ባለዘረመሉን ጥጥ (ቢቲኮተንን) በኢትዮጵያ ለማልማት ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ አዳዲስ ህጎች እንዲወጡና ነባሮቹም እንዲሻሻሉ ተደርጓል። ከህግ ማሻሻያዎቹ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዓመታትን የፈጀ ምርምርና ሙከራ ተደርጓል። በመጨረሻም ከህንድ የመጡ ሁለት ባለዘረመል የጥጥ ዝርያዎች አገሪቱ ያስቀመጠቻቸውን የደህንነት መስፈርቶች በማሟላታቸው ወደ ልማት እንዲገቡ ተፈቅዷል።
በጋምቤላ ክልል አኙዋክ ዞን አተቲ ቀበሌ በጥጥ ግብርና ላይ የተሰማሩት “የኪዳኔ ወልደማርያም እርሻ ልማት ”ባለቤት አቶ ኪዳኔ ወልደማርያም ባለዘረመሉ ጥጥ እንደተፈቀደ ዘሩን ከህንድ በማምጣት በ35 ሄክታር መሬት ላይ መዝራታቸውን ይናገራሉ።
ባለዘረመሉ ጥጥ ለልማቱ ፈተና የሆነውን ትል ለመከላከል ከአራት እስከ አምስት ጊዜ የሚደረገውን የኬሚካል ርጭት እንዳስቀረውና፣ በመደበኛ ዘር ይመረት ከነበረው ከሁለት እጥፍ በላይ ምርት እንዳስገኘና በጥራትም የተሻለ መሆኑን ይናገራሉ።
ባለዘረመሉ ጥጥ ውጤታማ ቢሆንም ከፍተኛ የዘር አቅርቦት ችግር መኖሩንና አልሚው ዘሩን የሚያገኘው በዶላር ገዝቶ በመሆኑ የውጭ ምንዛሪ ችግር እንዳለም ያብራራሉ፡፡
አንድ ኪሎ ዘር 24 ዶላር ነው። ማንኛውም ገበሬ ሊጠቀመው አይችልም በመሆኑም መንግስት ዘሩ በቅናሽ የሚቀርብበትን ስርዓት መዘርጋት አለበት ሲሉ ያመለክታሉ።
የግብርና ባለሙያው አቶ ሀዱሽ ግርማይ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ገበሬዎች ዘሩን በየዓመቱ ገዝተው ጥጡን ማልማት ያስቸግራቸዋል። በዚህ ስጋትም ባለዘረመል ጥጡ ውጤታማ እንደሆነ ቢረዱም አላለሙትም። በሌላ በኩልም አዘራሩና የልማት ሂደቱ ለአምራቾቹ በተሟላ ሁኔታ ግንዛቤ አልተፈጠረም።
ቴክኖሎጂውን በሚፈለገው ደረጃ ለመጠቀም ዘረመሉን በአገሪቱ ነባር ጥጦች ውስጥ ማስገባትና ማለማመድ፣ በአገር ውስጥ የሚገኝበት አሰራር ተግባራዊ ማድረግ፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡
በውጭ አገር ዘር አቅራቢዎች ላይ ጥገኛ ሆኖ ልማቱን ማካሄድ ቴክኖሎጂው በየጊዜው ስለሚለዋወጥ ውጤታማ ለመሆን አስቸጋሪ እንደሆነም ባለሙያው ይናገራሉ።
በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የባዮቴክኖሎጂ ግብርና ምርምር አስተባባሪ ዶክተር ታደሰ ራባ ነባሩን የጥጥ ዝርያ ከትል ለመከላከል እስከ ስምንት ጊዜ የኬሚካል ርጭት ይደረግ እንደነበር አስታውሰው፤ አዲሱን አንዱን ኪሎ ግራም በ26 ዶላር ቢገዛም ትሉን ለመከላከል ኬሚካል ርጭት ስለማይኖርና ምርቱም ብዙ ስለሆነ ውድ ነው የሚለው ሀሳብ ትክክል አለመሆኑን ይናገራሉ።
የዘር አቅርቦት አልሚው በሚፈለገው ጊዜ መቅረብ እንዳለበት እናምናለን ይህንንም ለማድረግ ከውጪ ዘሩን ለማስመጣት የገበያ ሰንሰለት ለመፍጠር እየተሰራ ነው። ሆኖም በአገር ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ፍላጎት ሳይፈጠር ዲቃላ የጥጥ ዝርያዎችን ማምረት አዋጭ ባይሆንም ምርምር እያደረግን ነው ይላሉ።
እንደ አስተባባሪው ጥቆማ፤ ሁለቱን የጥጥ ዝርያዎች ከህንድ በማምጣት በሰባት ቦታዎች ከፍተኛ ምርምር ከተደረገና የጎንዮሽ ችግር እንደሌለባቸው ከተረጋግጠ በኋላ ፍቃድ በማግኘት ወደልማት እንዲገቡ ሆኗል። በጥራትና በምርታማነት ከነበሩት የጥጥ ዝርያዎች የተሻለ መሆኑን በዘር አጽዳቂ ኮሚቴ ተረጋግጧል። ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጣ ቡድንም የልማቱን ውጤታማነት ክትትል እያደረገ ይገኛል::
የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ምርት ግብዓት ኢንስቲትዩት የጥጥ ልማት ዳይሬክተር አቶሳምሶን አሰፋ በበኩላቸው፤ ባለዘረመል ጥጡ ያለኬሚካል ርጭት ትሉን መከላከል ማስቻሉን፤ የጥጡን ዘር ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ልማቱን ለማስፋት ግብረ ሀይል ተቋቁሞ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
ባለዘረመሉ ጥጥ የባክቴሪያን ዘረመል በመውሰድ የግብርና ባዮቴክኖሎጂን በመጠቀም በጥጡ እንዲገባ ከተደረገ በኋላ የገባው የባክቴሪያ ዘረመል የጥጥ ጓልን በመብላት ለልማቱ ፈተና የሆነውን ትል ይከላከላል። ይህ እስከስምንት ጊዜ የሚደረገውን የኬሚካል ርጭት በማስቀረትና አካባቢውን በመጠበቅ በኩል ትልቅ ሚና ተጫውቷል ይላሉ።
አዲስ ዘመን ህዳር 24/2012
አጎናፍርገዛኸኝ