በሀገራችን በርካታ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ቅርሶች ይገኛሉ። ነገር ግን በሚገባ ባለመንከባከባችንና ባለማስተዋወቃችን ማግኘት ያለብንን ጥቅም ካለማ ግኘታችንም በላይ ሀገራችን የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤት መሆኗን ሳናስተዋውቅ ቀርተናል። ጉዳዩ በሚመ ለከታቸው አካላት የተሰጣቸው ትኩረትም እምብዛም አይደለም። በርካታ ሀገሮች እንደ ሀገር ተመስርተው ሳይታወቁ ኢትዮጵያ ከመታወቅም በላይ ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎችን ሰርታለች። አንዳንድ ሀገሮች ታዋቂ ጥንታዊ ለቅርስነት የሚበቃ ቅርስ ሳይኖራቸው እንዳላቸው ተደርገው ታውቀዋል። ምክንያቱ ያሏቸውን ጥቂት ቅርሶችን በመንከባከባቸውና ለማስተዋወቅ በመጣራቸው ነው።
በአንፃሩ ኢትዮጵያ ብዙ ሳትሰራ ያሏትን ቅርሶች በትንሹ በማስተዋወቅ ብቻ ከዘርፉ ብዙ መጠቀም ስትችል፤ ለቅርሶቿ ትኩረት በመነፈጉ ተጠቃሚ ሳትሆን ኖራለች። በቀላሉ ለቅርሶቻችን እድሳት እያደረግን ቱሪዝምን የሀገራችን ኢኮኖሚ ዋልታ ማድረግ ባለመ ቻላችን የእድገት ጎዳና እንደ ሰማይ እርቆን ይገኛል።
በማደግ ላይ ያሉ ሀገሮች ሳይቀሩ ኢኮኖሚያቸውን በግብርና ከመደገፍ ወጥተው ቱሪዝምን የኢኮኖሚያቸው የጀርባ አጥንት አድርገዋል። ኢትዮጵያ ያሏትን ቅር ሶች የሚያክል ጥንታዊ ቅርስ የሌላቸው ሀገሮች ኢኮኖሚያቸው በቱሪዝም ላይ የተመሰረተ ነው። በሀገራችን ከቱሪዝም ዘርፍ የሚገኘው ገቢ እጅግ አነስተኛ እና የሥራ እድልን ከመፍጠር አንፃር ጉልህ ሚና እየተጫወተ አይደለም።
ዘርፉን ለመቆጣጠርና ለመከታተል በፌዴራልም ይሁን በክልል ደረጃ የተቋቋሙ መስሪያ ቤቶች ሥራቸውን በሚጠበቅባቸው ልክ ሰርተዋል ለማለት አያስደፍርም። ይህ ደግሞ የውጭ ሀገር ዜጋ ይቅርና የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችም ሳያውቋቸው ተደብቀው የሚኖሩ ቅርሶች በርካቶች እንዲሆኑ አድርጓል።
በተለይ ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ብዙ ቅርሶችን በውስጧ ይዛለች፤ ነገር ግን ከጊዜ ብዛት የተነሳ አደጋ ተጋርጦባቸው ይገኛሉ። ከነዚህም ውስጥ በጣና ሀይቅ ውስጥና በጎርጎራ የሚገኙ ገዳማት በጉዳት ላይ ካሉ ቅርሶች መካከል በከፍተኛ ሁኔታ የአደጋው ሰለባዎች ናቸው። ገዳማቶች እራሳቸውን ከማስተዳደር አልፈው ለሀገር የሚተርፉ ቢሆንም ሀብታቸውን እንዲጠቀሙ እርዳታ ስላልተደረገላቸው በድህነት ውስጥ ይገኛሉ።
ገዳማቱ ቅርሶቻቸውን የሚያስጎበኙበት የመጽሐፍት መደርደሪያ የላቸውም፣ እድሳት አልተደረገላቸውም፣ በተደጋጋሚ ተዘርፈዋል፣ በርካታ የብራና መጽሐፍትን ከጠላት ለመከላከል በማለት በመሬት ውስጥ ተቀብረዋል፣ እንዲሁም ለጎብኚዎች አመች ባለመሆናቸውና በመሳሰሉ ችግሮች ገቢ እያገኙ አይደለም። አንዳንድ ገዳማቶች ላይ ደግሞ ከቋንቋ ጋር ተያይዞ ችግሮች ይስተዋላሉ። መንግሥትም ይህን ችግር ለመቅረፍ አንድም እርምጃ ባለመራመዱ ችግሮች በብርሃን ፍጥነት ጉልበት እያበጁ ተጠናክረው ቀጥለዋል።
በጎርጎራ አካባቢ ከሚገኙ ገዳማቶች መካከል አንዷ ደብረሲና ማርያም አንድነት ገዳም ተጠቃሽ ናት። ከተመሰረተች 700 ዓመታትን አስቆጥራለች። ለእይታ ማራኪና የበርካታ ታሪክ አካል ብትሆንም ከችግር ሊታደጋት የሚችል አካል አላገኘችም። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ችግሮች ተደራርበው ህልውናዋን እየተገዳደሯት ይገኛሉ። የተጋረጠባት ችግር ከአካባቢው ምዕመናንና አስተዳዳሪ በላይ ነው። ገዳማቷ ከራስዋ አልፋ ለሀገር የሚጠቅም ሀብት ቢኖራትም እራስዋን ከማስተዳደር ይልቅ እርዳታን ጠባቂ ሆናለች። በተደጋጋሚ በጀልባ እየታገዙ በሚዘርፉ ሌቦች በርካታ ጊዜ ተፈትናለች፤ የተወሰኑ ቅርሶችም ተዘርፈውባታል። ከጥቂት አባቶችና ምዕመናን በስተቀር እንደ እድሜ ጠገብነቷ የሚያስታውሳት፣ የሚያውቃትም ሆነ እድሳት ያደረገላት የመንግሥት አካል የለም። በመሆኑም የቱራስትን ዓይን እየሳበች አይደለም።
በጣና ሀይቅ ደሴቶች፣ በጎርጎራና አካባቢዋ በሚገኙ ቀደምት ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት የሥልጣንን በትር የጨበጡ የነገስታትን አፅም፣ እልፍ ጉዳዮች የተወሰኑባቸው ቁሳቁሶች፣ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተሰባሰቡ ውድ የታሪክ ቅርሶች ይገኙበታል። እነዚህ ቅርሶች ለአካባቢው ብቻ ሳይሆን የሀገራችንን ቀደምት የታሪክ ምስጢር መፍቻ ቁልፍ ናቸው። የታሪክና የአርኪዮሎጂ ተመራማሪዎች የጥናት አቅጣጫቸውን ወደ አርባ አራቱ ጎርጎራ አካባቢ ቢያተኩሩ አዳዲስ ታሪኮችን ለሀገራችን ማስተዋወቅ ይችላል። ጎብኚዎችንም መሳብና የዘርፉ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ አይነተኛ አማራጭም ከመሆኑ በላይ የሥራ እድልን መፍጠር ይቻላል።
44ቱ ጎርጎራ
ከ700 ዓመት በፊት ማለትም በ13ኛው ክፍለ ዘመን የጎርጎራ ደብረሲና ማርያምን ጨምሮ በርካታ ገዳማት በመኖራቸው የተነሳ አርባ አራቱ የሚል ስያሜ ወጥቶለት እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ። ብዙዎቻችን አርባ አራቱ የሚል ቃል ስንሰማ ቀድመን በአይነ ህሊናችን የምናስበው ጎንደር ከተማ ነው። እርግጥ ነው፤ በጎንደር ከተማ አርባ አራቱ ይገኛል። ምክንያቱም አፄ ፋሲለደስ ጎንደር ከተማ የሀገሪቱ መናገሻ ለማድረግ በንግስና ዘመናቸው ካስገነቧቸው ህንፃዎች ባሻገር በርካታ አብያተ ክርስቲያናትንና ገዳማትን በጎንደርና አካባቢዋ ማሰራታቸው ነው። ነገር ግን ቀደም ሲል ማለትም ከፋሲለደስ የንግስና ዘመን ከ300 ዓመታት በፊት በአፄ አምደ ጽዮን ዘመን መንግሥት ከ13ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በጎርጎራ ከተማና አካባቢዋ በተለይ በጣና ሀይቅ ውስጥ በሚገኙ ደሴቶች በርካታ ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናት በመሰራታቸው አካባቢው አርባ አራቱ ጎርጎራ እየተባለ ይጠራ እንደ ነበር ታሪክ ያትታል።
ከአርባ አራቱ ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናት መካከል አብዛኛዎቹ በ16ኛው ክፍለ ዘመን ጠፍተዋል። የተወሰኑ ገዳማት ዘመን ቢሻገሩም ከተወሰኑ አሥርት ዓመታት በፊት ሀገራችን ባስተናገደቻቸው ተደጋጋሚ ጦርነቶች የተነሳ ወድመዋል። እንደ ደብረሲና ማርያም አንድነት ገዳም ያሉት ደግሞ በርካታ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ችግሮችን መቋቋም ቢችሉም እድሳት ተነፍገው በዝናብና ጸሐይ እየተፈተኑና እየወደሙ ይገኛሉ።
ደብረሲና ማርያም አንድነት ገዳም
ገዳሟ በሳር የተከደነች ናት። በዚህ አካባቢ አርባ አራቱ ጎርጎራ ተብለው ከሚጠሩት ውስጥ በ1312 ዓ.ም የተመሰረተችው ደብረሲና ማርያም አንድነት ገዳም አንዷ ናት። በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት ደብረሲና ማርያም ህዳር 21 ቀን 2012 ዓ.ም 700ኛ ዓመት የምስረታ በዓሏን በደማቅና በልዩ ሁኔታ ተከብሯል። ከባህርዳር በጣና 78 ኪሎ ሜትር፤ ከጎንደር በአዘዞ 64 ኪሎ ሜትር ላይ ትገኛለች። እኛም በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ግብዣ በስፍረው ተገኝተን ለመጎብኘት ታድለናል፤ በረጃጅሞቹ ዛፎች፣ በፓፓያና ማንጎ የተሸፈነው አካባቢ በአይናችን እያየን የወፎችን ዝማሬ እያደመጥንና ንጹህ አየር እይተነፈስን አድናቆታችንን ቀጠልን። በወቅቱ ይሄንን የሰሩትን መለስ ብለነ ስናደንቅ የአሁኑን ደግሞ እንድንወቅስ እድል ከፍቶልናልና ራሳችንን ወቀስን። ግን ደግሞ ዛሬም ቀን አለና አስበልጠን ልናስውበው፣ የቱሪስት መስህብ ልናደርገው እንደምንችል ሳስብ ከወቀሳዬ ታቀብኩ።
ደብረሲና ማርያም አንድነት ገዳምን ያሰሯት የአፄ አምደ ጽዮን የጦር አዛዥ የሆነው ኤስድሮስ የሚባል ሰው ነው። የጦር አዛዡ ኤስድሮስ በጎርጎራ አካባቢ የሚያስቸግሩ ሽፍቶችን በመደምሰስ ህዝቡ በሰላም እንዲኖር፣ ለሀገራቸው የሚጠበቅባቸውን እንዲገብሩና ቤተ አይሁዶችን ወንጌል በማስተማር እንዲጠመቁ ካደረገ በኋላ ደብረሲና ማርያምን አሰርቷል። የኤስድሮስ ሀገር መንዝ ሲሆን ልዩ ቦታዋ ደግሞ ደብረሲና ትባል ነበር። የቤተ ክርስቲያኗን ስምም ደብረሲና በማለት በሀገሩ ሰይሟታል።
ደብረሲና ማርያም በጣና ሀይቅ ዳርቻ የተመሰረተች በመሆኗ የጎንደር ነገስታት መዳረሻ እንደነበረች ይነገራል። ብዙ ነገስታቶችም ሃይማኖታዊ ተግባራትን ከመፈፀም በተጨማሪ በየጊዜው እድሳት ያደርጉላት ነበር። የአጼ ሱስንዮስ ልጅ የሆነችው መለኮታዊት ወደ ደብረ ሲና መጥታ ከሀይቁ ተጠምቃ ከነበረባት ደዌ ተፈውሳለች፡ እቴጌ መለኮዊት ከበሽታዋ በመዳኗ ‹‹ለደብረሲና ምን ላድርግላት›› ብላ ሊቃውንቱን አማከረች። እነሱም ቤተክርስቲያኗ የግድግድ ስዕል የላትም፤ አሰሪላት አሏት።
ትእዛዙን በመቀበል በወቅቱ ጎጃም ውስጥ በስዕል ችሎታቸው የሚታወቁ ወንድማማቾችን በማነጋገር የግድግዳ ስዕሉን አሰራች። ስእሉ በአሁኑ ወቅት በዝናብ ፍሳሽ ምክንያት የተወሰነ ችግር ቢደርስበትም ጥንታዊ ይዘቱን እንደጠበቀ ዘመናትን ተሻግሮ ዛሬም ለዕይታ እየበቃ ይገኛል። የገዳሟ አሰራር መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ያለውና ጥንታዊ ይዘቱንም ያለቀቀ ነው። ከደብሯ በር ላይ ነገስታቱ የሚያርፉበት በኖራ የተሰራ ግንብ ነበር። ይህም ሌላኛው ዘመን ተሻጋሪ ቅርስ ሲሆን፤ ነገር ግን በጣሊያን ወረራ በተደጋጋሚ በከባድ መሳሪያ ተመቶ ፈርሷል።
ሥዕለ ግብፃዊ ማርያም
ደብረሲና ማርያም ካሏት ለዕይታ ከሚማርኩ ስዕሎች መካከል አንዱ የግብፃዊት ማርያም ስዕል ነው። በገዳሙ ውስጥ ከግድግዳ ላይ ካሉ ስዕሎች መካከል በአፈ ታሪክ የገዳሟ መስራች አባ ኤስድሮስ ከግብፅ እንዳመጧት የሚነገርላት ግብጻዊት ማርያም ሲሉ ምዕመናን የሚጠሯት የድንግል ማርያም ስዕል በስተምስራቅ በኩል ትገኛለች። በሌላ በኩል ግብፃዊት ማርያምን እቴጌ መለኮታዊት በልዩ ሱባኤ እንዳሰራቻትና በአንድ ወቅት ተሰርቃ ወደ ግብፅ ተወስዳ እንደነበር ይነገራል። ሆኖም ከሄደችበት በታምር ወደ ደብረሲና ማርያም መመለሷ ይነገራል። ግብፃዊት ማርያም ከልብ አምኖ ለተማፀናት የልቦና መሻትን የምትፈፅምና ተአምራትን የምታደርግ እንደሆነ የአካባቢው ምዕመናን ይናገራሉ። አስገራሚው ነገር ግብፃዊት ማርያም አሁን ድረስ ትገኛለች።
ደብረሲና ማርያምና ቅርሶቿ
የውስጥ የግድግዳ ላይ ሥዕሎቿ የተመራማሪዎችን ቀልብ ይስባሉ። ከ350 ዓመታት በላይ ያለ እድሳት የኖሩ ሥዕሎቿ ትናንትን ያሳያሉ፤ ጥንታዊ ታሪኩንም ይዘክራሉ።ደብረሲና ማርያም አንድነት ገዳም ካሏት ዘመን ተሻጋሪ ቅርሶች መካከል በርካታ የብራና መጽሐፍት በግንባር ቀደምት ተጠቃሾች ናቸው። የቀሩት የብራና መጽሐፍትና ሌሎች ቅርሶችን ለመታደግ አነስተኛ ሙዝየም ያስገነባች ቢሆንም ቅርሶችን በቋሚነት ለማስጎብኘት ከገዳሟ የአገልጋይ እጥረት አንፃር እስካሁን ለመጎብኘት አልታደለም። ነገር ግን የ700 መቶ ዓመት የምስረት በዓሏን ምክንያት በማድረግ ያሏትን ቅርሶች ምዕመናን እንዲጎበኙ ሙዝየሙ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል። ከቅርሶች መካከል ከ13ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ሲያገለግሉ የነበሩ ጽሃዎች፣ተክሊሎች፣ ገድሎች፣ ድርሳኖች፣ በገዳሟ ስም የተቀረፁ ማህተሞች፣የብር መስቀሎች፣ ልብሰ ተክህኖዎች፣ ቃጭሎች፣ የፀበል ኩስኩሶችና መቋሚያዎች በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ።
የገዳሟ ይዞታ
ቀደም ባለው ጊዜ ገዳሟ ወደ ሰባ ስምንት ሄክታር የሚሆን የይዞታ መሬት ነበራት። ይህም ሁኔታ እራስዋን በራስዋ ተንከባክባ ለማስተዳደር መልካም አጋጣሚን ፈጥሮላት ኖሯል። አገልጋዮቿንና የተቸገሩ ምእመናን እየረዳች ዘመናትን ተሻግራለች። ነገር ግን በደርግ መንግሥት ይዞታዋን ተነጥቃለች። ከ1983 ዓ.ም በኋላ ደግሞ በግለሰቦች ይዞታ ስር ይገኛል። አገልጋዮቿም ወደ ሌላ ገዳማት ተሰደዋል። በአሁኑ ወቅትም በሰዎች ድጎማ ላይ ወድቃለች። ቅርሶቿም ለተለያዩ አደጋዎች ተጋልጠዋል። ገዳሟም ብቻዋን ከጣና ሀይቅ ጋር ተፋጣ ቀርታለች። ታዛቢዋ ጣና ብቻ ነው።
በተደጋጋሚ የቆርቆሮ ክዳን ለማልበስ ቢሞከርም ሳይሆን ቀርቷል። ታዲያ የሳር ክዳን ህልውናዋ በመሆኑ ያላትን መሬት ለሳር አገልግሎት ብቻ ታውለዋለች። ቅርሶችን ጠብቃ እንድትቆይ ለማድረግ ክዳን የሚያስፈልጋት ቢሆንም ማግኘት ተስኗት ዝናብ ክፉኛ ጎድቷታል። እንዲሁም በርካታ ቅርሶቿ በምስጥና በሌሊት ወፍ ጉዳት እየደረሰባቸው ይገኛል። ለተለያዩ ሃይማኖታዊ ክንውኖች የሚመጡ ምዕመናንም በችግር ላይ ይገኛሉ። በአጠቃላይ ገዳሟ የድረሱልኝ ጥሪ እያሰማች ትገኛለች።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 5 /2012
ሞገስ ፀጋዬ