አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ በመንገድ ላይ የሚደርሰው የትራፊክ አደጋ ከመቀነስ ይልቅ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የትራንስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በብሔራዊ የመንገድ ደህንነት ምክር ቤት 5ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ተገኝተው እንደገለፁት፤ በሀገሪቱ የመንገድ ላይ የትራፊክ አደጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ በአሳሳቢ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል፡፡
እንደ ሚኒስትሯ ገለፃ፤ በ2010 ዓ.ም ብቻ 5 ሺህ 118 ሰዎች በመንገድ ላይ የትራፊክ አደጋ ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን፤ ይህም በ2009 ዓ.ም ከነበረው 4 ሺህ 479 የሞት ቁጥር ጋር ሲነፃፀር በ639 ዜጎች ሞት ብልጫ እንዳለው ያሳያል፡፡ ይህም አደጋው በአስከፊ ሁኔታ እየጨመረ እንደመጣና በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ይጠቁማል፡፡
ለትራፊክ አደጋ መጨመር አንዱ ምክንያት የብሔራዊ መንገድ ደህንነት ምክር ቤት ለጉዳዩ የሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሯ፤ ለዚህም ማሳያው ምክር ቤቱ ባለፉት ሰባት ዓመታት ቢያንስ 14 ጊዜ ከአባላቱ ጋር እየተገናኘ ሥራዎችን በጥልቀት እየገመገመ አቅጣጫ ማስቀመጥ ሲገባው መገናኘት የቻለው ግን ለአራት ጊዜ ብቻ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በ10 ሺህ ተሽከርካሪዎች የሚደርሰውን አደጋ ከ68 በመቶ ወደ 27 በመቶ ለመቀነስ ታቅዶ መፈፀም የተቻለው ግን 60 በመቶ ብቻ መሆኑን ሚኒስትሯ ጠቅሰው፤ በተመሳሳይም በ2ኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በ10 ሺህ ተሸከርካሪዎች የሚደርሰውን አደጋ 27 ለማድረስ ታቅዶ እስከ 2010 ዓ.ም ባለው ጊዜ መፈፀም የተቻለው 54 በመቶ ብቻ በመሆኑ በተሽከርካሪ የሚደርሰውን የመንገድ ላይ የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ እየተደረገ ያለው ጥረት ውጤቱ አነስተኛ ነው ብለዋል፡፡
ሚኒስትሯ አያይዘውም፤ እየጨመረ የመጣውን የመንገድ ላይ የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ የብሔራዊ መንገድ ደህንነት ምክር ቤት በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መሰየሙን ገልፀው፤ በቀጣይ ጊዜያት አደጋውን ትርጉም ባለው መልኩ ለመቀነስ በሚደረገው ርብርብ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው አስታውቀዋል፡፡
ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ጉዳዩን በባለቤትነት ተቀብሎ በእኔነት ስሜት ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ በጋራ መሥራት እንደሚጠበቅበትና ግንዛቤ በማሳደግና ሕግ በማስፈፀም በኩል የተሠሩ ሥራዎች ውስንነት የሚታይባቸው በመሆኑ ትኩረት ተሰጥቷቸው ርብርብ ሊደረግባቸው እንደሚገባም ሚኒስትሯ አሳስበዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 24/20111
በአስናቀ ፀጋዬ