ምህረቱ የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ነው። ስምንተኛ ክፍል ደግሞ ለቀጣይ ህይወቱ ታላቅ መሰረት የሚጥልበት በመሆኑ አጥጋቢ ውጤት ለማምጣት ቀን ከሌት የሚያጠናበት ወሳኝ ወቅት ነው።
ምህረቱ የአርሶ አደር ልጅ ነውና ከብቶቹን ይዞ ከእርሻ ይውሏል። በድንገት አንድ ቀን ምህረቱ ሜዳ የዋሉትን ከብቶች ከሄዱበት መልሶ ራመድ ከማለቱ በአንደኛው እግሩ ድንገት የተሰነቀረው እሾህ አላራምድ አለው። በእሾህ መወጋት ለገጠሩ ወጣት ብርቅ ባይሆንም ጊዜ መስጠትን አልፈለገም። እንደተለመደው የእግሩን እሾህ ከገባበት ሊያወጣ በእጆቹ መነካካት ያዘ።
ማምሻውን እያነከሰ ከቤቱ ሲገባ እናት በፈገግታ ተቀብላው እሾሁን ሊያወጡለት ሞከሩ። እሱ ግን ለጉዳዩ ትኩረት ሳይሰጥ ለአዳር ከመኝታው ጋደም አለ። ሲነጋ ከምህረቱ እግር የገባው እሾኽ እንደተደላደለ ነበር። ምህረቱ አሾሁን በእጆቹ እየነካካ ለማውጣት ሞከረና ሳይሳካለት ቀረ። እየቆየ የሚሰማው ሕመም ለየት ሲልበት ግን ቤተሰቡ ተነጋግሮ ወደ ሀኪም ዘንድ ወሰዱት።
ከሀኪምቤቱ ሲደርሱ ሰአቱ ለምሳ ተቃርቦ ነበር።በስፍራው ያገኙት የዕለቱ ተረኛ ነርስ በዚህ ጊዜ መምጣታቸው ያስደሰተው አይመስልም። ወደቤቱ ለመውጣት እየተጣ ደፈ ነበርና ተቀብሎ ለማስተናገድ ፊት አልሰጣቸውም። ይህኔ ስጋት የገባቸው እናት ፈራ ተባ እያሉ ልመናቸውን ቀጠሉ። የልጃቸውን ጭንቅ የያዘው ፊት በሩቅ እያሳዩም በልመና ተማጸኑ።
ነርሱ የእናትን ልመና ከምንም አልቆጠረም። የምሳ ሰአቱ መባከን እያናደደው ታማሚውን ወደውስጥ እንዲያስገቡት ትዕዛዝ ሰጠና ወዲያው መድሀኒት የሞላ መርፌ ይዞ ተመለሰ። አፍታ አልቆየም። በታማሚው አንድ እግር ላይ ሁለት መርፌ ወግቶ ‹‹ጨርሻለሁ››ሲል ከክፍሉ ሊወጣ ተጣደፈ።
ምህረቱ መርፌውን እንደተወጋ ራሱን መቆጣጠር አልቻለም።በታፋው ሲወርድ የተሰማው መድሀኒት ነርቩን ሰብስቦ ስቃዩን ቢያበዛው ህመሙን በጨኽት ለመግለጽ ሞከረ። እግሩ ግን በሚያስገርም ፍጥነት ማበጥ ጀምሮ ነበር።ውሎ አድሮ ደግሞ እብጠቱ አመርቅዞና ደምና መግል ይዞ መፈንዳቱን ቀጠለ።ይህኔ ስቃዩን ማየት የከበዳቸው ወላጆች ልጃቸውን አዝለው ወደ ባህርዳር ፈለገ ህይወት ሆስፒታል ገሰገሱ።
የሆስፒታሉ ባለሙያዎች ምህረቱን እንዳዩት አልጋ አስይዘው ህክምናውን ቀጠሉ። ስጋውን አልፎ አጥንቱን መጉዳት የጀመረውን ቁስል እያከሙም ከስቃዩ ሊታደጉት ሞከሩ፡ ፤አሁንም ግን የምህረቱ እግር የታሰበውን ያህል ለውጥ ማምጣት አልቻለም።ጥቂት ቆይቶ የተገኘው ውጤት ደግሞ ህመሙ ወደ አጥንት ቲቪ መለወጡን አመለከተ።ይህኔ መላው ቤተሰብ በጭንቀት ተውጦ በሀዘን ተኮራመተ።
በዚህ መሀል ደግሞ ከቤት የቀሩት አባወራ በጠና መታመማቸው ተሰማ ።ይህኔ ምርጫው ያልነበራቸው እናት ልጃቸውን ይዘው ለአባወራው ለመድረስ ወደቤት ሊመለሱ ግድ ሆነ።
ከቀናት በኋላ የምህረቱ አባት በሞት ሲለዩ ቀድሞ በችግር የተፈተነው ቤተሰብ ሀዘን የከበደ ሆነ ።ይህ ክፉ አጋጣሚ ደግሞ ህመሙ በከፋ ደረጃ እንዲባባስ ሰበብ ሆኖ ምህረቱ አስራአንድ አመታትን በአልጋ ላይ እንዲያሳልፍ አስገደደ።
እነሆ! ዛሬ የትናንትናው ብርቱ ተማሪ አስራአንድ አመታትን በህመም ካሰለፈበት አልጋ ላይ ውሎ የነገን መንጋት በተስፋ ይጠብቃል።እነዚህን አመታት ከማይድን ቁስል ጋር ሲታገል የቤተሰቦቹ ሀብትና ጥሪቶች ተሽጠው ገንዘቡ ለህክምና ውሏል።
የዛኔ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የነበረው የቤቱ ታላቅ ልጅ ስራ ከያዘ በኋላም የአቅሙን በማገዝ ወንድሙን ለማዳን ሞክሯል። ይሁን እንጂ የምህረቱ የህክምና ውጤት ተስፋ ከማስቆረጥ የዘለለ ለውጥ አልተገኘበትም። በየጊዜው ኢንፌክሽን የሚፈጥረው ቁስል እስከአጥንቱ ዘልቆ እያመረቀዘ ስቃዩን አበርትቶበታል።
ከአመታት በፊት ከምህረቱ ጋር ትምህርት ከጀመሩት ባልንጀሮቹ መሀል አንዳንዶቹ ዛሬ ኢንጂነር፣ዶክተርና መምህራን ሆነዋል።ይህን የሚያውቀው የትናንቱ ጎበዝ ተማሪ ደግሞ የአልጋ ቁራኛ ያደረገውን ክፉ አጋጣሚ ሲያስብ ልቡ በሀዘን ይሰበራል። የዛኔ ለሞዴል ፈተና የተነሳውን ፎቶግራፍና በወቅቱ የነበሩትን አስገራሚ የትምህርት ውጤቶች አሁንም በግርምታ ያስተውላል። በክፉ ደዌ የታሰሩ እግሮቹን እያየም አንገቱን በትካዜ ይደፋል።
ምህረቱን ጨምሮ መላው ቤተሰብ ለዚህ አስከፊ ችግር መፈጠር መነሻ የሚያደርጉት ደግሞ ከአስራአንድ አመታት በፊት በአካ ባቢያቸው ጤና ጣቢያ የተካሄደውን ህክምናና ከዚሁ ጋር ተያይዞ ተከስቷል ያሉትን ሙያዊ ስህተት ነው።
ምህረቱ ለአንድ ሚዲያ እንደገለጸው፤ ይህ ችግር ከተከሰተ በኋላ የህክምና ባለሙያውን ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም። ክሊኒኩም ስለመፍረሱ ተሰምቷል። በወቅቱ መላው ቤተሰብ በእሱ ጉዳይ ላይ ብቻ ማተከኮሩ ግለሰቡን ተከታትሎ ለህግ ማቅረብ እንዳላስቻለም በቁጭት ይናገራል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምግብ መድሀኒትና ጤና እንክብካቤ ቁጥጥር ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ደብረወርቅ ጌታቸው ግን ማንኛውም ሰው ከህክምና ጋር ተያይዞ የሚያጋጥመውን ስሕተትና ሙያዊ የስነምግባር ጥሰት ተመልክቶ ዝም ሊባል እንደማይገባ ይናገራሉ።
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ጊዜ ይህን ችግር የሚያጠናና ከተገልጋዩ የሚቀርቡ ክሶችን መርምሮ ወደ ሕግ የሚያቀርብ የሙያ ስነምግባር ኮሚቴ ተቋቁሞ ስራ ጀምሯል።ኮሚቴው በህግና ደንብ ደረጃ ተሰይሞ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ሲሆን፤ በህክምና ስህተቶችና በሚያጋጥሙ የሙያዊ ስነምግባር ጥሰቶች ላይ የሚቀርቡ ክሶችን የመመርመርና ውሳኔ የማሳለፍ መብት የተሰጠው ነው።
በቅሬታና በክስ መልክ የሚቀርቡ ጥቆማዎችን ተቀብሎ ለማስተናገድ በተደረገው ጥረት በአዲስ አበባ ከተማ 180 ክሶች ለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ቀርበዋል። ከእነዚህ መሀልም አስራአንድ ያህሉ ጉዳያቸው ከአዲስ አበባ ውጪ በመሆኑ የክስ መዝገቡን ለፌዴራል መስሪያ ቤቱ ማስተላለፍ መቻሉን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
ህክምና አሰጣጥና ሥነምግባር ጥሰት ላይ ያላቸውን ቅሬታና ክስ ይዘው የሚቀርቡ ተገልጋዮችንና የሚመለከታቸውን የህክምና ተቋማትን አቅርቦ በህግ የመጠየቅ ኃላፊነት የተሰጠው ይህ ተቋም በኮሚቴው በኩል ተገቢውን እርምጃ የመውሰድ መብት እንዳለውም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
እንደ አቶ ደብረወርቅ ማብራሪያ ለተቋሙ የሚቀርቡ ጉዳዮች ከቅሬታ አልፎ ወደ ወንጀል የሚጠጉ ሆኖ ከተገኘ በህግና ደንቡ መሰረት ወደ ፍርድ ቤት የሚላኩበት አግባብ እንደሚኖር ተናግረዋል። ዳይሬክተሩ አክለውም ህብረተሰቡ በህክምና ላይ ስህተቶች ሲያጋጥሙት ጉዳዩን ወደ ህግ የመውሰድ ልምዱ አነስተኛ መሆኑን ገልጸዋል። እንዲህ ዓይነት ልማድ መኖሩን ከግምት ያስገባው ተቋምም በተለያዩ ሚዲያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫዎችን በመስጠት ለተደራ ሽነቱ በየክፍለ ከተሞቹ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታውቀዋል።
ህብረተሰቡ በማንኛውም ጊዜ የህክምና ስህተቶችና የስነምግባር ጥሰቶች ሲያጋጥሙትም በነጻ የስልክ መስመር 8464 በመደወል ጥቆማ ማድረግና መብቱን በህግ ተጠቅሞ መፍትሄ መሻት ይገባዋል ሲሉ አቶ ደብረወርቅ አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 27/2012
መልካምስራአፈወርቅ