በህይወታቸው የገጠማቸው ተግዳሮት ተደጋ ጋሚና ተስፋ አስቆራጭ ቢሆንም እጅ አልሰጡም። ወደኋላ መለስ ብለው ያሳለፉትን ችግር ባስታወሱ ቁጥር ዓይናቸው እምባ ያቀርራል። ሆኖም በእል ህና አልሸነፍ ባይነት ሁሉን በበጎ ተመልክተው አሳልፈዋል። ይሄም ወደ ቀጣዩ የህይወት ምእራፍ የሚያደርሳቸውን መንገድ ከፈተላቸው እንጂ ከመንገድ አላስቀራቸውም።
ከአንድም ሶስት ጊዜ ተይዘው ሰባት ዓመት ተኩል ለእስር መዳረጋቸውን ያስታውሳሉ። በማረሚያ ቤት ቆይታቸው እስር ቤቶችን ለማሻሻል ያደረጉት ጥረት ሰዎች ባሉበት ቦታ ሁሉ በጎ ተግባራትን መፈፀም እንደሚችሉና ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ምንም ነገር እንደማያግዳቸው ያረጋግጣል። ለሰሩት ሥራ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ በማረሚያ ቤቱ ግቢ በስማቸው የተሰየመላቸው አደባባይ ምስክር ነው።
እኚህ ብርቱ ሰው እምብዛም በማይደፈሩትና ብዙዎች በማይገቡበት የሴቶችና ህፃናት ንፅህና መጠበቂያ ማምረት ሥራ ብቸኛው ኢትዮጵያዊ በመሆን ይፍጨረጨራሉ። ከውጪ የሚገቡ የሴቶችና ህፃናት የንፅህና መጠበቂያ ምርቶችን በአገር ውስጥ በማምረት ለተጠቃሚዎች ለማቅረብ ቀዳሚ ሆነው እየሰሩ ቢገኙም በውጭ ምንዛሪ እጥረትና በጥሬ እቃ አቅርቦት ችግር ምክንያት የፋብሪካቸው ህልውና ስጋት ላይ ጥሏቸዋል።
ለዛሬው ‹‹የህይወት እንዲህ ናት›› ዓምድ እንግዳችን አድርገን የመረጥናቸው የላይላክ ሴቶችና ህፃናት የንፅህና መጠበቂያ አምራች ድርጅት ባለቤት አቶ መሃመድ የሱፍ ናቸው። ከእሳቸው ጋር ያደረግነው ቆይታ እንደሚከተለው አሰናድተነዋል። መልካም ንባብ።
ልጅነትና ትምህርት
በአዲስ አበባ መርካቶ ልዩ ስሙ አደሬ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በ1940 ዓ.ም ይህችን ዓለም ተቀላቀሉ፤ አቶ መሃመድ የሱፍ። የአደሬ ብሄረሰብ የሆኑት የአቶ የሱፍ አሊ እና የወይዘሮ አይሻ እስማኤል አብራክ ክፋይ ለቤተሰባቸው ዘጠነኛና የመቁረጫ ልጅ ናቸው አቶ መሃመድ። እንደ መርካቶ ልጆች ሁሉ በልጅነታቸው ኳስና ብይ ተጫውተዋል፤ መርካቶን መስለው መሀል መርካቶ አድገዋል።
በወቅቱ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን የጀመሩት ሰለፊያ በሚባል የአረብኛ ትምህርት ሲሆን በመቀጠልም በወሰን ሰገድ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በልኡል መኮንን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እስከ አስረኛ ክፍል ድረስ ከዘለቁ በኋላ በብሄራዊ ንግድ ሥራ ትምህርት ቤት በመግባት ለአራት ዓመታት ተምረው በ1962 ዓ.ም በአካውንቲንግ ዲፕሎማ ተመርቀዋል። ከዛም አምሮፓ በሚባል ፎርድ መኪናና መለዋወጫ እቃ አስመጪ ካምፓኒ ውስጥ በሂሳብ ሠራተኛነት ተቀጥረው ለስምንት ዓመታት ማገልገላቸውን አጫውተውናል። የመን ግሥትም ሆነ የግል ተቀጣሪ መሆን አዋጪ አይደለም ብለው በማሰብ የራሳቸውን ሥራ መፍጠርን እንደ ጥሩ አማራጭ ወሰዱ።
ወደ ንግዱ ጎራ
መርካቶ የአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ሳትሆን የአገሪቱ ዋነኛ የንግድ መናኸሪያም ናት። በመርካቶ ብዙዎች ነግደው አትርፈዋል፤ ብዙዎችም ከስረው እጅ ሰጥተዋል። የመርካቶና አካባቢው ነዋሪ አብዛኛው ህይወት የተመሰረተው በንግድ ላይ ነው ። መርካቶ ተወልዶ፣ እዛ አድጎ፣ መርካቶ ገብቶ ማን ጦሙን ሊያድር ? መርካቶ ገብቶ ሥራ መች ጠፍቶ። መበርታት፣ መጠንከርና መስራት ብቻ ነው ወሳኙ።መርካቶ ሥራም ገንዘብም አለ።
በጊዜው በመርካቶ ውስጥ በንግድ ሥራ ታዋቂዎች ከነበሩት መካከል የአደሬ ብሄረሰብ መሆኑ ይነገራል። በአደሬ ብሄረሰብ ዘንድም ንግድ እንደ ባህል ይታያል። ለአቶ መሃመድም የቤተሰብ ተፅእኖ ብቻ ሳይሆን የመርካቶ የንግድ እንቅስቃሴ ከአደሬ ብሄረሰብ የንግድ ባህል ጋር ተዳምሮ ወደ ንግዱ ዓለም እንዲቀላቀሉ በር ከፍቶላቸዋል።
በተመረቁበት የሂሳብ ስራ ሙያ ቀደም ሲል ተቀጥረው ሲሰሩበት በነበረው የግል ድርጅት ውስጥ እየሰሩም አእምሯቸው አንድም ቀን ስለንግድ ሥራ ሳያስብ ውሎ አያውቅም። ከብዙ ማውጠንጠንና ማሰላሰል በኋላም በአንድ የንግድ ሥራ ላይ ቢሰማሩ ውጤታም ሊሆኑ እንደሚችሉ ከሃሳብ መቋጫ ላይ ይደርሳሉ። ያመጡት የንግድ ሃሳብ እምብዛም ያልተለመደ ቢሆንም በምፅዋ ወደብ አካባቢ የተከማቸና ተራራ የሚያክለውን በርካታ የጨው ሀብት ወደ ገንዘብ ሊቀየር እንደሚችል ገምተዋል። በወቅቱ የምፅዋ ወደብ ዝግ ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ በጨው ንግድ ሥራ መሰማራቱ ያን ያህል አዋጭ ነው ተብሎ የሚታሰብ ባይሆንም ይህንኑ የጨው ሃብት ወደአገር ውስጥ በማስገባት ለመሸጥ ቆርጠው ይነሳሉ።
የአሰብ ወደብም በተመሳሳይ ዝግ በመሆኑ በምፅዋ ላይ ተከማችቶ የሚገኘውን ጨው በዶላር በመግዛት ወደ ጅቡቲ ከላኩ በኋላ ከጅቡቲ በባቡር ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት በወቅቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ያመለክታሉ። ከቢሮው የተሰጣቸው ጥያቄ ‹‹ይህን ለማድረግ ይችላሉ ወይ?›› የሚል ነበር። ሆኖም ብዙ ሳይቆይ ጥያቄያቸው መልስ አገኘ። በመቀጠልም የንግድ ፍቃድ በመውሰድ በ1970ዎቹ መጨረሻ ላይ በምፅዋ የሚገኘውን ጨው በዶላር መግዛት ጀመሩ። ጨው በመርከብ በማስጫን ወደ ጅቡቲ እዛም በጆንያ አሽገው ወደ ኢትዮጵያ ያስገባሉ። ከጊዜ ወደ ጊዜም የጨው ንግዳቸው እየደራ ሄደ።
በጊዜው እርሳቸው ያቀረቡት ሃሳብ የተለየ በመሆኑ በጨው ንግድ እንዲሰማሩ በመንግሥት በኩል የተፈቀደላቸው ቢሆንም ውሎ አድሮ ግን ከሌሎች ነገዴዎች እንዴት ለእርሱ ብቻ ይፈቀዳል? የሚል ጥያቄ ማስነሳት ጀመረ። ከዚሁ ንግድ ዳጎስ ያለ ገቢ ማግኘት ሲጀምሩም እርሳቸው የጀመሩት የንግድ ሃሳብ በብዙዎች ዓይን ውስጥ ገባ፤ በመንግሥት ትእዛዝም ንግዱ እንዲቋረጥ ተደረገ።
አዲስ ምዕራፍ
ንግዱ ከተቋረጠ በኋላ ለጨው ግዢ ያወጡት ዶላር እንዲመለስላቸው ከፍተኛ ጥረት ካደረጉና ብዙ ውጣውረድ ካሳለፉ በኋላ ተመልሶላቸዋል። ይህም በህይወታቸው የገጠማቸው የመጀመሪያው ፈተና እንደነበር ያስታውሳሉ። በገጠማቸው ችግር ብዙም ያልተደናገጡት አቶ መሃመድ ከዚህ በኋላም በሌላ የንግድ እንቅስቃሴ ዳግም መሳተፋቸውን ቀጠሉ።
በ1982 ዓ.ም አሁንም በኢትዮጵያ ብዙም ባልተለመደውና ባልታወቀው የሴቶችና የህፃናት ንፅህና መጠበቂያ ቁስ ማምረት ሥራ ለመግባት ይወስናሉ። በከተማ አካባቢ መኖራቸው ደግሞ እንዲህ አይነቱን የንግድ ሃሳብ ለመድፈር የራሱን አስተዋፅኦ አበርክቶላቸዋል።
ከጨው ንግድ የተመለሰላቸውን ዶላር በመጠቀም ከሁለት ወዳጆቻቸው ጋር በመሆን በጥምረት የሴቶችና የህጻናት የንፅህና መስጫ ማምረቻ ማሽን ከጣሊያን ሀገር ለመግዛት ከስምምነት ላይ ይደርሳሉ። በስምምነታቸው መሰረት ማሽኑን ወደአገር ውስጥ አስገቡ። መንግሥት አዲስ አበባ ገርጂ አካባቢ በሰጣቸው መሬት ላይ የማምረቻ ቤት መገንባት ጀመሩ። ይሁንና በጥምረት ቢዝነስ መስራት ብዙም ያልተለመደ በመሆኑና ከወዳጆቻቸው ጋር ያለመግባባት በመፈጠሩ ነገሮች ወዳልታሰበ አቅጣጫ መጓዝ ጀመሩ። በወቅቱ እርሳቸውን ለማሳሰርም በርካታ ሙከራዎች እንደነበሩ ይናገራሉ። ቢሆንም በንግዱ ዓለም በተለይም በከተማው አካባቢ በአብዛኛው በመን ግሥትም ጭምር የሚታወቁ በመሆናቸው የተደረጉ ሙከራዎች ሁሉ ሳይሳኩ መቅረታቸውን ያስታውሳሉ።
የስርዓት ለውጥ
ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ሲመጣ ደግሞ ቀደም ሲል አብረው ሲሰሩ በነበሩ አጋራቸው በቅድሚያ ወንድማቸው ይታሰራሉ። በመቀጠልም እርሳቸው ማእከላዊ እስር ቤት እንዲገቡ ይደረጋል። በወቅቱ የታሰሩበትን ምክንያት ሊያውቁ ባይችሉም በመጨ ረሻ ግን አንደኛው የሥራ አጣማሪቸው በሰጡት የተሳሳተ መረጃ መሆኑን ይረዳሉ። በኋላ ላይም ወንድማቸው በእስር እንዲቆዩ ሲወሰን እርሳቸው ከአንድ ወር በኋላ መለቀቃቸውን ይገልጻሉ። ከሸሪኮቻቸው ጋር ያቋቋሙት ፋብሪካ ሥራውን ሳይጀምር ቆሞ ቀረ።
ከዚህ በኋላ ከጣሊያን አገር አዲስ ማሽን ከነጥሬ እቃው ገዝተው ወደአገር ውስጥ በማስገባት በአሁኑ መኖሪያ ቤታቸው በሚገኝበት ቃሊቲ በአዲሱ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ አማካኝነት ላይ ላክ የሴቶችና ህጻናት ንፅህና መጠበቂያ ማምረቻ አቋቋሙ።
ከእስር ቤት ከተለቀቁ በኋላ በተደጋጋሚ በስልክ የሚሰነዘርባቸው ማስፈራሪያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ሄደ። በዚህ ወቅት ወደ አሜሪካን ሀገር አቀኑ። እዛ ሆነው እቤታቸው ድረስ የፍርድ ቤት መጥሪያ ደብዳቤ መምጣቱን ሰሙ። ይሄንን ጉዳይ የሚያውቁ ብዙዎች ወዳጆቻቸው ወደ አገር ቤት ሲመለሱ ሊታሰሩ እንደሚችሉ ቢያስጠነቅቋቸውም ምንም አይነት ወንጀል እንዳልሰሩ በመተማመን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ወሰኑ።
ከአሜሪካን አገር እንደተመለሱ ከግል ጠበቃ ቸው ጋር በመሆን ወደ ልዩ አቃቤ ህግ ቀረቡ። ለምን እንደተፈለጉ ማብራሪያ እንዲሰጣቸውም ጠየቁ። ይሁንና ማንም እንዳልፈለጋቸው ተነገራ ቸው። ሆኖም ግን እዚሁ ትቆያላችሁ ከተባሉ በኋላ ወደ ሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ ተወሰዱ። በወንጀል የሚያስጠይቃቸው ምንም አይነት ድርጊት ሳይፈፅሙ በፖሊስ ጣቢያው ቀናቶች ተቆጠሩ። ሳምንታት ካለፉ በኋላ በፖሊስ አዛዡ ቢሮ እንዲቀርቡ ተደረገ። የፖሊስ አዛዡም ምንም አይነት ጥፋት እንደሌለባቸውና ገንዘብ ካልሰጠህ በሚል እንደታሰሩና ዓቃቤ ህግ በዋስ እንደሚያስወጣቸው ነገራቸው። ይሁንና ከእስር መውጪያ ደብዳቤ ስላልደረሳቸው ተመልሰው ወደ እስር ቤት ለመግባት ተገደዱ። አቃቢ ህግ በሃያ ሺ ብር ዋስ እንዲለቀቁ የወሰነ ቢሆንም በገንዘቡ ጉቦ ሰጥቶ ሊወጣ ነው በሚል ምክንያት ከእስር አይለቀቅም የሚል ትእዛዝ ከበላይ ተላለፈ።
በማረሚያ ቤት – ልማት
በእስር መቆየታቸውን ሲያውቁ ተስፋ ያልቆረጡት አቶ መሃመድ የእስር ቤቱን ኃላፊዎች ፍቃድ በመጠየቅ የሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ እስር ቤት ያለበትን ሁኔታ ለማስተካከል ቆርጠው ተነሱ። ፍቃድ በማግኘታቸውም የእስር ቤቱን ምድረግቢ በአጠቃላይ የፀረ ተባይ መድኃኒት አስረጩ። በእያንዳንዱ የእስር ቤት ክፍሎችም ሰሌን እንዲነጠፍ አደረጉ። የፕላስቲክ ቱቦዎችን በራሳቸው ወጪ በማስገዛትና ውሃ በመሳብ የእስር ቤቶቹ ክፍሎችና መጸዳጃ ቤቶች እንዲፀዱ ፣ እስር ቤቱ ንፁህና ለታራሚዎች ምቹ እንዲሆን ለማድረግም ሞከሩ።
አብዛኛዎቹ እስረኞች ወደ ሆለታ ሲወሰዱ እርሳቸው ግን እዛው እንዲቆዩ ተደረገ። በዚህ ጊዜም ጓደኞቻቸው እስር ቤት ድረስ በመምጣት ከእስር ለመለቀቅ ጉቦ መክፈል እንዳለባቸው ይነግሯቸዋል።እርሳቸው ግን ሰባራ ሳንቲም እንደ ማያወጡና ከአቋማቸውም ፍንክች ሳይሉ በእስር እንደሚቆዩ ያሳውቃሉ። ከዛም ሆለታ እስር ቤት ተወሰዱ ሆኖም አቋማቸውን ሳይለውጡ ለሁለት ዓመታት በዛው ቆዩ።
በእዛ የእስር ቤት ቆይታቸው እንደልማዳቸው ከማረሚያ ቤቱ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት ጥረቶችን አድርገዋል። የውሀ አቅርቦት ያልነበረውን
ማረሚያ ቤት አርባ ሜትር ቱቦ በማዘርጋት የገላ መታጠቢያና የመጠጥ ውሃ ማሰራታቸውን ያስታውሳሉ። በቀጣይም ከሆለታ ወደ ቃሊቲ እስር ቤት እንዲመጡ ተደረገ።
“ግቢው ጨለማና እስረኞች የሚታሰሩባቸው ክፍልችም ምቹ አይደሉም።ስለዚህ ይሄንን ማስተካከል አለብኝ ብዬ በማመን ለማስተካከል እንድችል ኃላፊዎችን ፍቃድ ጠይቄ ይሁንታ አገኘሁ። በእያንዳንዳቸው እስር ቤቶች ውስጥ መፀዳጃ ቤቶች ገነባሁ። የእስር ቤቱ ግቢ ረግረጋማ በመሆኑም ከእስረኞች ጋር በመተባበር ግቢው ሙሉ በሙሉ ቀይ አሸዋ እንዲነጠፍበት አድርጌያለሁ። ” ይላሉ።
በማረሚያ ቤቱ ውስጥ የሚያደርጉትን የልማት ሥራ በማጠናከርም ትምህርት ቤት፣ መፅሃፍት ቤትና የእስረኛ ኮሚቴ ቢሮ በአብዛኛው ከራሳቸው ገንዘብና በራሳቸው ተነሳሽነት ጥሩ የሚባል ሥራ መስራታቸውን ይናገራሉ። የእስር ቤቱን ምድረ ግቢ በአበባና በሌሎች እፀዋቶች የማስዋብ እንዲሁ አሻራቸውንም አሳርፈዋል። ቴሌቪዥን በሁሉም ክፍሎች እንዲዳረሱ አድርገዋል። እስረኞችን ለመጠየቅ የሚመጡ ቤተሰቦች የሚያርፉበት ትልቅ አዳራሽም አስገንብተዋል። የፍተሻ ቦታዎችንም አስተካክለዋል። በአጠቃላይ እስር ቤቱ ሥርዓትና መልክ እንዲይዝ ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን ይናገራሉ።
አቶ መሃመድ ከእስር የሚወጡበትን ጊዜ በየጊዜው ቢጠይቁም ጠብቁ ከማለት ውጪ ያገኙት ምላሽ አልነበረም። በኋላ ላይ ግን በክሱ ላይ ያላደረጉትን ነገር አደርጋችኋል በማለት የሃሰት ክስ በፍርድ ቤት ይከሰሳሉ። የክሱ ውሸትነት በመረጋገጡም ከሰባት ዓመት ተኩል ቆይታ በኋላም በነፃ ተለቀቁ። በወቅቱ አብረዋቸው የነበሩ ሌሎች ታራሚዎች ትልቅ ዝግጅት አድርገው በስማቸው አደባባይ በማረሚያ ቤቱ ቅጥር ግቢ በመስራትና በመሰየም ለእርሳቸው ያላቸውን አክብሮት አሳይተዋል።
ዳግም መነሳት
ያለ ሥራ መቀመጥ እረፍት የሚነሳቸው አቶ መሃመድ ከዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ በኋላም ምን መስራት እንዳለባቸው ማሰብና ማውጠንጠን ይጀምራሉ። ቀደም ሲል ቃሊቲ ያቋቋሙት ላይላክ የተሰኘው የሴቶችና የህፃናት ንፅህና መጠበቂያ ፋብሪካ ቆሞ ስለነበር በፊት ከነበራቸው ልምድ በመነሳት የሴቶችና ህፃናት ንፅህና መጠበቂያ ቁሶችን በአዲስ መልኩ ለማምረት ወደ ጥናት ገቡ። በባለሙያ አስጠንተው ካጠናቀቁ በኋላም ቀደም ሲል የነበራቸውን ንብረት ሁሉ በመሸጥ ይህንኑ ምርት የሚያመርት በአሜሪካውያን ደረጃ የተሰራ ማሽን ወደ አገር ቤት አስገቡ።
ላይላክ የሴቶችና ህፃናት ንፅህና መጠበቂያ ማምረቻ ድርጅት በሚል ስያሜ በ2005 ዓ.ም በ100 ሚሊዮን ብር ካፒታል ለሶስተኛ ጊዜ አቋቁመዋል። ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ፋብሪካው ሙሉ በሙሉ ወደማምረት ሥራ መግባቱንም ነው የሚናገሩት። በአሁኑ ወቅትም 49 ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር ችለዋል። ከነዚህ ውስጥ 42 በመቶ ያህሉ ሴቶች ናቸው።
አቶ መሃመድ ከብዙ ውጣውረድ በኋላ ፋብሪካውን ዳግም በማቋቋም በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባውን የህፃናትና ሴቶች ንፅህና መጠበቂያ በአገር ውስጥ እንዲመረትና በርካቶችም እንዲጠቀሙበት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ሆኖም ግን አሁንም እንቅፋቶች እንዳልተለዩዋቸው ይጠቅሳሉ።
የዛሬው እንቅፋት
አቶ መሃመድ የንፅህና መጠበቂያ ማምረቻ ማሽኑን ወደአገር ውስጥ ለማስገባት ከአንድ ዓመት በላይ ፈጅቶባቸዋል። ማሽኑ ወደፊት የሚሻሻሉ ነገሮች ካሉ ሊስተካከል የሚችልና ገና ጥቅም ላይ ያልዋሉ ቴክኖሎጂዎችን የያዘ በመሆኑ ምንም አይነት ቅሬታ አይሰማቸውም። ይህ ሁሉ ተሟልቶ ግን በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ጥሬ እቃዎችን ወደ አገር ውስጥ ማስገባት ባለመቻላቸው ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ማምረት እንዳልቻለ ይገልፃሉ።
ማሽኑ በደቂቃ 500 የህፃናት እና 600 የሴቶች ንፅህና መጠበቂያዎችን የማምረት አቅም እንዳለው የሚናገሩት እንግዳችን ይህም በአንድ ፈረቃ ቢሰራ በዓመት እስከ 72 ሚሊዮን የህፃናት እና 84 ሚሊዮን የሴቶች ንፅህና መጠበቂያዎችን የማምረት አቅም እንዳለው ያሳያል። ይሁን እንጂ ማሽኑ የታሰበውን ያህል ለማምረት ወደ ሃያ አይነት የጥሬ እቃዎች ያስፈልጉታል። ጥሬ እቃዎቹ በአብዛኛው የሚገባው ከአሜሪካን፣ ከጃፓን፣ ቻይናና ሆንግኮንግ ቢሆንም ዛሬ ላይ ለማስገባት አቅም እንዳነሰ ያስረዳሉ።
በመጀመሪያ ዙር ጥሬ እቃዎችን ለማስገባት አስፈላጊው ጥረት ሁሉ ተደርጓል። ጥሬ እቃው ለምርት ሙከራ ካለቀ በኋላ ለሁለተኛ ዙር ለማስገባት ግን አቅም አጥሯል። በዚህም ምክንያት ማሽኑ ማምረት የሚችለውን አቅም መጠቀም አልተቻለም። የፋብሪካ ማሽነሪ መለዋወጫ እቃዎችም በመበላሸት ላይ ይገኛሉ። ይህንኑ የአቅም ክፍተት በባንኮች በኩል ለመፍታት ጥረት ቢደረግም ባንኮቹ ይህን ግዙፍ ፋብሪካ እያዩ፤ የማምረት አቅም እንዳለውና በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ወጪውን መክፈል እንደሚችል እያወቁ የመስሪያ ካፒታል ብድር ለማግኘት ጥረት ቢደረግም አልተሳካም። ሆኖም ግን በመንግሥት በኩል ለእንደዚህ አይነት ግዙፍ ፋብሪካዎች ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋል።
ለኢትዮጵያ በየዓመቱ ከአንድ ቢሊዮን በላይ የሴቶችና ህፃናት ንፅህና መጠበቂያ ምርት እንደሚያስፈልጋት በተለያዩ ጊዜያት በመንግሥት መነገሩን የሚያስታውሱት አቶ መሃመድ፤ ይህን ያህል ብዛት ያለው የንፅህና መጠበቂያ ምርት ለማምረት ምን ያህል ፋብሪካዎች በአገሪቱ መኖር እንዳለባቸው ከግምት ውስጥ የገባ አይመስልም ይላሉ። ይህን ፍላጎት ለማሟላት መንግሥት በቅድሚያ ሀገር በቀል ባለሃብቶችን መደገፍና ማበረታታት እንደሚገባውም ያሳስባሉ።
ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ቢሰራ ስምንት ሚሊዮን ዶላር በዓመት ያስፈልገዋል። ይህም የፋብሪካውን አቅምና ለአገሪቷም የከፍተኛ የገቢ ምንጭ መሆኑን ያሳያል። ይሁንና ፋብሪካው ጥሬ እቃዎቹ ሳይቋረጡበት መስራት ይጠበቅበታል። ፋብሪካው ቢያንስ በየአራት ወሩ የአንድ ሚሊዮን ዶላር ጥሬ እቃዎችን ቢያገኝ በሙሉ አቅሙ ማምረት ባይችልም እንኳን ሥራውን እንዳያቆም እንደሚረዳውም ነው አቶ መሃመድ የሚገልፁት።
የገንዘብ ፣ንግድና ኢንዱስትሪ እንዲሁም ጤና ሚኒስቴሮች ሴቶችን ለመርዳት አንድ መቶ ሃያ ሚሊዮን የሴቶች ንፅህና መጠበቂያ ምርቶች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ጠይቀው እንደነበር አቶ መሃመድ ያስታወሱ ሲሆን ምርቶቹን የሚያመርቱ ፋብሪካዎች በአገር ውስጥ እያሉ ምርቶቹ ከቀረጥ ነፃ መግባት እንደማይኖርባቸውና በአገር ውስጥ ምርቱን የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ለምርቱ የሚያስፈልጉ ጥሬ እቃዎችን በነፃ በእንዲያስገቡ መገለፁ መልካም መሆኑን ይጠቅሳሉ።
መረዳዳት ኢትዮጵያዊ ባህል
ከቤተሰብም ባለፈ አቶ መሃመድ በአካባቢቸው ላሉና እርዳታ ለሚሹ በርካታ ድርጅቶች ድጋፍ በማድረግ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን በመወጣት ላይ እንደሚገኙም ይናገራሉ። ከነዚህ ውስጥም ስለእናት የሴቶችና ህፃናት በጎ አድራጎት ድርጅት፣ ሜቄዶኒያ የአረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን መርጃ ድርጅት፣ አበበች ጎበና የህፃናት ክብካቤና ልማት ማህበር እንዲሁም ሌሎችንም በመጎብኘት ሁለት ሚሊዮን ብር የቁሳቁስ እና የገንዘብ ድጋፍ እንዳደረጉ ይጠቅሳሉ።
ላለፉት ሁለት ዓመታት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አቅም ለሌላቸው ወላድ እናቶችና ለህጻናቶች የንፅህና መጠበቂያ በቋሚነት ከ10 ሺህ እስከ 40 ሺህ ብር የሚደርስ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ይናገራሉ። በዚሁ ሆስፒታል የህክምና ትምህርት የሚከታተሉና የንፅህና መጠበቂያ የመግዛት አቅም ለሌላቸው አንድ መቶ ሃምሳ ሴት ተማሪዎችም ለዘጠኝ ወር የሚሆናቸውን የሴቶች ንፅህና መጠበቂያ በነፃ እንዲሰጣቸው አድርገዋል። በቃሊቲ አካባቢም ለህዝበ ሙስሊሙ መስጂድ በራሳቸው ወጪ ማሰራታቸውን ገልጸውልናል።
በሀገራችን አጋጥሞ በነበረው ግጭት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ100 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን ያስታውሳሉ። በተለይም ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በአማራ ክልል ለተፈናቀሉ ዜጎች የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውን አንስተዋል ። አቅም ገድቧቸው እንጂ ብዙ ቢያደርጉ፤ የተቸገረን ሁሉ ቢጎበኙ ምንኛ ደስ ባላቸው ነበር።
የቤተሰብ ክብካቤ
በአደሬ ብሄረሰብ ባህል መሰረት ትዳር የሚመሰረተው በቤተሰብና በትውውቅ በመሆኑ አቶ መሃመድም ትዳር መመስረት እንዳለባቸው በቤተሰብ ደረጃ ስለተነገራቸው ከባለቤታቸው ወይዘሮ መርያ መሃመድ ጋር በ1993 ዓ.ም ጋብቻ መፈጸማቸውን ይጠቅሳሉ። ለባለቤታቸው ከፍ ያለ ክብርና ፍቅር አላቸው። በአስራ ዘጠኝ ዓመት የትዳር ቆይታቸውም አንድ ሴትና አንድ ወንድ ልጆችን ማፍራት ችለዋል።
ወይዘሮ መርያ ከቤት ውስጥ ባለፈም በፋብሪካው ውስጥ ኃላፊነት በሚጠይቅ ቦታ ላይ በትጋት ሥራዎችን በማከናወን ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸው ይናገራሉ። እርሳቸው በሌሉባቸው ጊዜያት የእርሳቸውን ሥራ በመተካት ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ። ችግሮች ሲያጋጥሙ እንኳን እርሳቸውና ባለቤታቸው በመነጋገርና በመረዳዳት እንደሚፈቱም ነው ያጫወቱን።
በቢዝነስ ውስጥ የተሰማሩ ሰዎች ከሥራቸው አንጻር ለቤተሰብ የሚሰጡት ጊዜ ያነሰ ነው ተብለው የሚታሙ ቢሆኑም እርሳቸው ግን ባገኙት ጊዜ ሁሉ ከቤተሰባቸው ጋር ጥሩ ጊዜያትን እንደሚያሳልፉና ልጆቻቸውንም ከትምህርት ቤት ከማምጣት ጀምሮ በማስጠናት ፣ እንደ አባት ብቻም ሳይሆን እንደ ጓደኛ በመቅረብ ይንከባከቧቸዋል።
እንደማጠቃለያ
ከህይወት ውጣ ውረድ ተለይተው የማያውቁት አቶ መሃመድ ፈተና ሲገጥም በበጎ ማየትና ለመፍትሄው በቅንነትና በሀቅ መትጋት እንደሚገባ ለብዙዎች ይመክራሉ። ሰዎች ከመጠን በላይ ሀብት አለኝ ብለው መኮፈስን ሆነ የለኝም በሚል አንገታቸውን መድፋት እንደማይገባቸው ይገልፃሉ። ሰዎች ምንም አይነት እምነት ይኑራቸው ጥንካሬ ካላቸው ከችግር መውጣት እንደሚቻል የራሳቸውን ተመክሮ በማንሳት ይመክራሉ።
አሁን በመንግሥት ደረጃ ያሉ ፖሊሲዎች ጥሩ የሚባሉ ቢሆኑም ታች ሲወርድና በአፈፃጸም ደረጃ ብዙም የሚተባበር ሰው ባለመኖሩ የቢዝነስ ዘርፍ መሳተፍ በጣም ተስፋ አስቆራጭና አስቸጋሪ መሆኑን ይጠቅሳሉ።በቅንነት የውስጥ ችግርን የሚረዳ አካል እንደሌለም ያብራራሉ። በዚህ ረገድ መንግሥት ለባለሃብቶች የሚያደርገው ድጋፍ ወሳኝ መሆኑንም ይጠቅሳሉ።
አቶ መሃመድ ተስፋ ሳይቆርጡ እዚህ ደርሰዋል። አሁንም በየአቅጣጫቸው ተጨማሪ ሥራዎችን በመስራት ከራሳቸው አልፈው ለወገን ለመትረፍ ያልማሉ። አሁን ያሉባቸውን ችግሮች ለመቅረፍም በየመንግሥት ቢሮ ደጃፎች ላይ መሄዳቸውን አላቆሙም። ሰሚ ቢያጡም አንድ ቀን የሚሰማኝ አይጠፋም በሚል ውትወታቸውን ቀጥለዋል። ይሁንና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንን የመሳሰሉ አንዳንድ የመንግሥት ተቋማት ተስፋ ከመቁረጥ ወደ ተስፋ ማለምለም ስለወጧቸው በዚህ አጋጣሚ ማመስገን እንደሚፈልጉ ነግረውናል። እኛም “ይኸው ምስጋናው” ብለናል።
ለአቶ መሃመድ የሱፍ ቀሪ የህይወትና የስኬት ዘመን እየተመኘን ተሰነባበትን፤ ሰላም!
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 5 /2012
አስናቀ ፀጋዬ