የጥራት መሰረተ ልማት ሀገራት ወደ ውጪ የሚልኳቸውን ምርቶች ጥራት በማስጠበቅ በአለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ በርካታ ሀገራትም ምርቶቻቸው አለም አቀፍ ገበያውን ሰብረው እንዲገቡና በገበያ ውስጥ ፀንተው እንዲቆዩ የጥራት መሰረተ ልማታቸውን በየጊዜው እየፈተሹ ያዘምናሉ፡፡
ከኢትዮጵያ ወደ ውጪ ሀገራት የሚላኩ ምርቶችን ጥራትና ደረጃቸውን የሚቆጣጠሩ ተቋማት ቢኖሩም ወቅቱ ከሚጠይቀው ቴክኖሎጂና ሀገሪቱ ከደረሰችበት የኢኮኖሚ አድገት እኩል ሊራመዱ አልቻሉም፡፡ የሚሰጡት የጥራት፣ደረጃና ልኬት አገልግሎትም ውስን በመሆኑ ሀገሪቱ የግብርና ምርቶችን፣ቆዳንና ጨርቃጨርቆችን ብቻ ለውጪ ገበያ ታቀርባለች፡፡ የጥራት መሰረተ ልማት በበቂ ሁኔታ አለመሟላት ደግሞ የዘርፉ ዋነኛ ችግር ሆኖ ቆይቷል፡፡
የአገሪቱን የጥራት መሰረተ ልማት ለማሻሻል ከአለም ባንክ በተገኘ የ50 ሚሊዮን ዶላር ብድር የአምስት ዓመት ፕሮጀክት ተነድፎ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ሲደረግ ቆይቷል፡፡ ፕሮጀክቱ አጠቃላይ ሀገራዊ የጥራት መሰረተ ልማትን ለማሳደግ፣ በጥራት ልማት ዘርፉ የግሉን ዘርፍ ለማሳተፍና የአስተዳደር፣ ቁጥጥርና ግምገማ ስርዓት ለመዘርጋት ያስችላል፡፡
ፕሮጀክቱ በአሁኑ ወቅት በስራ ላይ ያለውን የብሄራዊ ጥራት መሰረተ ልማት አምራቾችና አገልግሎት አቅራቢዎች የሚሰጡት የጥራት ማረጋገጥ አገልግሎት በአለም አቀፍ ደረጃ በሁሉም ዘርፍ አውቅናና ተቀባይነት እንዲኖረው እንዲሁም የሰው ኃይልና የዘመናዊ መሳሪያ አቅማቸውን ማሳደግ የሚያስችል ነው፡፡
አምራቹና በጥራት የማምረት እንዲሁም አገልግሎት ሰጪው ጥራት ያለው አገልግሎት የመስጠት አቅማቸው እንዲሁም በጥራት አረጋጋጭ ድርጅቶች በኩል የሚሰጡትን የጥራት ማረጋገጥ አገልግሎት የመጠቀም ፍላጎትን በማሳደግ አለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን ለማጎልበት የሚያስችል የአቅም ግንባታ ስራም ያከናውናል፡፡
ፕሮጀክቱ የአገሪቱን የጥራት መሰረተ ልማት በማሻሻል በተለይ የወጪ ምርቶችን ጥራት በማሳደግ በአለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ትልቅ እገዛ እንደሚኖረው በርካታ ወገኖች ይስማማሉ፡፡
በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የጥራት መሰረተ ልማት ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ወንድወሰን ፍሰሃ እንደሚሉት፤ፕሮጀክቱ በሀገሪቱ ጠንካራ የጥራት መሰረተ ልማት አሰራር እንዲፈጠር እገዛ ይኖረዋል፡፡ በተለይም እየሰፋ የመጣውን የኢንዱስትሪ ፍላጎት ሊያሟላ የሚችል የጥራት መሰረተ ልማት አገልግሎት መዘርጋት ያስችላል፡፡የጥራት ማነቆዎችን በመፍታት የኢትዮጵያ ምርቶች በአለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ ወደ ውጪ ሀገራት ተልከው በጥራት ጉድለት ምክንያት የሚመለሱ ምርቶችን ችግር ለዘለቄታው ይፈታል፤ ማንኛውም ምርት ደረጃውን ጠብቆ እንዲመረትም ይረዳል፡፡
እንደ አስተባባሪው ገለፃ፤ በፕሮጀክቱ የሚካተቱ ዘርፎችም ቆዳ፣ ጨርቃጨርቅና የግብርና ምርቶች ሲሆኑ፣ ፕሮጀክቱ የተዘጋጀው የጥራት መሰረተ ልማት አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት አቅማቸውን በማጥናትና በኢንዱስትሪው በኩል ያለውን ፍላጎት በመለየት ነው፡፡
የጥራት መሰረተ ልማት ተቋማት፣ የጥራት ቁጥጥር ባለስልጣናትና ምርቶችን ወደ ውጪ ሀገራት የሚልኩ የግል ዘርፎች የፕሮጀክቱ ዋነኛ ተጠቃሚዎች መሆናቸውንም አስተባባሪው ይጠቁማሉ፡፡
ፕሮጀክቱ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ አስራ አምስት ወራትን አስቆጥሯል የሚሉት አስተባባሪው፤ በነዚህ ወራት ወስጥ የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ፣ ብሄራዊ አክሪዲቴሽን ጽ/ቤት፣ የብሄራዊ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት እና ተስማሚነት ምዘና ድርጅት በመሳሪያ፣ በላብራቶሪ፣ በሰው ኃይል ስልጠናዎችና ከሌሎቸ ሀገራት ጋር የልምድ ልውውጥ በማድረግ አቅማቸው እንዲገነባ መደረጉን ያብራራሉ፡፡
በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የግል ንግድ ዘርፍ ከፍተኛ ባለሙያ ወይዘሮ ስንዱ ፋኑኤል እንደሚናገሩት፤ የጥራት መሰረተ ልማት ፕሮጀክቱ በዋናነት የአገሪቱን ኤክስፖርት መር የንግድ ስትራቴጂ ይደግፋል፡፡ ፕሮጀክቱ የተጀመረበት ዋነኛ አላማም ሀገሪቱ ወደ ውጪ የምትላካቸው ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማድረግ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ምርቶቿን ወደ ውጪ ሀገራት ለመላክ በርካታ ገንዘብ ወጪ ታድርጋለች፡፡ ለግሉ ዘርፍም በመንግሥት በርካታ ድጋፎች ይደረጋሉ፡፡ ወደ አምራች ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር እቅድ ተይዞ መሰራት ከተጀመረም ብዙ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ይሁን እንጂ እስከ አሁን ምርቶቹ የዓለም ገበያውን ሰብረው መግባት አልቻሉም፡፡ ከዚህ አኳያ ፕሮጀክቱ የጥራት መሰረተ ልማት አገልግሎትን በማሳደግ ምርቶቹ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡
ሀገሪቷ በርካታ ምርቶችን ወደ ውጪ ሀገራት የመላክ ፍላጎት እንዳላት የሚናገሩት ባለሙያዋ፤ የምርት ጥራት ስርዓትና ቁጥጥር ደካማ መሆን ምርቶቹ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ አላማስቻላቸውን ይጠቁማሉ፡፡ በተለይም የጥራት ቁጥጥር የሚያደርገው ተቋም በዝቅተኛ ደረጃ ላይ መገኘት ምርቶቹ በዓለም ገበያ እንደልብ እንዳይቀርቡ እንቅፋት ሆኗል ይላሉ፡፡
በመሆኑም ፕሮጀክቱ ኤክስፖርት መር የንግድ ስትራቴጂውን በመደገፍ የቆዳ፣ ጨርቃጨርቅና የግብርና ምርቶች ጥራታቸውን ጠብቀው ለዓለም ገበያ እንዲቀርቡ ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግም ነው ባለሙያዋ ያመለከቱት፡፡ በቆዳ፣ ጨርቃጨርቅና የግብርና ምርቶች ላይ ፕሮጀክቱ አተኩሮ የሚሰራውም ቀደም ሲል በእነዚህ ዘርፎች ላይ ሀገሪቱ ትኩረት አድርጋ ስትስራ በመቆየቷና በነዚህ ምርቶች የገበያ ተደራሽንቷ ከፍተኛ በመሆኑ ነው ይላሉ፡፡ ሁሉንም ምርቶች ተደራሽ ማድረግ ስለማይቻልና በውስን ሃብት ስለሚሰራ ፕሮጀክቱ በዋናነት በሶስቱ ዘርፎች ላይ አተኩሮ እንደሚሰራም ይጠቅሳሉ፡፡
ወይዘሮ ስንዱ እንደሚሉት፤ ከአምስት ዓመት በኋላ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ነባሩን የጥራት መሰረተ ልማት በማሻሻል፣ የተለያዩ መሳሪያዎችንና ባለሙያዎችን በበቂ ሁኔታ በማሟላት ብሎም የምርቶቹን ገዢዎች ፍላጎት በመለየት የተሻለ የጥራት መሰረተ ልማት አገልግሎት መስጠት ያስችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በቂ የደረጃ አሰጣጥ፣ ምርመራና ሰርተፊኬሽን እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው የአክሪዲቴሽንና የልኬት ስርዓት እንዲኖር ይረዳል፡፡ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርም ሌሎች አጋሮችን በማሳተፍና ተጨማሪ ሃብቶችን እንደ ግብዓት በመጠቀም በቆዳ፣ ጨርቃጨርቅና የግብርና ምርቶች የወጪ ንግድ ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ይችላል፡፡
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዛብሔር፤ የጥራት መሰረተ ልማት አገልግሎት ሀገሪቷ የምትገኝበት ደረጃ ዝቅተኛና ከደረሰችበት የኢኮኖሚ እድገት ጋር የሚመጣጠን አይደለም ይላሉ፡፡ በቀድሞው ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ስር የነበሩት የጥራት ደረጃ አረጋጋጭ ተቋማትም የመንግሥት ድጋፍ አግኝተው ለመስራት ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸውን አስታውሰው፣ እነርሱን የሚቆጣጠረው አካል ግን ድክመት እንደነበረበት ይናገራሉ፡፡ ተቋማቱም በንፅፅር ሲታዩ ለሀገሪቱ ዕድገት የሚመጥኑ አልነበሩም ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
እንደ ሚኒስትሯ ገለፃ፤ ከጥራት መሰረተ ልማት አገልግሎት ዝቅተኛነት ጋር በተያያዘ በተለያዩ ጊዚያት በርካታ የጥራት ችግሮች ሲያጋጥሙ ቆይተዋል፡፡ መንግሥትም ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት የብሄራዊ
ጥራት መሰረተ ልማት አገልግሎትን ለማጠናከር እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ለዚህም ከዓለም ባንክ በተገኘ ብድር የተጀመረው ፕሮጀክት አንዱ ማሳያ ሲሆን፣ መንግሥትም በከፍተኘ ደረጃ ገንዘብ በመመደብ የጥራት መሰረተ ልማትን ለማሳደግ እየሰራ ነው፡፡
በተለይም ከግንባታ ስራዎች ጋር በተያያዘ የተለያዩ መሳሪያዎች ጥቅም ላይ መዋላቸውን ሚኒስትሯ ጠቅሰው፣ እንዲያም ሆኖ የጥራት ችግሮች እያጋጠሙ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ ለዚህም ሲባል የጥራት መሰረተ ልማትን ለማጠናከር መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ይላሉ፡፡ ስራው ጅምር ላይ መሆኑን በመጥቀስም፣ የሚፈለገው ደረጃ ላይ እስኪደርስ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ለሀገሪቷ ኢኮኖሚ የሚመጥን የጥራት መሰረተ ልማት መገንባት ያስፈልጋል ይላሉ፡፡
ፕሮጀክቱን ለማስፈፀም ከዓለም ባንክ የተገኘው ብድር ከፍተኛ መሆኑን የሚገልፁት ሚኒስትሯ፣ የጥራት መሰረተ ልማት አገልግሎቱን ለማስፋትና ተደራሽ ለማድረግ ገንዘቡ በአግባቡ ስራ ላይ ሊውል እንደሚገባም ያስገነዝባሉ፡፡
እንደ ሚኒስትሯ አነጋገር፤ የጥራት መሰረተ ልማትን ለማሻሻል የሚያግዙ አብዛኞቹ መሳሪያዎች በውድ ዋጋ የሚገዙ እንደመሆናቸው መሳሪያዎቹን በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ በፕሮጀክቱ የሚከናወኑ ስራዎች አንዳንዶቹ በሂደት ላይ ቢሆኑም አንዳንድ የአፈፃፀም ችግሮች ይታይባቸዋል፡፡
ፕሮጀክቱን በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ማጠናቀቅ እንደሚያስፈልግ አስገነዝበው፣ ይህም ሁለተኛውን የፕሮጀክቱን ምዕራፍ ለመጀመር እንደሚያስችል ይጠቁማሉ፡፡
የብሔራዊ ጥራት መሰረተ ልማት ፕሮጀክት ከቀድሞው ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር (የአሁኑ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ) ወደ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እንደሚተላለፉ በሽግግር ውስጥ መጓተቶችና ሌሎች ችግሮች እንዳይኖሩ ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ይህን አስቀድሞ በመገንዘብ ለመስራት ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ ቀደም ሲል የተጀመሩ ስራዎችም የበለጠ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አበክሮ ይሰራል፡፡ በንግድና ኢንዱስትሪ ዘርፍ ከተሰማሩ የግል ባለሃቶችም ጋር በቅርበት በመስራት የሚፈልጉትን አገልግሎት እንዲያገኙ ጥረት ያደርጋል፡፡
የብሄራዊ ጥራት መሰረተ ልማት ፕሮጀከት ላለፉት 15 ወራት በቀድሞው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሲመራ ቆይቶ በቅርቡ በተደረገ የመንግሥት መዋቅር ለውጥ ምክንያት ፕሮጀክቱን በባለቤትነት የመምራትና የማስፈፀም ኃላፊነት ለንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መተላለፉ ይታወቃል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 23/2011
አስናቀ ፀጋዬ