አዳማ፡- ዘንድሮ ለ14ኛ ጊዜ በኦሮሚያ ክልል አዘጋጅነት በፊንፊኔ የሚከበረው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ቀን የህዝቦችን የአብሮነት እሴት አጉልቶ ማሳያ መድረክ እንደሚሆን የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሎሚ በዶ ተናገሩ። ለበዓሉ በስኬት መጠናቀቅ ህዝቡም የሰላም ባለቤትነቱን በተግባር የሚያሳይበት ሊሆን እንደሚገባም ገልጸዋል።
አፈ ጉባኤዋ ወይዘሮ ሎሚ በዓሉን አስመልክተው ትናንት በገልማ አባገዳ እንደገለጹት፤ በዓሉ ብሔር ብሔረሰቦች ለዘመናት ተጭኗቸው የቆየውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ የጭቆና ቀንበር ያስወገዱበትና የነጻነታቸው ሰነድ የሆነው ሕገ መንግስት የጸደቀበትን ቀን ምክንያት በማድረግ ይከበራል። ዘንድሮ የሚከበረው በዓልም በህዝቦች መካከል ያለውን የአብሮነትና የመቻቻል ታሪክ አጉልቶ ማሳያ በሚሆን መልኩ ሲሆን፤ ለበዓሉ በሰላም መጠናቀቅም የጸጥታ መዋቅሩ በቅንጅት እየሰራ ይገኛል።
እንደ ወይዘሮ ሎሚ ገለጻ፤ ላለፉት 29 ዓመታት የህዝቦችን ጥያቄ ከመመለስ፣ አብሮነታቸውን ከማጠናከርና ሌሎችም በርካታ ውጤቶች የተመዘገቡበት ቢሆንም፤ የራሱ የሆኑ ክፍተቶችም ነበሩበት።
ከእነዚህ መካከል በልዩነት ላይ የተሰራውን ያክል በአንድነት ላይ ያለመሰራቱ እንዱ ነው፤ ብሔር ብሔሰረቦች በሕገ መንግስቱ የተቀመጠላቸውን ያህል መብቶቻቸውን በአግባቡ መጠቀም አለመቻላቸው የሚገለጽበት የፌዴራል የስራ ቋንቋ አንድ ብቻ መሆኑም ሌላው መገለጫው ነው። በመሆኑም በዓሉ ሲከበር የሕገ መንግስቱ አንቀጾች በምን ደረጃ እየተተገበሩ ነው የሚለው የሚታይበት፤ በህዝቦች መካከል ልዩነት የተሰበከበት አካሄድም በህዝቦች መካከል ያለው የአንድነትና የመቻቻል ታሪክ ጎልቶ እንዲወጣ የሚደረገበት ይሆናል። የፓናል ውይይቶችም ይደረጋሉ።
በዓሉ በህዝቦች መካከል አብሮነትን የሚያጎለብቱ ተግባራት የሚከናወኑበት መሆኑን የጠቆሙት ወይዘሮ ሎሚ፤ የህዝቦች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ትስስሮችን ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት መደረጉንም አስታውቀዋል። በተለይ ክልሉ ካለው አጠቃላይ የኢኮኖሚና የቱሪዝም ሀብት ብሎም በአቃፊነትና በገዳ ባህል ዙሪያ የማስተዋወቅ ሰፊ ስራ የሚከናወንበት እንደሆነም አብራርተዋል።
በዓሉ ‹‹ሕገ መንግስታችን ለዘላቂ ሰላም›› በሚል መሪ ሀሳብ የሚከበር ይሆናል፤ በአሉ ሕገ መንግስታዊ መብቶች መተግበርን፤ እዚህም እዚያም የሚታዩ አለመረጋጋቶች በውይይት መፍታትን፤ ያልተገቡ አካሄዶች በሕግ የበላይነት ፈር እንዲይዙ የማድረግ አሰራር ማስፈንን እንዲያመለክት ተደርጎ የተቀረፀ ስለመሆኑ ተጠቁሟል። በበዓሉም ከ30 እስከ 35 ሺህ ሰው እንደሚሳተፍም ታውቋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 23/2012
ወንድወሰን ሽመልስ