-ለበጀት ድጋፍ፤ ዕርዳታና ብድር ከ40 ቢሊዮን ብር በላይ ተገኝቷል
አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ በ2012 የመጀመ ሪያው በጀት ዓመት ሶስት ወራት ውስጥ 5 ነጥብ 563 ቢሊዮን ብር የውጭና የአገር ውስጥ ብድር ክፍያ ፈጽማለች።በአንጻሩ የተለያዩ ተቋማት እና መንግስታት ድጋፍ በመጠናከሩም ለቀጥታ በጀት ድጋፍ፤እርዳታና ብድር ከ40 ቢሊዮን ብር በላይ መገኘቱን ገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የገንዘብ ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሃጂ ኢብሳ እንደገለጹት፤ በ2012 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ለማዕከላዊ መንግሥት የውጭ ብድር ለዋና ዕዳ ክፍያ ብር በድምሩ ብር 3 ነጥብ 520 ቢሊዮን ብር ክፍያ ለመፈጸም ታቅዶ ለዋና ዕዳ 1 ነጥብ 76 ቢሊዮን ብር ክፍያ የተፈጸመ ሲሆን ለወለድ እና ለባንክ ማስተላለፊያ ክፍያ ደግሞ 1 ነጥብ 36 ቢሊዮን ብር በድምሩ ብር ከ3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ክፍያ በመፈጸም የዕቅዱን 88 ነጥብ 6 ከመቶ አፈጻጸም ማስመዝገብ ተችሏል።
እንደ ሚኒስቴሩ መረጃ ከሆነ፤ በሌላ በኩል ለአገር ውስጥ የማዕከላዊ መንግሥት ብድር ለዋና እና ወለድ እንዲሁም ለቀጥታ ግምጃ ቤት ሰነድ ብድር ወለድ በድምሩ ብር 2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ዕዳ ክፍያ ለመፈፀም ታቅዶ ነበር። ለማዕከላዊ መንግሥት ብድር ዋና እና ወለድ 462 ነጥብ 28 ሚሊዮን ብር እንዲሁም ለቀጥታ የግምጃ ቤት ሰነድ ብድር ወለድ 1 ነጥብ 98 ቢሊዮን ብር በድምሩ ከ2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ዕዳ ተከፍሏል። ክፍያው ከዕቅዱ አንጻር የ111 በመቶ አፈጻጸም አለው።
ከብድር ክፍያ በዘለለ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ ተቋማትና መንግሥታት ጋር ያላት የኢኮኖሚ ትብብር እና የፋይናንስ ግኝት መጨመሩን የገለጹት አቶ ሃጂ፤ በበጀት ዓመቱ በመጀመሪያዎች ሦስት ወራት 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር መገኘቱን ገልጸዋል። ከአውሮፓ ሕብረት እና ከዓለም አቀፍ የልማት ማህበር (IDA) ለፍትሐዊ መሠረታዊ አገልግሎት ለጋራ ብልጽግና ፕሮግራም (ESPESP) የተገኘውን ገንዘቡን ቀጥታ ወደ ማዕከላዊ ትሬዠሪ ፈሰስ የሚደረጉ ሲሆን፤ መንግሥት የፈለገውን የልማት ዕቅድ ለመፈፀም እንዲሁም የበጀት ጉድለቱን ፋይናንስ ለማድረግ የሚያስችሉ ናቸው።
እንደ አቶ ሐጂ ገለጻ፤ የውጭ ሀብት ፍሰት እና ግኝት አፈጻጸም በተመለከተ በሦስት ወራቱ ከተለያዩ ለጋሽና አበዳሪ ተቋማት እና የልማት አጋር መንግሥታት በብድርና በዕርዳታ ወደ አገር ውስጥ ከ1 ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ተገኝቷል። ከዚህ ውስጥ ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እና ከመንግሥታት ትብብር የተገኘው ገንዘብ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል።
ከዓለም አቀፍ ተቋማትና መንግሥታት ጋር ያደረገቻቸው የኢኮኖሚ ትብብር ስምምነቶችን እየጨመሩ መምጣታቸውን የገለጹት አቶ ሐጂ፤ ይህም የኢትዮጵያ የፋይናስን ምንጭ መጠናከሩን እንደሚያሳይ ገልጸዋል። እንደ እርሳቸው በልዩ ልዩ ዘርፎች የታቀዱ የመንግሥት የልማት ሥራዎችን ለመደገፍ የሚያስችሉ የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፎችን እንዲሁም የንግድና የኢንቨስትመንት ዕድሎች አሁንም እየተገኙ ነው። ድጋፎቹም መንግሥት ቀጣይና ዘላቂ የሆነ ልማት እና ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት ለማረጋገጥ በሚያደርገው ጥረት ጉልህ ሚና አላቸው።
ለአብነትም በቅርቡ የጀርመን መንግ ሥት ያደረገው የ352 ሚሊዮን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ ኢትዮጵያ በተለያዩ ሀገራትና ተቋ ማት ዘንድ ያላት ተቀባይነት እየጨመረ መምጣቱን የሚያሳይ መሆኑን ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 27/2012
ጌትነት ተስፋማርያም