ የጥንታዊ ከተሞች ታሪክና ዕድገት ፈር ቀዳጅ የሆነውን የጎንደር ነገሥታት ህንፃ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ሌላው የኮንሶ ባህላዊ መልክዓ ምድርና የአፈር እቀባ፤ የእርሻ አስተራረስ ዘዴ፣ እንዲሁም በአገሪቱ መካከለኛ ክፍል የሚገኘው የጢያ ትክል ድንጋዮች ስፍራ፣ የታችኛው ኦሞ እና የመካከለኛ አዋሽ ፓሊዮ አንትሮፖሎጂካል ሥፍራዎች፣ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተመዘገቡ 12 ባህላዊ፣ ታሪካዊ ተፈጥሯዊ ቅርሶች፣ 12 የሥነ ጽሑፍ ሀብቶች እና 4 ጥበቅ ብዝሃ ሕይወት ቦታዎች ኢትዮጵያ የቱሪዝም ሀብት ባለቤት ስለመሆኗ ከቱሪዝምና ባህል ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ እንዲሁም፤ ኢትዮጵያ ከ80 በላይ የሚሆኑ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች ሕዝቦች ሀገር ናት፡፡ ሕዝቦቿም የየራሳቸው የሆነ ማንነት የሚገለጽበት ባህል፣ ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ስነቃል፣ ወግ፣ ዕምነት፣ ዕሴትና ሥነጥበብ ሀብቶች አሏቸው፡፡
ይህ ሁሉ የቱሪዝም ሃብት ባለቤት ብትሆንም የቱሪስት ፍሰቱ ግን ከሌሎች የአፍሪካ ሃገሮች ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ነው፡፡ የአለም የቱሪዝም ድርጅት እአአ የ2017 መረጃ እንደሚያመለክተው ሞሮኮና ደቡብ አፍሪካ እያንዳንዳቸው 10 ሚሊዮን፣ ቱኒዝያ 5ነጥብ72 ሚሊዮን፣ ግብጽ 5ነጥብ26 ሚሊዮን፣ ዝምባብዌ 2ነጥብ 17 ሚሊዮን ቱሪስቶች የጎበኟቸው ሲሆን ኢትዮጵያን የጎበኙት ግን 900ሺ ቱሪስቶች ብቻ ናቸው፡፡ ይህ የሚያሳየው ካላት ሃብት አንጻር አነስተኛ መሆኑ ነው፡፡
‹‹የቱሪዝምን ፍሰት መጨመርና ተጠቃ ሚነትን ማሳደግ የሚቻለው መጀመሪያ አስተ ማማኝ ሰላም በማስፈን ነው የሚሉት የሀረሪ ክልል የባህልና ቱሪዝም ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አዮብ አብዱላሂ፤ ሰላም ለቱሪዝም ዕድገት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ሁለተኛው፤ የቱሪስት መስህቦችን በበቂ ሁኔታ የማስተዋወቅና የማልማት ተግባር ነው፡፡ በታወቁ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችና በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች በመጠቀም ሀብቱን በሚገባ ለመላው ዓለም ማስተዋወቅ ተገቢ ይሆናል ይላሉ፡፡ ማስተዋወቅ ላይ ማተኮር ብቻ ሳይሆን የቱሪስት መዳረሻዎችንም ማልማት ጎን ለጎን የሚሰራ አንኳር ተግባር ነው የሚል ሀሳብ አላቸው፡፡
ቱሪስቱ በማስታወቂያ የሰማውንና ያየውን በትክክል በመሬት ላይ መኖሩን ማረጋጋጥ ይፈልጋል፤ ይገባል፡፡ ቱሪስቶች በመንገድ ላይ ምጽዋት በመጠየቅ የሚያስቸግር ሰው አይወዱም፡፡ በየሄዱበት አካባቢ ሁሉ የተሟላ የሆቴልአገልግሎት ማግኘት አለባቸው፡፡ሆኖም በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ባለአራት ኮከብ ሆቴልና ኬንያ ወይንም ዛንዚባር ውስጥ የሚገኝ ባለ አራት ኮከብ ሆቴል የአገልግሎት ጥራትና አይነቱ ልዩነት ሰማይና ምድር ነው፡፡ ስለዚህ ኮከቡን ማን እንደሚሰጣቸው አይታወቅም፤ ሲሉ በኛ ሀገር ሆቴሎች አገልግሎታቸውና ማዕረጋቸው የተመጣጠነ አለመሆኑን በትዝብታቸው አካፍለውናል፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ብዙ የቱሪስት መስህብ ቦታዎች ቢኖራትም በቱሪስት ፍስት ግን ኬንያ ትበልጣታልች የሚሉት አቶ አዮብ፤ እንዳለን ሀብት ምንም አልተጠቅምንበትም ማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ብዙ የቱሪስት መስህቦች አሉን፤ ግን ብዙ ቱሪስት ማምጣት አልቻልንም ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ በሌላ በኩል፤ የቱሪስቱ ፍስት ይህን ያህል ጨምሯል ተብሎ ይፋ የሚደረገው መረጃም የተጋነነ ነው የሚል እምነት አላቸው፡ ምክንያቱም በአንድ ከተማ አራት ሙዚየም ካለ አንዱ ሰው አራቱንም ቢገባ አራት ጊዜ ይቆጠራል፤ ሲሉ ይፋ የሚደረገው የቱሪስት ቁጥር ስህተት መሆኑን ማሳያ በመጠቀስ አስረድተዋል፡፡
አንድ ቱሪስት ወደ አገር ውስጥ መጥቶ ገንዘብ የሚያወጣባቸውን ብዙ አይነት አገልግሎቶች ማቅረብ ካልተቻለ ተጠቃሚነቱም አነስተኛ ነው የሚሉት ምክትል ቢሮ ሀላፊው፣ የተለያዩ አማራጭ አገልግሎቶችን በመፍጠር ገንዘብ ማግኛ ዘዴውን ማስፋት ሲቻል ከቱሪዝም የሚፈለገውን ይህን ጥቅም ማግኘት ይቻላል የሚል ሀሳብ አላቸው፡፡ እናም አሉ አቶ አዮብ፤ ቱሪስቱ በሚያያቸውና በሚጠቀማቸው ነገሮች ላይ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይገባል፡፡ የቱሪስት መስህብ አካባቢዎችን ማልማት ያስፈልጋል፡፡
ይሁን እንጂ፤ የቱሪስት መስህብ አካባቢዎችን በማልማት ረገድ ውስንነት ይታያል፡፡ የአገሪቱን የቱሪዝም ዘርፍ ከነበረበት አዝጋሚ የለውጥ እንቅስቃሴ ወደ እመርታዊ ለውጥ እንዲሸጋገር ከፍተኛ ኃላፊነት ተሰጥቶት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 294/205 የተቋቋመው የኢትዮጵያ ቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት እስካሁን ድረስ ወደመሬት የወረደ ምንም የሰራው ነገር የለም፡፡ በዘርፉ ባለሙያዎችን በመመደብ ረገድም በመጠቃቀም ላይ ያዘነበለ እንጂ ከልብ ለአገር የሚሰራ ሰው አይገኝም፡፡
እውነት ዘርፉን ለማሳደግ ከተፈለገ አሉ አቶ አዮብ፤ ለዘርፉ ዕድገት ሰርተው ማሳየት የሚችሉና ቁርጠኝነቱ ያላቸው ባለሙያዎች የማፍራት ጉዳይ ቀዳሚ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ አገልግሎት ሰጪዎችም የሚሰጡት አገልግሎትና የሚጠይቁት ገንዘብ መመጣጠን አለበት፡፡ ቱሪስቶቹ የሚፈልጓቸውን አገልግሎቶች በቀላሉና በተሟላ መልኩ ማግኘት አለባቸው የሚል እምነት አላቸው፡፡
ባለፉት ሶስት ዓመታት በአገሪቱ የተከሰተው የጸጥታ ችግርና ቀደም ሲል በአገሪቱ ታወጀው የነበሩት ሁለት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች የቱሪዝሙን ዘርፍ እንቅስቃሴ አዳክመውት እንደነበር የሚያስታውሱት ደግሞ የቱር ኦፐሬትሮች ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ኪሮስ መሀሪ ናቸው፡፡ በአገሪቱ የጸጥታ ችግር ምክንያትም ብዙ የውጭ አገራት ለዜጎቻቸው “ወደ ኢትዮጵያ እንዳትሄዱ” የሚል የጉዞ እግድ ጥለው ነበር ይላሉ፡፡
ይሁንና ከለውጡ በኋላ አገራት ወደኢትዮጵያ እንዳይጓዙ ጥለዋቸው የነበሩት ክልከላዎች ተነስተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት፤ በአሁኑ ጊዜ ካለፉት ሶስት ዓመታት በተሻለ መልኩ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣው የቱሪስት ቁጥር ከፍተኛ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ አሁን የሚመጣው የቱሪስት ቁጥር የተሻለ ነው ባይ ናቸው፡፡ ይህ ማለት ግን አልፎ አልፎ ስጋት አይኖርም ማለት አይደለምለምሳሌ፤ በቅርቡ ቱሪስቶች ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ሲሄዱ ግጭቶች አጋጥመዋቸዋል፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች ካዩት ሁኔታም ተነስተው በኢትዮጵያ ሰላም ላይ የተዛባ ግንዛቤያቸውን ለሌሎች ቱሪስቶች ሊናገሩ ይችላሉ፡፡ ይህም በቱሪስት ፍሰቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ይኖረዋል፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ ግን በአሁኑ ጊዜ ካለፉት ሶስት ዓመታት የተሻለ የቱሪዝም እንቅስቃሴ መኖሩን ጠቅሰዋል፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ብዙ የቱሪዝም ሀብት ቢኖራትም የሀብቷን ያህል ተጠቃሚ አይደለችም፡፡ ምክንያቱም በዓለም ዝቅተኛ የቱሪዝም ኢንቨስትመንት ካላቸው አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ናት›› የሚሉት አቶ ኪሮስ፤ ስለዚህ ማህበሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ችግሮችን ለመፍታትና የዘርፉን ገቢ ለማሳደግ ጥረት እያደረገ ነው፡፡ ቱሪዝም ለዚች አገር ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጸኦ የሚያበረክት ስለመሆኑ በህብረተሰቡ፣ በአስፈጻሚና በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጭምር አስፈላጊው ግንዛቤ መፈጠር አለበት የሚል ሀሳብ አላቸው፡፡
በመንግሥት በኩል ደግሞ፤ ለቱሪዝም ዕድገት አመቺና ሊያሰራ የሚችል ፖሊሲ፣ ህግና መመሪያ ማዘጋጀትና ስርዓት መዘረጋት ያስፈልጋል፡፡ እንዲሁም ኢትዮጵያ በርካታ የቱሪስት መስህቦችና መዳረሻዎች ቢኖሯትም የቱሪስት መሰረተ ልማቱ በሚፈለገው መልኩ ባለመዘርጋቱ ፍሰቱ አነስተኛ ነው፡፡ ስለዚህ የቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎችን ማልማት ቀዳሚ ተግባር ነው የሚሆነው፤ በተመሳሳይ የኢንተርኔት፣ የስልክ፣ የመንገድ፣ የሆቴልና መሰል አገልግሎቶችን በጥራት ተደራሽ ማድረግ ይገባል፡፡ ስለዚህ የየአካባቢው ማህበረሰብ፣ መንግስትና የግል ባለሀብቱ በተቀናጀና ውጤት በሚያመጣ መልኩ መስራት ይኖርባቸዋል፤ ሲሉ ምክረ ሀሳብ ይሰጣሉ፡፡
ሌላው በኢትዮጵያ ውስጥ የፓርኮች አያያዝም የሚያረካ አይደለም፡፡ ለምሳሌ፤ አንዳንድ ብሄራዊ ፓርኮች የመጥፋት ስጋት ተደቅኖባቸዋል፡፡ ይህም ቱሪስት ለማስጎብኘት አስቸጋሪ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ በዚህ ረገድ ምክር ቤቱ ተቋቋመ እንጂ ወደ መሬት ወርዶ የሰራው ስራ ብዙም አይደለም፡፡ መንግስት ለዘርፉ ከጊዜ ወደ ጊዜ ትኩረት ቢሰጠውም የቅንጅት ችግር ጎልቶ ይታያል፡፡ ስለዚህ የተጠቀሱትን ችግሮች በመፍታት ቱሪዝምን በዘላቂነት ማሳደግ ይቻላል የሚል ሀሳብ አክለዋል፡፡
ስለዚህ ኢትዮጵያ ያሏትን ባህላዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ሀብቶች በመጠበቅ፣ በመንከባከብና በማበልጸግ የቱሪስትን ፍሰት መጨመር፤ ተጠቃሚነትንም ከፍ ማድረግ ይገባል፡፡ ለዚህም የቱሪስት መስህቦችን ማስተዋወቅ፤ ጎን ለጎንም የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ተገቢ ትኩረት የሚያሻው ይሆናል፡፡ ይህንንም ለማሳካት መንግስትና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ውጤት በሚያመጣ ስራ ላይ ማተኮር ይኖርባቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 24/2011
ጌትነት ምህረቴ