እውቁ ፈላስፋ ፕሌቶ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ375 አካባቢ በፃፈው ‹‹The Republic›› የሚል ስያሜ የሰጠው መፅሀፍ ላይ ‹‹ሶክሬተስ›› የተሰኘ ገፀ ባህሪ ከአቴናዊያን እና ከበርካታ የውጪ ዜጎች ጋር ስለ ፍትህ፣ ትክክለኛ መንግስትና ትክክል ስለሆኑና ስላልሆኑ ሰዎች ምንነት ሲወያይ ይነበባል። ይህ ታላቅ ሰው የደረሰው መፅሀፍ እስካሁን ከተፃፉ የፍልስፍና እና የፖለቲካ ፅንሰ ሀሳቦች ወደር የማይገኝለት በሚል የከፍታ ማማ ላይ የተቀመጠ ነው። ብዙዎችን በእውቀት ማእበል ያጥለቀለቀ፤ ያወያየ እንዲሁም ደስተኛ የመሆን ምንነት ላይ አበክሮ ትርጉም ለመፈለግ የባተተ የህይወት መንገድን የሚያሳይ ነው።
የፕሌቶ ‹‹ዘሪፐብሊክ›› በጣም ሰፊና ብዙ ገፆች ያሉት ውይይት ወይም በፈረንጅኛው አፍ ‹‹Socratic dialogue›› ሲሆን ለዛሬ በቀጣይ ለማወጋው ሀሳብ ጠቃሚ ነው ብዬ ያሰብኩትን አንድ ክፍል ወስጄ ሀሳቤን ለመሰንዘር እሞክራለሁ። በዚህ እሰጣ እገባ በበዛበት የፍልስፍና እይታ ውስጥ ሀሳብ ሲብላላና በየፈርጁ ሲሰደር እውቀት የሁሉም ችግሮች ቁልፍ መሆኑን እንገነዘባለን። በቀጣዩ ክፍል ይህን የሚያስረዳልልን የፕሌቶን ፅንሰ ሀሳብና አሁን ያለንበትን አገራዊ ውጥንቅጥ በጥቂቱ ተመልክቼ የግል አስተውሎት የታከለበት ሀሳብ ለመስጠት ልሞክር።
በ‹‹ዘሪፐብሊክ›› ላይ ‹‹The Allegory of the Cave›› ወይም ‹‹plato cave›› በሚል ፅንሰ ሀሳብ ዙሪያ በገፀባህሪነት የተሰየሙት ሶክራቲስ እና የፕሌቶ ወንድም ግላውኮን በአንድ ጉዳይ ላይ ሲወያዩ ያስነብባል። በዚህም ፈላስፋ ማለት ለዘመናት ከታሰረበት ዋሻ ውስጥ አምልጦ እንደወጣ እስረኛ ሲሆን ቀሪው የሚያየው ነገር ሁሉ ከዚህ ቀደም በህሊናው ካስቀመጠው ፍፁም የተለየ መሆኑን የሚያስቀምጥ ጉዳይ ላይ ይወያያሉ።
ፕሌቶ ‹‹ዘሪፐብሊክ›› ሶስት ከልጅነታቸው ጀምሮ በጨለማ ዋሻ ውስጥ ፊታቸውን ወደ ግድግዳው አዙረው የታሰሩ ሰዎችን እንድናስብ ይነግረናል። ከጀርባቸው ሁልጊዜም የሚነድ እሳት ያለ ሲሆን በእስረኞቹና በእሳቱ መሀል ደግሞ በዋሻው አካባቢ የሚኖሩ የመንደር ሰዎች ያልፋሉ። በዚህ አጋጣሚ እሳቱ የሰዎቹን እና የሚተላለፈውን ማንኛውንም ነገር እስረኞቹ ማየት በሚችሉት ግድግዳ ላይ ጥላ በመፍጠር እንዲያዩት ያደርጋል። በዚህ የተነሳም ለዘመናት የሚሰሙት ድምፅና የሚያዩት እውነት ሁሉ ከጥላው የሚወጣ መሆኑን ብቻ ይገነዘባሉ። ሶስቱ የዋሻው እስረኞች ‹‹እውነት›› ማለት እነሱ ከሚያዩትና ከሚንቀሳቀሰው ጥላ ውጪ እንዳልሆነ አምነዋል።
ከዘመናት በኋላ አንዱ እስረኛ ከታሰረበት ሰንሰለት ያመልጣል። ከዋሻው ውስጥ መውጣትም ይችላል። በዚህ ጊዜ ከእሳቱ በላይ ሌላ ብርሀን የሚሰጥ የተፈጥሮ ብርሀን (ፀሀይ) መኖሩን ይገነዘባል። ከዋሻው ሲወጣ ከተፈጥሮ ብርሀን ጋር ለመላመድ እና በትክክል ለማየት ተቸግሮ ነበር። ቀስ በቀስም ጥላው ብርሀኑ የሚፈጥረው አርቴፊሻል እውነት እንጂ ትክክለኛው ምስል ወይም ቁስ አለመሆኑን ይረዳል። ይህንንም ለማመን ጊዜ ይወስድበታል። በአጠቃላይ እድሜውን ሙሉ ሲያየው የነበረው እና እምነቱ ያደረገው የዋሻ ህይወት የተዛባ መሆኑን ይገነዘባል። አብሯቸው የታሰሩት ሁለት ሰዎች እርሱ የተረዳውን እውነት መመልከት እንዲችሉ በመጓጓትም ወደ ዋሻው ይመለሳል።
የሆነውን ነገር ለሁለቱ የዋሻ እስረኞች ይነግራቸዋል። ያየውን እና የተመለከተውን ከዛም ሲያልፍ ትክክል የሆነውን ነገር ሊያስረዳቸው ይሞክራል። ሆኖም ጓደኛቸው ማበዱን እንጂ ትክክል እንደሆነ ሊቀበሉት አልቻሉም። እውነት እነሱ ከሚያዩት አርቴፊሻል ብርሀን እና ጥላ ውጪ እንደሌለም አስረግጠው ይነግሩታል። ሁኔታውን ሳይቀበሉት ቀርተውም ከአጠገባቸው ዞር እንዲል ጫና ይፈጥሩበታል።
ምን እንረዳ?
የፕሌቶ የምናብ ዋሻ ‹‹allegory›› በርካታ ምሳሌዎችን ‹‹symbolism›› የያዘ ነው። ዋሻው በአርቴፊሻል እውነት ‹‹superficial physical reality›› ሲመሰል ከዚህ ባለፈም በ‹‹መሀይምነት›› እና በ‹‹አለማወቅ›› ይወከላል። አለማወቅ ደግሞ በይበልጥ በጭለማው ይወከላል። ምክንያቱም እስረኞቹ ከሚያዩት ጥላ ውጪ እውነተኛ ቁስ ወይም ተንቀሳቃሽ ነገር እንደሌለ እንዲያምኑ በመሆናቸው ነው። የታሰሩበት ሰንሰለት ደግሞ በአለማወቅ ወጥመድ መጠለፋቸውን እና ቀሪውን ዓለምና እውነት ማየት እንደተሳናቸው የሚያሳይ ነው። ከዋሻው ያመለጠው እስረኛ ደግሞ ከፍ ያለውንና ትክክለኛውን ‹‹the higher truth of ideas›› እውነት እንዲወክል ሆኖ የተቀረፀ ሲሆን ብርሀኑ ደግሞ ጥበብን እንዲወክል ተደርጎ ተቀርጿል።
አርቴፊሻሉን ብርሀን የፈጠረው እሳት እና ከጀርባው እንዲመላለሱ የተደረጉት ሰዎች ደግሞ ስልጣን ላይ ያሉ ፖለቲከኞችን፣ የመገናኛ ብዙሀን እና የማህበረሰቡን አመለካከት በሚፈልጉት መንገድ ደርዝ የሚያሲዙትን ግለሰቦች እንዲወክሉ ተደርገው ተቀርፀዋል።
ወደ ማህበረሰባችን አሁን ላይ ያጋጠመን እውነት ከላይ ያነሳነው የዋሻው ታሪክ ይመስላል። ሰዎች ትርክት በማዛባት ብዙሀኑን የህሊና እውር ለማድረግና ከራሱም ከወንድሙም ጋር ሲያላትሙት እንመለከታለን። የመገናኛ ብዙሀን ልክ እንደ አርቴፊሻሉ እሳት ለተከታዮቻቸው የሚሰብኩት ፕሮፓጋንዳ ከእውቀት እና ጥበብ ጋርዶታል። ጥላውን አይቶ ከግድግዳው ጋር ይጋጫል። ተፅዕኖ የሚፈጥሩ እና የገንዘብ አቅም ያላቸው ግለሰቦች ማህበረሰቡን ወደ ለምለሙ ሜዳ ሳይሆን ጥልቅ ወደ ሆነው ገደል ይመሩታል።
ፍሬውን ከገለባው ለመለየት መንሽ እንደሚያስፈልገን ሁሉ እውነቱን ‹‹ከተዛባው እውነት›› ለመነጠል ጥበብ ሊኖረው ይገባል። ሰንሰለቱ ጠፍሮ እንደያዛቸው የዋሻው እስረኞች ማህበረሰባችንን ጠፍሮ የያዘውን ‹‹አለማወቅ›› በጥሶ ለመውጣት የአንደኛውን እስረኛ ፈለግ መከተል ያስፈልጋል። እውቀትን መከተል እውነትን ማሳደድ ይኖርብናል። ነፃ የሚያወጣውን ጥበብ መሻት።
በፕሮፓጋንዳ እና መርዝ በተለወሰ ቃላቶች እያረሰረሱን እነርሱ ወደሚፈልጉት አቅጣጫ የሚወስዱንን ጥቂት ሰዎች ሳይሆን ማመን የሚኖርብን መርምሮ የሚያውቀውን መዝኖ የሚረዳውን ህሊናችንን ነው። ለዚህ ደግሞ እውቀትን መከተል ይኖርብናል። ምክንያቱም እውቀት እንጂ ጥቂቶች ነፃ አያወጡንም!!
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 5 /2012
ዳግም ከበደ