ሻሸመኔ፡- የአካል ጉዳተኞች መብቶች እንዲከበሩና ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን የሰራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ:: የአካል ጉዳተኞች ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ27ኛ ጊዜ ትናንት በምዕራብ አርሲ ዞን፣ ሻሸመኔ ከተማ ተከብሯል::
የሰራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ጌታሁን አብዲሳ፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለይም ከለውጡ ጋር ተያይዞ መንግሥት አካል ጉዳተኞችን ከልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል:: ሚኒስቴሩ በአዋጅ በተሰጡት ኃላፊነቶችና በተለያዩ ሕግጋት እንዲሁም ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች መሰረት የአካል ጉዳተኞችን የእኩል ዕድል ተሳታፊነትና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑንም ገልፀዋል::
ከዚህ በተጨማሪም፣ የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነትና ተሳትፎ ማሳደግ የብዙ ባለድርሻ አካላት ኃላፊነት ቢሆንም፤ የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ በበላይነት የሚያስተባብር የመንግስት ተቋም ተደራጅቶ በርካታ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል::
የአካል ጉዳተኞችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እውን ማድረግ የሁሉም የመንግስት አካልና የእያንዳንዱ የህብረተሰብ ክፍል አጀንዳና ኃላፊነት መሆኑን ጠቁመው፤ በሕግ ኃላፊነት ከሰጣቸው አስፈፃሚ አካላት በተጨማሪ የልማት ተቋማትና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች፣ የሲቪል ማህበራትና መላው ኅብረተሰብ ትልቅ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ አቶ ጌታሁን ጠይቀዋል::
የኦሮሚያ ክልል የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ጀሚላ ሲሚብሩ በበኩላቸው፣ በሕገ መንግስቱ የተደነገጉትን የአካል ጉዳተኞች መብቶች ወደ ተግባር ከመለወጥ አኳያ ያለውን ውስንነት ለመቅረፍ ከለወጡ ወዲህ ሁሉም የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በትኩረት መስራት መጀመራቸውን ገልጸዋል::
የአካል ጉዳተኝነት በዘርና በሃይማኖት የተወሰነ አለመሆኑንና በተለያየ መልኩ ማንኛውም ሰው ላይ ሊከሰት የሚችል መሆኑን አመልክተው፤ አካል ጉዳተኞቹም አልችልም ከማለት ይልቅ ብቃታቸውን በማሳየት የሚችሉ መሆናቸውን ማረጋገጥ እንዳለባቸው አስረድተዋል::
‹‹ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀንን የምናከብርበት ዋናው ዓላማ ስለአካል ጉዳተኞች መብት ለማህበረሰቡ ለማስተዋወቅ እንዲሁም የአካል ጉዳተኞች ደህንነትን በሁሉም የማህበረሰብ ልማት እንቅስቃሴ ውስጥ ለማስረፅ ነው›› ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማህበራት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ምህረት ንጉሴ ናቸው::
እንደርሳቸው ገለፃ፣ ግንዛቤን በማስፋት በማህበራዊ፣ በፖለቲካዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በባህላዊ ጉዳዮች ውስጥ የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ ለማጐልበት ጥረት ይደረጋል:: በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ የአካል ጉዳተኞችን እኩልነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአካል ጉዳተኞች መብት ኮንቬንሽንና የአፍሪካ የአካል ጉዳተኞች መብት ድንጋጌዎች ጸድቀዋል::
ከበዓሉ ተሳታፊዎች መካከል የአዲስ አበባው ተስፋዬ ገብረማሪያም ኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞችን ያሳተፈ ሁለንተናዊ ልማት ለማካሄድ ዓለም አቀፋዊ ድንጋጌዎችና እንዲሁም አገር አቀፍ ሕግጋትንና ፖሊሲዎችን የፈረመችና ያወጣች ቢሆንም ተግባራዊነታቸው ላይ ግን ብዙ ችግሮች እንዳሉ ተናግሯል::
‹‹የአካል ጉዳተኞች በተለይ የአመራር ሠጪነት ሚናቸው እጅግ አነስተኛ ነው:: በኢትዮጵያውያን አካል ጉዳተኞች ላይ የሚደርሰው መገለልና የተጠቃሚነት ክፍተት ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም:: ይህን ችግር ለማቃለል መንግስት ብቻ ሳይሆን የግሉ ዘርፍ ባለሃብቶችን ጨምሮ መላው ህዝቡ ተገቢውን ኃላፊነት እንዲወጣ ግንዛቤን የማስፋት ሥራው በአግባቡ መሰራት አለበት›› ብሏል::
የዘንድሮው የአካል ጉዳተኞች ቀን የተከበረው ‹‹የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎና መሪነት በማጎልበት የ2030ን የልማት አጀንዳን ውጤታማነት እናረጋግጣለን›› በሚል መሪ ቃል ነው::
አዲስ ዘመን ህዳር 24/2012
ምህረት ሞገስ