አዲስ አበባ፡- የግልም ሆነ የቡድን አቋም ከአገርና ከህዝብ በላይ ሊሆን እንደማይገባ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዔ ገለጹ።
የምክር ቤቱ አፈጉባዔ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ ላይ እንደተናገሩት፤ ምክር ቤቱ በዞን፣ በወረዳና በክልል ወሰኖች አካባቢ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ወጣቶችንና የአገር ሽማግሌዎችን አወያይቷል። በውይይቱ ህዝቡ ሰላም ፈላጊ መሆኑ ተረጋግጧል።
አንዱ ብሔር ሌላውን ብሔር ሊያጠቃ የሚመጣውን ሸሽጎ አድኗል። ሆኖም የተማረው የህብረተሰብ ክፍል ላይ የአመለካከት ክፍተት አለ። እየተጣላ ያለው ህዝቡ ሳይሆን የሚያጣሉት የራሳቸው አጀንዳ ያላቸው ከግጭት የሚጠቀሙ ግለሰቦችና ቡድኖች እንጂ ህዝቡ ጨዋ መሆኑ ታይቷል። ሆኖም መታወቅ ያለበት የግልም ሆነ የቡድን አቋም ከአገርና ከህዝብ በላይ ሊሆን አይገባም።
‹‹ሁሉም የየራሱ አቋምና ፍላጎት ቢኖረውም የተማረ ሰው ግን ከሁሉም በላይ ስለህዝብና አገር ማሰብ ይጠበቅበታል›› ያሉት ወይዘሮ ኬሪያ፤ ህዝቡ በየመድረኮቹ ‹‹ሳይማር ያስተማረን ህዝብ አትበሉን፤ ተምራችሁ ያልተማራችሁ እናንተ ናችሁ፤ አገሪቱን ለማፍረስ የተነሳችሁት የተማራችሁት ናችሁ። የእዚህችን አገር አንድነትና ክብር ያስጠበቅነው እኛ ነን፣ ያስተማርናችሁ አገሪቷን አደጋ ላይ እንድትጥሏት አይደለም።›› እያለ የተማረውን እየወቀሰ መሆኑንም አመልክተዋል።
እንደ አፈጉባዔዋ ገለፃ፤ ዘንድሮ በተፈጠረው የህዝብ ለህዝብ መድረክ በተማረውና ባልተማረው ማህበረሰብ መካከል ያለው የአመለካከት ልዩነት ቁልጭ ብሎ ታይቷል። ህብረተሰቡ በየአካባቢው ሰላም እንዲፈጠር የራሱን ሚና እየተጫወተ ነው። ስለአገርና ስለህዝብ ብቻ ከታሰበ የማይስተካከል ነገር የለም። በተለይ በወጣቱና የተማረው ኃይል በዚህ ላይ ማሰብ ይጠበቅበታል።
‹‹የፌዴራል ሥርዓቱ ፍትሐዊነትን እና እኩልነትን ለማስፈን የተዘረጋ ነው። ከዚህ አንፃር ብዙ ሥራ ይጠበቃል። አገሪቱ የሁሉም ናት። የምናስተዳድራትም በጋራ ነው።›› ያሉት ወይዘሮ ኬሪያ ፤ አንዳንዴ የተማረው ኃይል ዋጋ መክፈል ካለበት ዋጋ ከፍሎም ቢሆን ይህቺን ታላቅ አገር መጠበቅ እንዳለበት ጠቁመዋል። ግጭት ሲፈጠር ወጣቶች ማረጋጋት መጀመራቸውን አስታውሰው፤ ይኸው ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትና ምክር ቤቱም ግንዛቤ የማስፋት ሥራውን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 29/2012
ምህረት ሞገስ