አዲስ አበባ፡- በስፔን በሚካሄደው 25ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ የኢትዮጵያን ጥቅም ሊያስጠብቁ በሚችሉ አጀንዳዎች ላይ ድርድር እንደሚደረግ የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን አስታወቀ።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፈቃዱ በየነ እና ሌሎች የስራ ሃላፊዎች ትናንት በጋራ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፤ እኤአ ከታህሳስ 2 ቀን 2019 አንስቶ በሚካሄደው 25ኛው የተመድ የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ የምትደራደርባቸውን አጀንዳዎች ይፋ አድርገዋል።
ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፈቃዱ እንደተናገሩት፤ የመንግስታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፋዊ ስምምነት ሴክሬተሪያት ለድርድር የሚቀርቡ አጀንዳዎችን ልኳል። እነዚህን አጀንዳዎች ከኢትዮጵያና ከሌሎች ታዳጊ ሀገራት ፖሊሲ አንጻር በመቃኘት የሀገሪቱን ጥቅም ሊያስጠብቁ የሚችሉ አጀንዳዎች ተለይተዋል።
ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ አጀንዳዎችን በመለየት ለድርድሩ ዝግጅት መደረጉን የተናገሩት ፕሮፌሰር ፈቃዱ፤ ‹‹በጉባኤው ያደጉት ሀገራት ከዚህ ቀደም የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የገቡትን ቃል ለመከለስ እንዲችሉ እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ ጫናዎችን መቋቋም የሚያስችሉ ስራዎች በትኩረት እንዲሰሩ ጫና ማሳደር ኢትዮጵያ ትኩረት ከምትሰጥባቸው ጉዳዮች አንዱ ይሆናል›› ብለዋል።
እንደ ፕሮፌሰር ፈቃዱ ማብራሪያ፤ በ24ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ ውሳኔ ያልተደረሰባቸው የፓሪስ ስምምነት መተግበሪያ መመሪያዎች በተለይም የካርቦን ንግድን የተመለከቱ መመሪያዎች በስፔን ከእልባት እንዲደርሱ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ፍላጎት ያላት በመሆኑ ወደ ፍጻሜ እንዲደርሱ የበኩሏን ታበረክታለች።
በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን መቋቋም እንዲችሉ ያደጉት ሀገራት የፋይናንስ፣ የቴክኖሎጂ፣ የአቅም ግንባታና የቴክኒክ ድጋፍ ማድረግ አለባቸው የሚል እምነት በኢትዮጵያ በኩል መኖሩን የተናገሩት ፕሮፌሰሩ፤ ‹‹እነዚህ ሀገራት ከዚህ ቀደም በማደግ ላይ ያሉትን ሀገራት ለመደገፍ የገቡትን ቃል እንዲፈጽሙ ትጠይቃለች›› ብለዋል።
እንደ ኮሚሽነሩ ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያ እያከናወነች ላለችው የአየር ንብረት ለውጥ የመከላከል ስራዎች ድጋፍ የማሰባሰብ ስራዎችም ይሰራሉ። ከጉባኤው ጎን ለጎን በሚካሄዱ ጉባኤዎች ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ጉልህ ሚና እየተጫወተች መሆኑን የማስረዳት ስራ በትኩረት ይሰራል፤ ይህም ከአጋር አካላት ጋር ቁርኝት ለመፍጠር ይረዳል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንበረት ለውጥ ማዕቀፋዊ ስምምነት ዋነኛው ዓላማ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የከባቢ የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ አባል ሀገራት የድርሻቸውን በሚችሉት ልክ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ የሚጠይቅ ስምምነት ነው።
አዲስ ዘመን ህዳር 23/2012
መላኩ ኤሮሴ