የአንድ አገር መሪ የሚናገረው ንግግር ዓለም አቀፍ ወሬ ይሆናል:: እንዲያውም አንዳንዴ ከሚሠሩት ሥራ ይልቅ በሚናገሩት ንግግር ይመዘናሉ:: ከሥልጣን ሲወርዱ ወይም በሞት ሲለዩም ከሠሩት ሥራ ይልቅ የተናገሩት ነገር ጉዳይ ይሆናል:: ንግግሮቻቸውም በታሪክ ተሰንደው ይቀመጣሉ:: ክፉም ይሁን ደግ ከሠሩት ሥራ ይልቅ ክፉም ይሁን ደግ የተናገሩት ነገር በየአጋጣሚዎች ይነሳል:: ለምሳሌ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ከሠሩት ሥራ ይልቅ ንግግራቸው ሲደጋገም እናያለን:: አቶ መለስ ዜናዊም ከሠሩት ሥራ ይልቅ ንግግራቸው ሲደጋገም ነው የሚታየው::
ለዚህም ነው በመሪዎች ቃላት ይፈጠራሉ:: ይፈጠራሉ ሲባል የግድ አዲስ ቃል መፍጠር ብቻ ላይሆን ይችላል፤ ግን የነበሩት ቃላት የበለጠ ትኩረት ይሰጣቸውና ታዋቂ ይሆናሉ:: እስከመኖራቸውም ልብ ያልተባሉ ቃላት በመሪዎች ሲነገሩ ይጎላሉ:: አንዳንዶቹ ደግሞ ከዚያ በፊት የሚታወቁበት ትርጉም ይቀየርና መሪው (ባለሥልጣኑ) በተናገሩበት አውድ ይታወቃሉ:: ከዚያ በኋላ ትርጉማቸው መሪው የተናገረው ይሆናል:: ለምሳሌ በኢህአዴግ ዘመነ መንግሥት (ኢህአዴግ በቀድሞው ስሙ ሊባል እኮ ነው)፤ ኪራይ ሰብሳቢ፣ ትምክህት፣ ጠባብ፣ ጨለምተኛ… የሚሉ ቃላት ታዋቂ ሆነዋል:: በቀልድም በቁም ነገርም ወርወር ይደረጋሉ:: አንዳንድ ቃላት የመንግሥት ብቻ እስከሚመስሉ ድረስ የሚሰጣቸው ትርጉምም መንግሥታዊ ይሆናል:: ለምሳሌ ‹‹ልማት›› የሚለውን ቃል ኢህአዴግ አልፈጠረውም:: ግን የኢህአዴግ ባለሥልጣናት ደጋግመው ስለሚናገሩት የእነርሱ ብቻ መሰለ:: ልማት የሚለው ቃል ግን በራሱ ለምላሜና በተፈጥሮ ሀብት ሠርቶ መበልጸግን የሚገልጽ ነው:: በእርግጥ ኢህአዴግም ሲጠቀመው የነበረው ሠርቶ መበልጸግን ለመግለጽ ነው:: የዚህ ቃል ትርጉም ለምላሜና ሀብት መሆኑን ለማወቅ ገበሬዎችን ልብ ብሎ ማየት ነው:: የሆነ የሚያምር ተፈጥሮ ሲያዩ ‹‹ለምለም ነው፤ የለማ ነው›› ሲሉ ይሰማል:: ለልጆቻቸው ‹‹ለማ›› የሚል ስም የሚያወጡትም ለዚህ ነው:: በአጭሩ የጥፋት ተቃራኒ ማለት ነው::
የመሪዎች ንግግር ተጽዕኖ ፈጣሪነት ዓለም አቀፍ ነው:: ለዚህም ነው በየጋዜጣውና መጽሔቱ ሃሳብ የሚጀመረው በንግግራቸው ነው:: እገሌ እንዲህ አለ፣ እገሌ እንዳለው እየተባለም ይገለጽላቸዋል:: በደርግ ዘመነ መንግሥት አንድ ገበሬ ተናገሩት የተባለውን ቀልድ እንጥቀሰው:: ንግግር የሚያደርገው ሰውየ ‹‹ሌኒን እንዳለው፣ ማርክስ እንዳለው፣ ኤንግልስ እንዳለው፣ ስታሊን እንዳለው…›› እያለ ያወራል:: ግራ የተጋቡት ገበሬ ‹‹እኔ እምለው! እኒህ አባ እንዳለው የሚባሉት ሰውየ ግን ስንት ልጆች ነው ያሏቸው?›› ብለው ጠየቁ አሉ፤ ምስኪን የኔ አባት!
ወደ አገራችን መሪዎች ስንመጣ፤ በንጉሡ ጊዜ፣ በደርግ ጊዜ፣ በኢህአዴግ ጊዜ የነበሩ መሪዎች ሁሉ ንግግራቸው ይደጋገማል:: እንኳን የተናገሩት ነገር ያልተናገሩት ነገር እንኳን ለቀልድ ተብሎ ይፈጠራል:: ያ ቀልድ የሚፈጠረው ግን በትክክል ከተናገሩት ነገር በመነሳት ነው:: በመሪው የንግግር ባህሪ ላይ በመመስረት ሊል ይችላል በሚል ምናባዊ ፈጠራዎች ይፈጠራሉ:: ለምሳሌ አቶ መለስ ዜናዊ በፓርላም አስቂኝና ቆምጨጭ ያለ ነገር ይናገሩ ስለነበር ብዙ ቀልዶች ተፈጥረዋል::
አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በትክክል የተናገሩትንም ነገር ለሌሎች ቀልዶች መጠቀም የተለመደ ነው:: ለምሳሌ ዶክተር አብይ ወደ ሥልጣን የመጡ ሰሞን ንግግሮቻቸው የቀልድና ጨዋታ ማድመቂያዎች ነበሩ:: በዚያን ሰሞን የፋሲካ በዓል ነበርና በዶሮዎች ላይ እንዲህ ተቀልዷል:: ‹‹እኛ ዶሮዎች ስንኖር ዶሮ፤ ስንሞት ዶሮ ወጥ እንሆናለን!›› ይሄ ቀልድ የተወሰደው ‹‹ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ እንሆናለን›› ከሚለው የዶክተር አብይ ንግግር ነው::
እንግዲህ የመሪዎች ንግግር ይህን ያህል አቅም አለው:: ከእረኛ እስከ መሪ ባሉት ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል:: በመጥፎም በደግም ይተረጎማል:: ከዚህ ጋር ተያይዞ በአገራችን ያለው ችግር ግን የመሪዎችን ንግግር ተደራቢ ትርጉም መስጠት ነው:: ይሄ ደግሞ የሀሜተኛና የነገር ሰንጣቂነታችን መለያ ነው::
እንደሚታወቀው መሪዎች ብዙ ጊዜ ንግግር የሚያደርጉት በጽሑፍ ነው:: ያለ ጽሑፍ ንግግር የሚያደርግ መሪ እንደ ብቃት ይታይለታል:: ይህ ግን በእኛ አገር ይቻላል? ከባህሪያችን ጋር አብሮ ይሄዳል? አንዳንዴ እርበርሱ የተጣረሰ ባህሪ ነው ያለን:: ለምሳሌ ወረቀት ይዘው ሲያወሩ እንሰለቻለን፣ ያለወረቀት ማውራት የማይችሉ እያልን እንወቅሳለን:: ምክንያቱ ደግሞ በጽሑፍ ሲያወሩ ወጣ ያለና ዘና የሚያደርግ ቃላት ስለማናገኝ ነው፤ የፕሮቶኮል ንግግር ስለሚበዛው ነው::
በአንፃሩ ወጣ ያለና ዘና የሚያደርግ ቃላት የሚወጣው ደግሞ ያለ ጽሑፍ ሲናገሩ ነው:: ያለ ጽሑፍ ሲናገሩ ከገጠመኝም ሊነሱ ይችላሉ፤ አንዳንዴም በአዳራሹ ወይም በሚናገሩበት ቦታ ካስተዋሉት ነገር ሊነሱ ይችላሉ፤ ከመናገራቸው በፊት ከነበሩ ሁነቶች ወይም ተናጋሪዎችም ተነስተው ሊናገሩ ይችላሉ:: በጽሑፍ ሲሆን ግን ቀድሞ ስለሚዘጋጅ ለእነዚህ ነገሮች ዕድል አይሰጥም::
የየትም አገር መሪ ቢሆን አብዛኛውን ጊዜ ንግግር የሚያደርጉት በጽሑፍ ነው:: ልዩነቱ የእነርሱ በቴክኖሎጂ ነው:: ለተመልካች የማይታይ መሪው ብቻ የሚያነቡት ስክሪን አላቸው:: እጃቸው ላይ ምንም ዓይነት ወረቀት አይታይም:: ለምሳሌ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ሁሴን ኦባማ በንግግር ታዋቂ ናቸው፤ ግን ከስክሪን ላይ እያነበቡ እንደሆነ ነው የሚነገረው:: የአገራችን መሪዎች ግን ለተመልካች ወረቀት ይዘው ስለሚታይ ያለጽሑፍ የማያወሩ እነርሱ ብቻ ይመስሉናል:: በእርግጥ ብዙ የውጭ አገራት መሪዎችም ወረቀት ይዘው ሲናገሩ ይሰማል::
በእኛ አገር ሀሜትና ነገር ሰንጣቂነት ጽሑፍ ሳይዙ ያውሩ ማለት አይስኬድም:: የተለመደው ትርጉም እያለ ተደራቢ ትርጉም ፍለጋ የምንሄድ ነን:: ያልተቀኙትን ቅኔ የምንፈታ ነን:: የተለመደውን የፕሮቶኮል ንግግር ሲናገሩ ‹‹አሰልቺ፣ አዲስ ነገር የሌላቸው፣ አዝግ…›› እያልን እንወቅሳለን:: ወጣ ያለና ዘና የሚያደርግ ነገር ሲናገሩ ደግሞ ‹‹እንዴት ይሄ ከመሪ ይጠበቃል? መሪ እኮ በፕሮቶኮል ነው መናገር ያለበት..›› እንላለን:: ስለዚህ በተለመደው ፕሮቶኮል ቢናገሩ ይሻላል ማለት ነው::
የተለያዩ ጥናቶችና ጽሑፎች እንደሚያመለክቱት መሪዎች ንግግር ማድረግ ያለባቸው ጽሑፍ አዘጋጅተው ነው:: ይህ ሲሆን ግን አንድ የሚመከር ነገር አለ:: መሪዎች በጽሑፍ ንግግር ሲያደርጉ እያነበቡ ሳይሆን እየተናገሩ መምሰል አለበት:: ያ ማለት ዝግጅት ማድረግ አለባቸው ማለት ነው:: ሲያነቡ መደነቃቀፍ የለባቸውም ማለት ነው::
‹‹About Leaders›› የተባለው ድረ ገጽ ከሚዘረዝራቸው ነገሮች አንዱ ደግሞ ንግግራቸው አዝናኝና ሳቢ መሆን አለበት ይላል:: የሚናገሯቸው ቃላት ሳቢና ጆሮ ገብ መሆን አለባቸው:: የሚታወሱ ቃላት መሆን አለባቸው:: ለዚህም የምሁራንን፣ የስነ ጽሑፍ ሰዎችንና የሌሎች ታዋቂ ሰዎችን አባባል መጠቀም ይመከራል:: የሚነገሩት ቃላት ለሁሉም የሚገቡ እንጂ በአንድ ሙያ ላይ ብቻ የሆኑ (ጃርገን) መሆን የለባቸውም::
የመሪዎች ንግግር እንዲህ መሆን አለበት ብሎ መምከርም አስተያየት መስጠትም አይመችም:: ምክንያቱም ይህ የሚወሰነው በአገራቱ ነበራዊ ሁኔታ፣ በመሪዎቹ ባህሪ፣ በአገሪቱ ህዝብ ባህልና ደንብ መሰረት ነው:: መሪ ናቸውና የሚናገሩት ነገርም አድናቆት ወይም ወቀሳ ብቻ ያስተናግዳል ማለት አይቻልም:: ተመሪዎች ግን ልብ ማለት ያለብን ነገር ሰው መሆናቸውን ነው:: ‹‹ሚካኤል ወይም ገብርኤል አይደሉም›› ብለው ነበር መጋቢ ሐዲስ በአንድ መድረክ ላይ:: ችግራችን ሲሳሳቱም የሰው ተፈጥሯዊ ባህሪ መሆኑንም እንረሳለን:: እርግጥ ነው አንድ መሪ ከሌላው ተራ ግለስብ በብዙ እጥፍ መሻል አለበት፤ ለሚናገረው ነገር ጥንቃቄ ማድረግ አለበት፤ የእሱ ስህተት እንደ ሌላው ሰው ስህተት አይደለም:: ይህም ሆኖ ግን ስናደንቅም ስንወቅስም ሰዋዊ ተፈጥሯቸውን አንርሳ!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ህዳር 27/2012
ዋለልኝ አየለ