ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአንደኛ ዓመት ተማሪ የሆነው ፈይሳ ኩማ የጎንደር ዩኒቨርሲቲን የተቀላቀለው ዘንድሮ ነው። የኦሮሚያ ክልል ተወላጁ ፈይሳ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሲመደብ “ክፉ ነገር ይገጥመኝ ይሆን?” ብሎ ፈራ ተባ እያለ ሲያመነታ እንደ ነበር ይናገራል። “ጓደኞቼም አለቀልህ፤ አታስብ እንቀብርሀለን እያሉ ያሾፉብኝ ነበር፡፡ እኔ ግን በድፍረት መጣሁ፡፡” ሲል ሃሳቡን አካፍሎናል።
የተማሪ ፈይሳ ስጋት የሌሎችም ተማሪዎች ስጋት ነው። የእሱ ቤተሰቦች ጭንቀትም የብዙ ወላጆች ጭንቀት ነው። ሆኖም ግን ፈይሳ የጎንደር ህዝብ ስጋዬ እንጂ ስጋቴ አይሆንም ብሎ በድፍረት ወደ ተመደበበት ዩኒቨርሲቲ አመራ። ከተለያዩ ሰዎች የሰማውን ማስፈራሪያ ሁሉ ከእውነት የራቀ ሆኖ እንዳገኘው ይናገራል።
“ ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ጀምሮ ነዋሪ ሰው ወዳድ መሆኑን አይቼ አረጋግጫለሁ። በርካታ የኦሮሞ ልጆች ጎንደር ተምረው አግብተው የሚኖሩ አግኝቻለሁ፡፡ ባለፈው በነበረው መጠነኛ ችግር ወቅትም በርካቶች እየደወሉ ተደበቅ ሲሉኝ ነበር፤ ነገር ግን አኔ ከጓኞቼ ጋር አዘዞ ነበር ያሳለፍኩት፡፡ ብዙ ሰው አውቄያለሁ፤ መፍራትም ካቆምኩ ቆይቻለሁ፡፡ አሁን ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በመመደቤ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡” ሲል ይገልጻል።
ተማሪ ፈይሳ በዩኒቨርሲቲው” አንድ ተማሪ ለአንድ ቤተሰብ” በሚለው ፕሮግራም ያገኛቸው የአደራ ቤተሰቦቹ ምንም ችግር እንደማይገጥመው እርግጠኛ እንዲሆን አበረታተውታል።” ዛሬ ደስ የሚል ቤተሰብ አግኝቻለሁ፡፡ ‹የአደራ ልጃችን ነህ፤ እንዳትፈራ› ብለውኛል፡፡ እኔም እንደወለዱኝ ቤተሰቦቼ አያቸዋለሁ፡፡ በዕለቱ እነሱ ሲያበረታቱኝ የተሰማኝ ስሜት ትምህርት ጨርሼ የተመረቅኩ ያህል ነው። አሁን አብዛኞቹ የቤተሰቦቼ አባላት መጥተው ተዋውቀውኛል፡፡ ዛሬ ማታም የእራት ግብዣና ከተቀሩት የቤተሰቡ አባላት ጋር የትውውቅ ፕሮግራም አለ፡፡ እኔም የአደራ ቤተሰቦቼ ቤት ለመሄድም ተዘጋጅቻለሁ፡፡” ይላል።
የጎንደር ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ሀያት ሙላት አንድ ተማሪን የቤተሰባቸው አካል ለማድረግ አደራ መረከባቸው እንዳስደሰታቸው ይናገራሉ። “ያለኝ አንድ ልጅ ነበር። አሁን ሁለት ሆነውልኛል።” ሲሉ ነው የአደራ ለጃቸውን ከልጃቸው ሳይነጥሉ እንደሚደግፉት የገለጹት።
“ እንደወላጅ የሚያስፈልገውን ሁሉ አደርግለታለሁ። እሱም እንደእናት እኔን መጠየቅ አለበት። ከሌላ አካባቢ የመጡ ልጆች ወላጅ ማግኘታቸው የበአድነት ስሜት እንዳይሰማቸው ያደርጋል። በተለይም የእኔ ልጅ ከኦሮሚያ ክልል የመጣ በመሆኑ ቋንቋና ባህል ለመለዋወጥ ያግዘናል። ትምህርቱን ጨረሶ ወደ ወላጆቹ ሲመለስም ሄጄ ከቤተሰቦቹ ጋር እተዋወቃለሁ። ሁሉም ወላጅ በአደራ የተረከባቸውን ልጆች ልክ እንደልጆቹ መንከባክብና የጎደላቸውን በመጠየቅ ድጋፍ ማድርግ አለበት” ሲሉ ይገልጻሉ።
የኒቨርሲቲው አምስት ሺ ተማሪዎችን ለአምስት ሺ ቤተሰቦች በአደራ ለመስጠት የያዘው የመጀመሪያው ፕሮግራም የተካሄደው ትናንተ ነው። በዚሁ ዕለትም አንድ ሺ 500 ተማሪዎች ሃሳባቸውን የሚካፈላቸው ጭንቀታቸውን የሚጋራቸው ደግሞም መፍትሔና አለኝታ የሚሆናቸውን የአደራ ቤተሰብ አግኝተዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 28/2012
ሞገስ ፀጋዬ