አዲስ አበባ፡- በአገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች እየተደረጉ የሚገኙት የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ኢንቨስትመንትን በመሳብ ከፍተኛ መነሳሳት መፍጠራቸውን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገለጸ::
ዋና መቀመጫውን በእንግሊዙ ለንደን ከተማ ያደረገው ‹‹የኢንቨስት አፍሪካ ማህበር›› አባላት የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለመመልከት በኢትዮጵያ ተገኝተው ውይይት ባካሄዱበት ወቅት የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አበበ አበባየሁ እንደገለጹት፤ በአገሪቱ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ሁኔታን ለማሻሻል እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ለልዑካን ቡድኑ መነሳሳትን ፈጥረዋል::
ኢኪዮቲይ ፎር አፍሪካ ኃ/የ/የ/ማ ዳይሬክተር እና የኢንቨስት አፍሪካ ማህበር ቡድን አባል ጀረሚይ ሊፍሮይ በኢትዮጵያ ያለውን የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለመመልከት መምጣታቸውን ገልጸው፤ በግብርናው ዘርፍ ሰፊ ሃብት እንዳለ መገንዘባቸውን ፤ በተለይም በግብርና ውጤቶች ማቀነባበርና በወተት ምርት ያለውን ሁኔታ በማየት በቀጣይ በዘርፉ ለመሰማራት እንደሚወስኑ ተናግረዋል::
ከኢትዮጵያ መንግስት እና ኩባንያዎች ጋር የጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ ተግባቦት ለመፍጠር እንደሚያስቡ የገለጹት ሊፍሮይ፤ ለውጭ ኢንቨስተሮች ዝግ የነበሩ የተለያዩ ዘርፎች አሁን ክፍት መደረጋቸው የኢንቨስት አፍሪካ ማህበር አባላት ፍላጎታቸው በኢትዮጵያ ላይ እንዲሆን ትኩረት ማሳደሩን ጠቁመዋል::
ኮሚሽነሩ ኢንቨስት አፍሪካ ማህበር የውጭ ኩባንያዎች በአፍሪካ ኢንቨስትመንቶች እንዲያሰፉ የሚያስችል ማህበር መሆኑን ጠቅሰው፤ የማህበሩ የሰሞኑ ጉብኝትና ውይይት በአገር ውስጥ ያሉ የኢንቨስትመንት አጋጣሚዎች ምን እንደሆኑ የማጣራት፣ ለአባላቶቹም አማራጭ ዘርፎቹን የማስተዋወቅ ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል::
በኢትዮጵያ በኩል ከየተቋማቱ የተውጣጡ ሚኒስትሮች የተገኙ ሲሆን፤ በአይሲቲ፣ በሎጅስቲክስ፣ በትራንስፖርት፣ በግብርና፣ በማዕድን እና በሃይል አቅርቦቶች የሚኖሩ አማራጮችን ለልዑካን ብድኑ ገለጻና ማብራሪያ መደረጉን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል::
ኮሚሽነሩ የቡድኑ አባላት በኢንቨስትመንት ዘርፉ ተሰማርተው ተወዳዳሪ እና ምርታማ መሆን ፍላጎት ማሳየታቸውን ገልጸው፤ ለሶስት ቀናት በሚደረገው ውይይት ከሚመለከታቸው የዘርፍ መስሪያ ቤቶች ጋር ምክክር እንደሚደረግ ጠቁመዋል::
የለንደኑ ማህበር የቦርድ አባልና የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ፤ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት በተለያዩ ዘርፎች ኢትዮጵያ ውስጥ የተሰማሩ እና ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው ኩባንያዎች የተካተቱበት መሆኑን ጠቅሰው፤ የህክምና መሳሪያዎችን ለማምረት የሚያስችል ፋብሪካ ለመትከል ውሳኔ ላይ የደረሰ ኩባንያ እንዳለና በቆይታቸው ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ያለችበትን ደረጃና ያሉ አማራጮችን እንደሚመለከቱ አብራርተዋል::
ኢንቨስት አፍሪካ ማህበር 400 የሚደርሱ ከተለያዩ አገራት የተወከሉ ባለሃብቶችና ትላልቅ ኩባንያዎች አባል የሆኑበት ማህበር ሲሆን፤ አፍሪካ ውስጥ ኢንቨስት ለማድረግ የሚፈልጉ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ባለሃብቶችን ያቀፈ ነው::
አዲስ ዘመን ህዳር 24/2012
ዘላለም ግዛው