አዲስ አበባ፦ ከሽምብራ ሰብል ፕሮቲንን በማበልፀግ በሕፃናት ላይ የሚከሰተውን የመቀንጨር ችግር ለመከላከል ምርምር እየተደረገ መሆኑንና በዚህም ስኬታማ ውጤት መገኘቱን የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ። የምርምር ውጤቱ በያዝነው ዓመት መጨረሻ ይፋ ይሆናል።
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ዶክተር ኃይሉ ዳዲ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ከሽምብራ ሰብል ፕሮቲንን በማበልፀግ የመቀንጨር፣ የመቀጨጭ እንዲሁም በተመጣጠነ ምግብ እጥረት በሕፃናት ላይ የሚደርሱ ሌሎች የጤና እክሎችን መከላከል የሚያስችል ምርምር እየተደረገ ነው። በሂደቱም ውጤታማ ሥራ ተከናውኗል።
እንደ ምክትል ዳይሬክተር ጄነራሉ ገለጻ፤ የሽምብራ ሰብል ከፍተኛ ፕሮቲን አለው። ይህንን በተለያዩ ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም ፕሮቲኑን በመለየት እና በማበልፀግ ለሕፃናት የተመጣጠነ ምግብ ለማዘጋጀት እየተሠራ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ በተለምዶ ሽምብራን ‹‹ለቆሎ›› እና ‹‹ሽሮ›› ጥቅም ቢውልም አገልግሎቱ ግን ከዚያም ያለፈ ነው። በምርምር ሂደቱም ከሰብሉ ከፍተኛ ፕሮቲን ማበልፀግ የተቻለ ሲሆን ቀጣዩ ሥራ ከሌሎች አልሚ ንጥረ ነገሮች ጋር በማደራጀት ጥቅም ላይ እንዲውል ይደረጋል። ይህም ውጤት በዓመቱ መጨረሻ ይፋ ይሆናል።
‹‹በኢንስቲትዩቱ እና በሌሎች ተቋማት ያሉ ተመራማሪዎች መሰል ውጤታማ የምርምር ሥራዎች እንዲሠሩ ድጋፍ ይደረግላቸዋል›› ያሉት ዶክተር ኃይሉ፤ የአቅም ግንባታ ድጋፍ እና ለምርምር ውጤቶች የሚጠቅሙ አስፈላጊ ቁሶችን በማቅረብ የማበረታታት ሥራ እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ከሽምብራ ምርት ፕሮቲን በማበልፀግ ላይ የሚገኙት የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የስነምግብ ከፍተኛ ተመራማሪው ዶክተር እንዳለ አማረ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የሽምብራ ሰብል ሳይበለፅግ ከ10 እስከ 16 በመቶ ፕሮቲን አለው። አሁን እየተሠራ ያለው የምርምር ሥራ ከሰብሉ ፕሮቲኑን በመለየት ከ60 እስከ 90 በመቶ የፕሮቲን ይዘት እንዲኖረው ማድረግ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን በውስጡ ያሉትን አይረን፣ካልሺየምና ዚንክ የማሻሻል ሥራ እየተሠራ ነው።
‹‹በተለምዶ የተለያዩ ጥራጥሬዎችን ቀላቅሎ ተገቢውን የማበልፀግ ሥራ ሳይሠራ ሕፃናትን የመመገብ ባህል ይስተዋላል›› ያሉት ከፍተኛ ተመራማሪው፤ ይህ ደግሞ ምግቡ ምን ያህል ተገቢው የንጥረ ነገር ይዘት እንዳለው ሳይረጋገጥ የሚሰጥ በመሆኑ የጎንዮሽ ጉዳት እንዳለው ተናግረዋል። ምርምሩ በአገር ውስጥ ያለውን ይህን ባህል ለማስቀረት መሆኑን ጭምር ጠቅሰዋል። በተለይ ብሩህ አዕምሮ ያላቸውና ከተለያዩ የጤና እክሎች ነፃ የሆኑ ሕፃናትን ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
በሥርዓተ ምግብ ችግር ዙሪያ እ.ኤ.አ. በ2016 በተሠራ አንድ ጥናት፣ በኢትዮጵያ 67 በመቶ የሚሆኑት አዋቂዎች ዕድገት እንዲቀጭጭ ሆኗል:: በጥናቱ መሠረት፣ ከአምስት ዓመት ዕድሜ በታች በሆኑ ሕፃናት የመቀንጨር ችግር በስፋት የሚታየው በአማራ ክልል ነው፡፡ በክልሉ የመቀንጨር ችግር 46 ነጥብ 3 በመቶ ሲሆን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 42 ነጥብ 7 በመቶ፣ በአፋር ክልል 41 ነጥብ 1 በመቶ ነው:: በዚህ ረገድ የተሻሉ የተባሉት አዲስ አበባ 14 ነጥብ 6 በመቶና ጋምቤላ 23 ነጥብ 5 በመቶ መሆኑን ጥናቱ ያመለክታል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 28/2012
ዳግም ከበደ