‹‹ዛሬ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል?›› የሚለውን መመለስ የሚያስችል ቁንጽል መረጃ ቢኖረኝም፤ ‹‹በምን ምክንያት?›› ለሚለው ተጨባጭ ነገር ማቅረብ አላስቻለኝም። ምንም ይሁን ምን ግን ይህን የታሪክ አንድ ሁነት ለዛሬው ጽሑፌ ጉዳይ የመስፈንጠሪያ ነጥብ ላደርገው ወደድኩ። ይህ የታሪክ አንድ አካል ሆኖ ያለፈው ማዕከል በአምስት መንደሮቹ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሕጻናትን አሳድጓል። በሁለት የአጸደ ሕጻናት፣ በሁለት የመጀመሪያ ደረጃ እና በአንድ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶቹም አስተምሮ የእውቀት ባለቤት አድርጓል። ልጆች በእንክብካቤ እንዲያድጉና የቀለም ትምህርት እንዲቀስሙ ከማድረግ በተጓዳኝ አቅምና ክህሎታቸውን በሚያዳብሩባቸው የተለያዩ የኪነጥበብ አውዶችም በርካቶችን ከተሰጥዖአቸው ጋር አገናኝቷል፤ የአብዮታዊት ኢትዮጵያ ሕጻናት አምባ።
ሕጻናትን ‹የዛሬ አበባዎች፣ የነገ ፍሬዎች፣ አገር ተረካቢዎች፣› ከማለት ባለፈ፤ አበባዎቹ ሕጻናት ለፍሬ በቅተው አገር መረከብ እንዴት ይችላሉ? የሚለውን ሁሉም አስቦ ሊመልሰው የሚገባ ጉዳይ ነው። ምክንያቱም ሕጻናቱም ‹‹እምቡጦች ሎጋ ማራኪ ሸጋዎች ሕጻናት ናቸው አገር ገንቢዎች››ይላሉና፤ በንጹህ አዕምሯቸውም ‹‹ተንከባከቡን ፍሬ እንድንሆን፣ ሕጻናቶች ነን የአገር እድገቶች የነገ ኢትዮጵያ ተረካቢ አበቦች፤›› የሚል ድምጻቸውን ያሰማሉ።
የእነዚህ ሕጻናት ድምጽ በዋናነት ለወላጆች ቅርብ ነው፤ ወላጆች የልጆቻቸውን ህመም የሚታመሙ፤ ደስታም የሚደሰቱ፤ ስለነገ ፍሬያማነታቸውም አብዝተው የሚጨነቁ ናቸው። ይህ ሀቅ ነው። ዋናው ጉዳይ ይህን የሚሉ ሕጻናት ጥያቄያቸውን የሚመልስላቸው ወላጅ ከጎናቸው ሲያጡ ወይም ይሄን ማድረግ የማይችሉ ወላጆች ሲኖሩ፤ ሕጻናቱ ምን ይሁኑ? የሚለው ነው።
የኢትዮጵያ ሕጻናት አምባ ይሄን ጥያቄ መመለስ በሚያስችለው መልኩ የኢትዮጵያ ዳር ድንበር ለማስከበር ባደረጉት ተጋድሎ አባቶቻቸው የተሰውባቸውን እንዲሁም ሌሎች ማህበራዊ ችግር ያለባቸው ሕጻናትን ተንከባክቦ የማሳደግና በአገር ፍቅር አንጾ የእውቀትና ክህሎት ባለቤት አድርጎ የማውጣት ሃላፊነትም ተሰጥቶት በ1973 ዓ.ም እንደተቋቋመ መረጃዎች ያሳያሉ። በዚህ ማዕከል ታንጸው ያደጉ ሕብረ ብሔራዊ የኢትዮጵያ ሕጻናትንም አባትን በማጣት ውስጥ የአገር ፍቅርን፣ ህዝብ መውደድን ተምረዋል። ዛሬም ድረስ ከአዕምሯቸው የማይጠፋውን ዜማም እንዲህ አዚመዋል።
‹‹አንቺ እማማ ኢትዮጵያ የእኔ የእኔ (3)፣
እኔም የአንቺ አንቺም የእኔ፤
እራብ ጥማቴን አትወጂም አንቺ ጥፋቴን ሲባባ አንጀቴ፤
ኢትዮጵያ የእኔ፣ አንቺ ካለሽ ሁሉ ለምኔ፣
ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ የእኔ (3)፤››
አሳዳጊዎቻቸውንም ‹‹እማዬ፣ አባዬ›› ሲሉ ያደጉት እነዚህ ሕጻናት፤ ያ ጊቢ ብዙ ነገር ያሳለፉበት፤ ብዙ ነገር ያገኙበትና የዛሬው ማንነታቸው መሰረት የያዘበት ነውና ስለ አምባ ትዝታቸው አውርተው አይጠግቡም። ማውራት ብቻም አይደለም የአገርና ህዝብ ውለታ እንዳለባቸው ስላመኑ እነርሱን መሰል ባለብዙ ተሰጥዖ ሕጻናት በችግር ምክንያት መክነው እንዳይቀሩ የሚቻላቸውን ለማድረግ ሲታትሩ ይታያል። ከእነዚህ ውለታ ከፋዮች መካከል ደግሞ አቶ ካሌብ ፀጋዬ እና አብሮአደጎቻቸው(በእርሳቸው አጠራር እህትና ወንድሞቻቸው) ተጠቃሽ ናቸው።
የአምባው ቆይታቸውን ልክ እንደ እናት ቤታችን ነው የምንቆጥረው የሚሉት አቶ ካሌብ፤ የአስተዳደግ ሂደቱም ምንም አይነት የተደበቀ አጀንዳና ተልዕኮ የሌለው ፍጹም ኢትዮጵያዊነትን የተላበሰ፤ ልጆቹም በመልካም ስነምግባርና በንጹህ ፍቅር ታንጸው እንዲያድጉ የሚደረግበት እንደነበር ያስታውሳሉ። ሆኖም ምንም እንኳን አምባውን ሊያዘጋ የሚያስችል ምክንያት ባይኖርም የስርዓት ለውጡን ተከትሎ አምባው ወደመዘጋቱ ሲቃረብ ከአምባው እንዲወጡ ከተደረጉ የመጨረሻዎቹ ታዳጊዎች መካከል አንዱ እንደሆኑ፤ ይህ ደግሞ ምንም መጠጊያ ለሌለው አንድ ታዳጊ ከባድና ከባህር የወጣ ዓሣ አይነት ስለነበር ለከፋ ችግር እንዳጋለጣቸው ይገልጻሉ።
በዚህ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ የጠነከረ ራሱን ለማስተማርና ለመቀየር ሲችል፤ ከፊሉ ኑሮን መቋቋም ሳይችል ቀርቷል። እርሳቸውም በዚህ ውስጥ አልፈው ቀን እየሰሩ ማታ በመማር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከኮሜርስ ካምፓስ በማኔጅመንት ዲፕሎማ ይዘዋል። ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በኢንግሊዝኛ ዲግሪቸውን ሲይዙ፤ አሁን ላይ ለጀመሩት ስራ ያግዘኛል በሚል የልዩ ፍላጎት ትምህርት (ስፔሻል ኒድስ ኤዱካሽን) በሁለተኛ ዲግሪ(ማስተርስ) እየተማሩ ይገኛሉ።
አምባው፣ ብዙ ለአገርና ህዝብ የሚበጁ ዜጎች የሚፈሩበት፤ ለአገር የሚቆረቆሩና ሁሉንም ሰው በእኩል ዓይን የሚመለከቱ፤ ‹ድጋፍ ተደርጎልኛል፣ እኔኮ የኢትዮጵያ ውለታ አለብኝ፤ ህዝብ ነው ያሳደገኝ፤› የሚል መንፈስ ያላቸው ልጆች የሚያድጉበት እንደነበር የሚገልጹት አቶ ካሌብ፤ እነርሱም የዚህ ትውልድ አንድ ገጽ እንደመሆናቸው የድርሻቸውን ለመወጣት በሚል ‹‹አምባ- ትምህርት ለተቸገሩ ሕጻናት›› ማዕከልን ማቋቋማቸውን ይናገራሉ።
ማዕከሉን የማቋቋም ሀሳቡ የተጠነሰሰውና ወደተግባር የተቀየረበት ምክንያት በስራ ዓለም አዲስ አበባ የካ ክፍለከተማ ወረዳ ዘጠኝ በተለምዶው መጠለያ ተብሎ የሚጠራው አከባቢ ከኤርትራ ተፈናቅለው የመጡ፣ ባለቤታቸውን በሞት ያጡ፣ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸውና በተለያዩ ሕመም እንደልብ መስራት ያልቻሉ እናቶች ሁለትና ሶስት ልጆችን ይዘው ልጆቻቸውን ያለትምህርት ቤት ውስጥ ማስቀመጣቸውን መመልከታቸው ነበር።
ምክንያቱም በወቅቱ የመንግስት ትምህርት ቤት ልጆች ሰባትና ስምንት ዓመት ካልሞላቸው ስለማይቀበል፤ እቅም ያላቸው በግል ትምህርት ቤቶች ሲያስተምሩ፣ እነዚህ ልጆች የግል ትምህርት ቤት የቅድመ መደበኛ ትምህርት መማር ስለማይችሉ ከእድሜ አቻዎቻቸው ተለይተው በቤት ውስጥ ለመዋል ይገደዱ ነበር። ይህ ደግሞ በልጆቹ ስነልቡና ብቻ ሳይሆን ምናልባት እድሜያቸው ሲደርስ አንደኛ ክፍል መግባት ከቻሉ አንድ ብለው ፊደል መቁጠር ስለሚጀምሩ፣ ቃላት መመስረት ለምደው ከመጡ አቻዎቻቸው ጋር መወዳደር እንዳይችሉ ያደርጋቸዋል።
ከዚህ በመነሳትም እነዚህን ልጆች ቢያንስ ትምህርት ቤት እንዲውሉ ማድረግና ፊደል ማስቆጠር እንዴት ያቅተናል፤ በሚል ሀሳብ ሔኖክ የሚባል ጓደኛቸው የቤት ኪራይ ለመክፈል፣ አቶ ይታገሱ የሚባሉት ጓደኞቼን በማስተባበርም ቢሆን የትምህርት መርጃ ቁሳቁሶችን ለመቻል፣ አቶ ካሌብ ደግሞ በወቅቱ ማታ ላይ ስለሚሰሩ ቀን ነጻ ስለነበሩ ያላቸውን ሰዓት ሰጥተው ለመስራት ተነጋግረው ስራውን ለመጀመር ይወስናሉ። ሀሳቡንም በአከባቢው ላሉ እድሮች አስረዱ። የእድር አመራሮችም ሀሳቡ የተቀደሰ ቢሆንም በነጻ እናስተምራለን ማለታቸው ስራውን እንደሚያከብድባቸው በመግለጽ፤ ጠንክረው ከጀመሩት ግን ቢያንስ ችግር ያለባቸውን ሕጻናት በመለየት በኩል እንደሚረዷቸው ይነግሯቸዋል። እነርሱም የገቡትን ቃል አክብረው ስራውን ለመጀመር ዝግጁ ሲሆኑ፤ እድሮችም ሕጻናትን የመለየት ስራውን አግዘዋቸው የባሰ ችግር ያለባቸውን 75 ሕጻናት ይዘው በአንድ ጠባብ ክፍል ውስጥ በ2001 ዓ.ም ስራውን አንድ ብለው ጀመሩ።
ፊደል ለማስቆጠር የተጀመረው ስራ ግን እንደታሰበው ቀላል አልነበረም። ምክንያቱም ልጆቹ ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ቤተሰብ የመጡ ስለነበር ቁርስ እንኳን የሚበሉበት እድል አልነበራቸውም፤ ትንሽ መያዝ የቻሉትም ያደረና ልጆች ሊበሉት የማይችሉት፤ ጥሬ አሹቅና መሰል ነገሮችን ነበር የሚቋጠርላቸው። ይህ ደግሞ የህዝብና አገር ውለታን ላልዘነጉት ለእነ አቶ ካሌብ ጥሩ ስሜትን አልፈጠረላቸውም። በመሆኑም የተለያዩ አካላትንና የአከባቢውን ህብረተሰብ በማስተባበር ሕጻናቱን ቁርስ የሚያበሉበትን እድል መፍጠር እንዳለባቸው አሰቡ፤ ሂደቱ አልጋ በአልጋ ባይሆንላቸውም ተስፋ ባለመቁረጥ በአንድ ጢቢኛ ዳቦና ወተት ቁርስ ማብላት የሚችሉበትን እድል ፈጠሩ።
ወይዘሮ ሙሉወርቅ አበበ እና ወይዘሮ የሺ እሸቱ ደግሞ ማዕከሉ ለልጆቻቸው እውቀት ማዕድ ያቋደስ፣ የእነርሱንም ከሀሳብ ሸክም ያቀለለ ስለመሆኑ እማኞች ናቸው። ወይዘሮ ሙሉወርቅ አበበ፣ ከክፍለ አገር የመጣች በመሆኗ በአዲስ አበባ ቤተሰብም ሆነ ረዳት የላትም። በመስተንግዶና ልብስ አጥባ በምታገኛት ገቢ ልጇን ለማሳደግ ደፋ ቀና ብትልም የሀሳቧ ሳይሞላ ቀርቶ የቤት ኪራይ እንኳን መክፈል ሳትችል ልጇ እንደጓጓች በለጋ እድሜዋ የትምህርት ቤት ደጆችን ለመርገጥ እንዳትችል ሆነች። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንዳለች ነው በትምህርት ቤቱ የምታስተምርበትን እድል ያገኘችው። ዛሬ ላይ ልጇ የሶስተኛ ዓመት የቅድመ መደበኛ ትምህርቷን እየተከታተለች ሲሆን፤ እርሷም በትምህርት ቤቱ በተፈጠረላት እድል እንጀራ እየጋገረች ኑሮዋን ለማሸነፍ እየሰራች ትገኛለች።
ወይዘሮ የሺ እሸቱ፣ ደግሞ ቀደም ሲል ሁለት ልጆች አስተምረዋል፤ አሁንም አንድ ልጅ እያስተማሩ ይገኛሉ። ወይዘሮዋ፣ የሶስት ልጆቻቸው አባት በመሞታቸውና የሚረዳቸው ዘመድም ስላልነበራቸው በልቶ ማደር ግድ ነውና በሰው ቤት ልብስ በማጠብ የልጆቻቸውን ጉሮሮ ለመሙላት ደፋ ቀና ይላሉ። ሆኖም ከህመማቸው ጋር ታግለው እየሰሩ የሚያገኙዋት ገቢያቸው ከለት ጉርስ ተርፋ ለልጆቻቸው የትምህርት ቤት ውሎ የሚሆን ነገርን ማስገኘት አላስቻላቸውም። ለማደሪያ እንኳን ችግር ላይ ወድቀው ነበር። እስከ ክፍለከተማ ድጋፍ ቢጠይቁም፣ የበርካታ ድርጅቶችን ደጅ ቢያንኳኩም ምላሽ ስላጡ ስለልጆቻቸው ዕጣ ፈንታም ከእንባ የዘለለ መፍትሄ ማምጣት ባልቻሉበት ወቅት ነበር የማስተማር እድሉን ያገኙት። ለራሳቸውም ቢሆን በማዕከሉ አስተዳደሮችና ሰራተኞች በብዙ ተደጉመዋል።
እነዚህ እናቶች፣ ማዕከሉ የችግሮቻቸው ገመና መክደኛ የእፎይታ ጓዳቸው እንደሆነ ተነግሮለታል። ይህ ብቻ ሳይሆን ማዕከሉ እንደ አብዮታዊት ኢትዮጵያ አምባ ሁሉ የቀለም ትምህርትን ከክህሎት አቆራኝቶ፣ የአገር ፍቅርን ከህዝብ ወዳድነት ጋር አሰናኝቶ፣ ተፈጥሮ የለገሰቻቸውን ክህሎት የሚፈልጉበት አውድ ፈጥሮ እና እንደ እናት ማእድ አሰናድቶ ለህጻናቱ ምሉዕነት በሙላት የሚሰራ ስለመሆኑ ከማዕከሉ መስራችና ሰራተኞች ባለፈ የወላጆች ምስክርነት ተለግሶታል። ‹‹እንደ ትምህርት ቤት ብቻ ሳይሆን እንደ ቤተሰብ ነው›› ሲሉም፤ ለሰው ልጅ ስብዕና መሰረታዊ የሆነውን ፍቅርና ስነምግባር አስይዞ የሚያሳድግ ስለመሆኑም ወላጆች ይገልጻሉ።
አቶ ካሌብ ማዕከሉን አስመልክቶ እንደሚያብራሩት፤ ስራውን ሲጀምሩት በዚህ መልኩ በዘላቂነት እንሰራዋለን በሚል ሳይሆን፤ ለተደረገልን ነገር ጥቂት ማድረግ ብንችል በሚል የሀሳብ መነሳሳት ነበር። ሆኖም የወላጆች ሞራልና ድጋፍ ስራውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አድርጓቸዋል። ምክንያቱም በእነርሱ ጀማሪነትና በህዝብ ድጋፍ እየተጓዘ ያለው ስራቸው እየከበደ፤ ዓመት ዓመትን ሲወልድም የቤት ኪራዩም እየጨመረ ሄደ። በተለይ ሰፊ ድጋፍ ሲያደርጉላቸው የነበሩ የጣሊያን ትምህርት ቤትና መምህራን ስራቸውን አጠናቀው ከአገር መውጣትን ተከትሎ ችግራቸውን ከበደባቸው። ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንዲሉም፤ በ2007 ዓ.ም ለቤት ኪራዩ 25 ሺህ ብር እንዲከፍሉ ይነገራቸዋል። በዚህ ሁኔታ አቅም ፈትኗቸው ተስፋ በመቁረጥ ወላጆችን ሰብስበው ስለጉዳዩ አስረዱ።
ሆኖም የወረዳው ትምህርት ጽሕፈት ቤት አይዟችሁ የሚል ማበረታቻና የአከባቢው ህዝብ ብሎም የተማሪዎቻቸውና የወላጆቹ የተስፋ አድማስ ተዳምሮ ጉልበት ሆኖ ችግሩን ተቋቁመው ማለፍ የሚችሉበትን አቅም ፈጠረላቸው። የሚሰሩት ስራ ትርጉም እንዳለው እንዲረዱም ስላደረጋቸው የአባላት መዋጮን ተግባራዊ አደረጉ። የቤት ኪራዩ ጉዳይም በአማላጅ ተቀነሰላቸው። ከዚህ ሁሉ በኋላ ራሳቸውን ለማስተዋወቅ በእነርሱም በህብረተሰቡም ጥረት ተሰራ፤ ድጋፍ የሚያደርጉላቸው አካላትም እየተበራከቱ መጡ።
ይህ ሂደት ግን አንድ ትልቅ ነገርን ያሳየ፤ መልካም አርዓያ የሆነ ትውልድም ራሱን መተካት እንደሚችል አረጋገጠ። ምክንያቱም ተቋሙ ፈተና ላይ በወደቀ ጊዜ በተቋሙ ያለፉ ሕጻናት ድንኳን ጥለው ‹‹ያሳደገን ትምህርት ቤት ሊፈርስብን ነው እርዱን›› በሚል በለጋ እድሜ የማይታሰብ ተግባር አከናወኑ፤ ለምነው ያገኙትን ገንዘብም አንድ የድምጽ ማጉያ እና ጄኔሬተር ገዝተው እያከራያችሁ ገቢ አግኙበት በማለት ለትምህርት ቤቱ አበረከቱ። በዚህም ባለውለታዎች ከራሳቸው አጉድለው የደገፏቸው ሕጻናት ከዛሬው የአገርና ትውልድ ውለታ አለብን የሚል አስተሳሰብን መያዛቸው ተገለጠ።
እነዚህ ልጆች እንደማንኛውም ልጅ የሚገባቸውን አግኝተው እየተማሩ እንዲያድጉ ማድረግን ዓላማው ያደረገው ይህ ማዕከል፤ ሕጻናቱ ከቀለም ትምህርት ባለፈ ከልጅነታቸው ተሰጧቸውን እያጎለበቱና ዝንባሌያቸውን እንዲለዩ ለማስቻል የሚያግዙ የተለያዩ የሙያ ማጎልበቻ ስልጠናዎች ላይ እንዲሳተፉ ያደርጋል። በእነዚህ ሙያዎች ሲሳተፉም ከመስራቾቹም ሆነ ማዕከሉን የጎበኙ በጎ ፈቃደኛ ባለሙያዎች እየተገኙ የሚያስተምሯቸው ሲሆን፤ ለምሳሌ፣ በስዕል፣ ሙዚቃ፣ ድራማ፣ በእግር ኳስና ሌሎችም ውጤታማ የሆኑ ታዳጊዎችን ማፍራት ተችሏል።
ይሄን መሰል ትውልድ እያፈራ በተጓዘባቸው ዓመታት ከ400 ያላነሱ ሕጻናትን አስተምሮ ወደአንድኛ ክፍል ማሳለፍ ችሏል። የመጀመሪያ ዙር ተማሪዎቻቸውም ዘንድሮ 10ኛ ክፍል የደረሱ ሲሆን፤ ከአምባው የሚወጡት አብዛኞቹ ልጆችም ውጤታማና የደረጃ ተማሪዎች ናቸው። የእነዚህ ሕጻናት ሕልምም ተምረው ሲጨርሱ እነርሱን ለዚህ ያደረሳቸውን ትምህርት ቤት በሙያቸው ማገዝ፤ የበለጠ እንዲያድግና ራሱን ችሎ የድሃ ልጆችን እስከ 12ኛ ክፍል የሚያስተምርበት እድል መፍጠር ነው። ታዲያ ይህ እውን እንዲሆን ከማን ምን ይጠበቅ ይሆን?
ይህ ሀሳብ የማዕከሉ መስራቾች፣ መምህራንና የተማሪ ወላጆችም ጭምር ሆኖ እንዲህ ይደመጣል፤ አሁንም ይሄን እድል ያላገኙ በርካታ ወላጆችና ሕጻናት እድሉን እንዲያገኙ አንድም ማዕከሉን መደገፍና የተሻለ የሚሰራበትን አቅም እንዲፈጥር ማስቻል፤ ሁለተኛም መሰል ተቋማት እንዲበራከቱ ማድረግ ይገባል። ለዚህ ደግሞ ግለሰቦች፣ ድርጅቶችና የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት የሚጠበቅባቸውን ማበርከት ይኖራባቸዋል።
ምክንያቱም ይህ ማዕከል ሕጻናትን እየመገቡ ከማስተማር ባለፈ፤ እናቶችንም በማታ ትምህርት ፊደል ሲያስቆጥር፣ የሙያና የስራ ባለቤት እንዲሆኑም የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል። በዚህም ከቦሌ ክፍለከተማ ጋር በመጻጻፍ በ2004 ዓ.ም 30 እናቶች የልብስ ስፌት ሙያ ስልጠና እንዲያገኙ አድርጓል። ለስልጠናውም ለትምህርት ቤቱ በድምሩ ሦስት ሺህ ብር፤ ለትራንስፖርታቸውም በአራት ሺህ ብር ሀይገር ባስ ተከራይቶ፣ እንዲሁም እናቶቹ ስራ ፈትተው ስልጠናውን ስለሚወስዱ መደጎሚያ በሚል ለያንዳንዳቸው 150 ብር እየተከፈላቸው ነው። በተመሳሳይ በ2005 ዓ.ም ግሎባል ኢንፋንት ከሚባል ድርጅት ጋር በመጻጻፍ 58 እናቶች በምግብ ሙያ፤ በ2006 ዓ.ም ደግሞ 56 እናቶች በጸጉር ሙያ እንዲሰለጥኑ በማድረግ፤ በድምሩ ከ150 ያላነሱ እናቶች በተለያዩ ሙያዎች እንዲሰለጥኑ አድርጓል።
ከዚህ ባለፈም፣ ከሚያስተምራቸው ሕጻናት 10 በመቶ ያክሉ አካል ጉዳተኞች የሆኑት ይህ ማዕከል፣ በማዕከሉ የሚጠቀሙባቸው በርካታ ወንበርና ጠረጴዛዎች ከጣሊያን ስኩል፤ 11 ያክል ኮምፒውተሮችን ከጤና ጥበቃ ሚንስቴር ያገኙ ሲሆን፤ በቅርቡም የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ያለባቸውን የቤትና የቦታ ችግር ለማቃለል ቤት እንዲሰጣቸው ውሳኔ አሳልፏል። ለዓመታት ተዘግቶ የኖረ አንድ ጊቢ ከነቤቱ እንዲሰጣቸው ተብሎ ነበር። ነገር ግን ባለቤት ነኝ ባይ መንግስታዊ ተቋም ፈቃደኛ ባለመሆኑ፤ ማዕከሉም ለቦታው የአንድ ዓመት ውል ገብቶ 165 ሕጻናትን ተቀብሎ እያስተማረ ይገኛል። ይህ ደግሞ ቦታውን ሲያገኙ ስራቸውን ለማስፋት የነበራቸውን ተስፋ ስለሚጎዳ የሚመለከተው አካል እልባት ሊሰጠው ይገባል።
አዲስ ዘመን አርብ ህዳር 26/2012
ወንድወሰን ሽመልስ