አዲስ አበባ፡- በመደመር ንድፈ ሐሳብ እና በብልፅግና ፓርቲ ላይ የሚመለከታቸው አካላትም ሆኑ ህብረተሰቡ ግንዛቤ ሊያዝባቸው እንደሚገባ ተገለፀ።
በሚኒስትር ማዕረግ የፌዴራል ፍትህና ህግ ምርምር ማሰልጠኛ ተቋም ኃላፊ አምባሳደር ደግፌ ቡላ፣ የትዴት ፓርቲ ሊቀመንበር ዶክተር አረጋዊ በርሄ እና የኢዜማ የሙያ ማህበራት ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ አባል አቶ ወንድወሰን ተሾመ በተለይ ለአዲስ ዘመን በየበኩላቸው እንደገለፁት፤ በመደመር እሳቤ እና በብልፅግና ፓርቲ ላይ የሚመለከታቸው አካላትም ሆኑ ህብረተሰቡ መረዳቱ ሊኖራቸው ይገባል።
አምባሳደር ደግፌ በሁለቱም ላይ በተለያየ ደረጃ መድረክ ተዘጋጅቶ ግንዛቤ መፈጠር እንዳለበት ጠቅሰው፣መጀመሪያ የድርጅቱ አባላት በደንብ ግንዛቤ እንዲጨብጡ ማድረግ ላይ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። በመቀጠልም የመደመር መጽሃፍና የውህዱ ፓርቲ ሰነድ ለፓርቲም ለመንግስትም እንደሚጠቅም ተናግረው፣ አስፈፃሚው አካል ሊረዳው እንደሚገባም አመልክተዋል። ስለዚህ እያንዳንዱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ለራሱ የሚያስፈልገውን ወስዶ የእቅዱ አካል ማድረግ አለበት ያሉት አምባሳደር ደግፌ ፤ ይህ ካልሆነ ግን ያው በነበረው አካሄድ ብቻ እቅዱን እንደሚያወጣ ጠቁመዋል።
አምባሳደሩ፣ ‹‹ዋናው ነገር እንቀበላለን አንቀበልም ፤ ወይም ደግሞ ተደምረናል ወይስ አልተደመርንም አይደለም። ይዘቱ ምን እንደሆነ ከተረዳን በኋላ ለመቀበልም ለመተቸትም እንችላለን። በአሁኑ ወቅት በመገናኛ ብዙኃን የተወሰኑ ሰዎች ብቻ ቁንፅል ሐሳብ ይዘው ይናገራሉ እንጂ ሙሉውን ስዕል የሚሰጥ አይደለም። ስለዚህ መረዳቱ ሳይኖር አስተያየት በመስጠት መጠመዱ እንዲቀር ግንዛቤው ሊፈጠር ያስፈልጋል›› ብለዋል።
ዶክተር አረጋዊ በበኩላቸው፤ የመደመር አስተሳሰብና የውህድ ፓርቲ መፈጠሩን እንደሚደግፉት ጠቅሰው፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉት ፍልስፍናዎች በአንድ ጊዜ የተፈጠሩ ሳይሆን እየተደመሩ የመጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩም ያደረጉት ገንቢና መልካም አስተሳሰብ መሆኑን አመልክተው፣ አስተሳሰቡ ግን ወደ ህዝብ መውረድ እንዳለበት አስታውቀዋል። መፅሐፉ በጥቅሉ ይውረድ ሳይሆን መርሃግብር ተይዞለትም በየንዑስ ርዕሱ ግንዛቤ ሊያዝበት እንደሚገባ አስታውቀዋል።
እንደ ዶክተር አረጋዊ ገለፃ፤ ግንዛቤ በመፍጠሩ ረገድ የመገናኛ ብዙኃኑ ትልቅ ሚና አላቸው። በዚህም መሰረት ሐሳብ እንዲንሸራሸርና አስተያየት እንዲሰጥበት እንዲሁም የተደረሰበት ደረጃም እየታወቀ እንዲሄድ ማድረግ መልካም ነው።ምሁራን ትልቅ ድርሻ ያላቸው ሲሆን፣ የምጣኔ ሀብቱ ባለሙያ በኢኮኖሚው፣ የፖለቲካ ምሁሩ በፖለቲካ እና ሌሎችም በየንዑስ ርዕሱ ያለውን ጉዳይ በመያዝ የተደራጀ ውይይት እንዲያካሂዱ መድረኮችን መፍጠር ይገባል። ልዩነት መኖሩ እንደተጠበቀ ሆኖ የበሰለ ውይይት ማድረግ ከተቻለ መድረኩ የተራ ጯሂዎች ሆኖ እንዳይቀጥል ያደርጋል።
‹‹የመደመር እሳቤውም ሆነ የፓርቲው አካሄድ በግልፅ ወደሚመለከተው አካል ባለመድረሱ ሰው በድፍረት አስተያየት እየሰጠ ነው›› ያሉት አቶ ወንድወሰን ፤ በጉዳዩ ዙሪያ ውይይቶች መካሄድ እንዳለባቸው ተናግረዋል። ስለጉዳዩ በዩኒቨርሲቲ ደረጃም ውይይት ቢደረግበት መልካም ይሆናል ብለዋል።
በመጀመሪያ ደረጃ መደመር የሚለውን ንድፈ ሐሳብ በአፍሪካዊ መፃፉ በራሱ ሊደነቅ እንደሚገባ ተናግረዋል። ይህን ንድፈ ሐሳብ በአግባቡ ካለመረዳት የተነሳ እየተሰጠ ያለ አስተያየት እየበረታ መሆኑንም ጠቅሰው፣ ጉዳዩን ወደሚመለከተው የማድረሱ ስራ የፓርቲው ስራ ሊሆን እንደሚገባው አመልክተዋል።
እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ የውህዱን ፓርቲና የመደመር ደንብና መርሃግብር በአግባቡ መረዳት ያስፈልጋል። ግንዛቤ መፈጠሩ ካላስፈላጊ ትችትና ነቀፌታ ያድናል። ምክንያቱም ንድፈ ሐሳቡ መጠናት ያለበት ነው። መጽሀፉ ለስልሳ፣ ሰባ ብሎም ሰማንያ ዓመት ሊያገለግል የሚችል እሳቤ ነው። ስለዚህም ንድፈ ሐሳቡ በራሳቸው በፖለቲካ ተከታዮቹም ሆነ በምሁራን መታወቅ አለበት።
አዲስ ዘመን ህዳር 23/2012
አስቴር ኤልያስ