በ2011 መጀመሪያ ላይ የአጋጠመው ክስተት ዳግም እንዳይከሰት የሁሉም ነዋሪዎቿ ፍላጎት ነው። ስለ ክስተቱ ሲነሳ ሁሉም በቁጭት የሚናገረው፤ ከእውነት ይልቅ ስሜት ነግሶ፤ ከአንድነት ይልቅ ልዩነት ተሰብኮ፤ ማስተዋልን የጋረደ የፖለቲካ ጥቅመኞች ተረክና ተግባር የፈጠረው ስለመሆኑ ይናገራሉ። ይህ እውነትም ከትናንት በስቲያ 14ኛውን የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን አስመልክቶ በቡራዩ በተካሄደ የህዝቦች የውይይት መድረክ ላይ ተደምጧል።
በመድረኩ እንደተደመጠው፤ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የተለያየ ባህልና ቋንቋ ቢኖራቸውም አንድነታቸው የፋሽሽት ወራሪን ድል እስከመንሳት የጸና ነው። እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም ሆነ ነገ አንድነታቸው ጸንቶ ያለና የሚዘልቅ ነው። ይሁን እንጂ አሁንም የህዝቦችን አንድነት የማይሹ አካላት አሉ። ለዚህ ደግሞ ሊደገም የማይገባው ዓምና በቡራዩ የተፈጠረው ክስተት እማኝ ነው። በመሆኑም እነዚህ ኃይሎችን በመከላከል እና የህግ የበላይነትን በማስከበር ሂደት ግን የጸጥታ አካሉ አሁንም በትኩረት መሥራትና ሁሉንም በእኩል ዐይን ማገልገል ይጠበቅበታል።
ከተሳታፊዎች መካከል፣ አቶ አህመድ ከድር እንደሚናገረው፤የኢትዮጵያ ህዝብ ብዝሃነቱ ሳይወስነው አብሮ የኖረ፣ በጋብቻና በሌሎችም የትስስር ማህበራዊ እሴቶች የተቆራኘ ላይለያይ የተጋመደ አንድነት ያለው ነው። ነገር ግን እንዳንድ ልቅ ሚዲያዎች በህዝቦች መካከል መቃቃር እንዲፈጠር እየሠሩ ነው። ከማቀራረብ ይልቅ ማቃቃር ላይ እየሠሩ ያሉ አሉ። በመሆኑም እነዚህ ሚዲያዎች ሃይ ሊባሉ ይገባል። ሁለተኛም በለውጡ ዙሪያ ህዝቡ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ሊሠራ ይገባል። ምክንያቱም አሁንም ድረስ ህዝቡ ጋር በለውጡ ዙሪያ ብዥታዎች ስላሉ እነዚህ ብዥታዎች እንዲጠሩ መሠራት አለበት።
ሦስተኛም በአመራርና ካቢኔዎች ላይ የአቋም መዋዥቅ ይታያል። ይህ ደግሞ ህዝብንም ሆነ አገርን የሚጎዳ አካሄድ ስለሆነ ሊታረም፤ ሊጠራና በትክክለኛ የህዝብ አገልጋይነት አካሄድ ሊቃኝ ይገባል። እዚህ ላይም መንግሥት በደንብ ሊሠራ ይገባል።
እነዚህ ነገሮች መታረም ከቻሉ የኢትዮጵያ ህዝብ ድሮም አብሮ ያለ፤ አሁንም አብሮ እየኖረ ያለ በመሆኑ የህዝቡ አንድነት የሚያሳስብ ጉዳይ አይሆንም።
ሌላው ተሳታፊ አቶ ረታ ቶሎሳ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ የህዝቦች አንድነትና አብሮ መኖር እጅጉን አስፈላጊ ነው። የእስከአሁኑ የኢትዮጵያ ችግርም በምሁራኖች አካባቢ ግለኝነትን ማንጸባረቅና ጭፍን ጥላቻ ሲሆን፤ ይህ አስተሳሰብ ወደ ህብረተሰቡ ሲንጸባረቅ በህዝቡ ውስጥ ጥርጣሬና ጥላቻ እንዲፈጠር ማድረግ ነው።
በመሆኑም ህዝቡ ከግል ስሜትና ፍላጎት ይልቅ ለአብሮነትና እውነትን እያስጨበጡ ማስጓዝ የግድ ይሆናል። ለዚህ ደግሞ ታሪክን በሚዛኑ አቅርቦ ማስረዳት ተገቢ ሲሆን፤ የቀደሙ መሪዎች በየዘመናቸው በሠሩት ሥራ መጥፎ ገጽታን ከመተረክ ይልቅ ለአንድነት ያበረከቱትን አስተዋጽዖም ማሳየት፤ ዛሬም ኢትዮጵያውያን ካለፈው ክፉ ተግባር ተምረው እንዳይደገም፣ መልካም የአንድነት ጉዞዎችም እንዲጠናከሩ የሚያስችሉ ተግባራት እንዲከናወኑ ማስቻል ይገባል።
ነገር ግን የጠብ ደላሎች ህዝቦችን ለመለያየት እንደማይተኙ መገንዘብ ይገባል። ለዚህ ደግሞ ከአንድ ዓመት በፊት በቡራዩ ከተማ የሆነው እውነት ማሳያ ነው። በመሆኑም ይህ የቡራዩ ክስተት በቡራዩ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ የትኛውም ከተማ እንዲደገም መፍቀድ አይገባም። ይህ የሚሆነው ግን ህዝቦች ሰክነው አካባቢያቸውን በአግባቡ ሲያስተውሉ፤ ወጣቶች ከስሜት ወጥተው የህዝብና የሰላም ባለቤትነታቸውን ሲያረጋግጡ፤ የመንግሥትና የጸጥታ መዋቅሩ የተሰጠውን የህዝብ አደራ በአግባቡ መወጣትና የህግ የበላይነትን ማስከበር ሲችል ነው።
በመሆኑም ሁሉም በዚህ አግባብ ሊሠራ ከግል አስተሳሰብና ፍላጎት ወጥቶ አንድነቱ የተጠናከረና የበለጸገች አገር ለመፍጠር በሚያስችሉ የታሪክ ገጽታዎችና ሥራዎች ላይ ማተኮር ያስፈልጋል። እንደ አስቸጋሬ በሬ ግራና ቀኝ ከመሳሳብ ወጥቶ በጋራ ለጋራ ዓላማ ተግባብቶ መሥራት ይገባል ይላሉ።
የነዋሪዎቹን ሃሳብ የሚጋሩት የቡራዩ ከተማ ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ ቃበቶ አልቤ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ በነዋሪዎቹ የተነሱ ሃሳቦች እውነትም የህዝቡን አንድነትና አብሮነት የሚያንጸባርቁ ገንቢ ሃሳቦች ናቸው። በመሆኑም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና
ህዝቦች በጋራ የሚኖሩባት የእኔ የሚሏትን አገር በመገንባት ሂደት ውስጥ ከግል ስሜት ይልቅ የአገርና ህዝብ ጉዳይ ማስቀደም ተገቢ ነው። ለዚህ ደግሞ የትኛውም ብሔር በአገሩ ጉዳይ መብቱ ተከብሮለትና ጥቅሙ ተከብሮ፤ በፍቅርና በሰላም ተቻችሎ በአንድነት ሊኖር ግድ ይለዋል። ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያውያን የገዳ ዓይነት የአንድነት፣ የእኩልነት፣ የመቻቻልና የአቃፊነት በርካታ እሴቶች አሏቸው። በመሆኑም ሁሉም ህዝብ መብቱ ተከብሮለት በጋራ መኖር የሚችልባት አገር ለመፍጠር እየተሠራ ይገኛል።
በቀጣይም በህዝቦች መካከል አብሮነትና አንድነትን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በመስጠት፤ አንድነትን በሚያሻክሩ አካሄዶች ላይም እርምት እየተወሰደ የሚኬድ ይሆናል። እንደ ከተማ አስተዳደርም የህዝብ አንድነትን ከመገንባት አኳያ ቀጣይነት ያላቸው ሥራዎች እየተከናወኑ ከህዝብ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ይሠራል።
የከተማ ነዋሪ ብሄር ብሔረሰቦችም የኦሮሞ ህዝብ የፖለቲከኛ ጥቅም ፈላጊዎች በሚያናፍሱትና በሚፈጥሩት ማደናገሪያ ሳይሰጉ ያለምንም ፍራቻ በነፃነት መኖር እንደሚችሉ ማዋቅ አለባቸው። የከተማ አስተዳደሩም በዚሁ አግባብ እንደሚሠራ ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 29/2012
ወንድወሰን ሽመልስ