አዲስ አበባ፡- ፅንስ ማቋረጥ በሕግ ከተፈቀደ ወዲህ ንፅህናውን ባልጠበቀ የፅንስ ማቋረጥ ምክንያት የሚሞቱ እናቶች ቁጥር ከ20 በመቶ በላይ መቀነሱን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በጤና ሚኒስቴር የእናቶች፣ ሕፃናትና የሥርዓተ ምግብ ዳይሬክተር ዶክተር መሠረት ዘላለም በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፣ እናቶች ከሚሞቱባቸው ምክንያቶች ውስጥ ንፅህናውን ባልጠበቀ መንገድ በሚከናወን የፅንስ ማቋረጥ (ውርጃ) ተግባር የሚሞቱት እናቶች ቁጥር ከአጠቃላይ የእናቶች ሞት 32 በመቶ ድርሻ ነበረው::
ሕጋዊ ውርጃ የሚፈቅደው ሕግ እአአ በ2006 ከጸደቀና ሕጉን ተግባራዊ ለማድረግ በየጤና ተቋማቱ ንጽህናውን የጠበቀና ሕጋዊ የሆነ ፅንስ ማቋረጥ አገልግሎት መስጠት ከተጀመረ ወዲህ ከውርጃ ጋር ተያይዞ የሚሞቱት እናቶች ቁጥር ከ10 በመቶ በታች ወርዷል፡፡
በአሁኑ ጊዜ 50 በመቶ በሚሆኑት የጤና ተቋማት ንጽህናውን የጠበቀ የጽንስ ማቋረጥ አገልግሎትን እየተሰጠ እንደሚገኝ የገለፁት ዶክተር መሠረት እአአ በ2020 ሁሉም የጤና ተቋማት አገልግሎቱን እንዲሰጡ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
ጽንስ ማቋረጥ ሕጋዊነቱን ጠብቆ እስከተሰራ ድረስ የትኛውም የጤና ተቋም ላይ አገልግሎቱን የማግኘት የእናቶች መብት መሆኑን የገለጹት ዶክተር መሠረት የፌዴራል ጤና ሚኒስቴር የሕክምና ባለሙያዎቹን ክህሎት፣ እውቀት ለማሳደግ እንዲሁም አመለካከት ለመቀየር ሥልጠና እየሰጠና የሕክምና መሣሪያዎችን ተደራሽ ለማድረግ ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል፤ ይህን ተግባራዊ ለማድረግም የዘርፉ አመራሮች በየክልሎቹ በኃላፊነት መንፈስ እየሰሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡
ከ20 ዓመት በፊት 100ሺ እናቶች ቢወልዱ አንድ ሺህ የሚሆኑት ከወሊድ ጋር በተያያዘ ጤና እክል ይሞቱ ነበር የሚሉት የማህጸንና ጽንስ ሀኪምና የሕግ ባለሙያ የሆኑት ፕሮፌሰር ሰናይት ፍስሀ ተቋማትና ባለሙያዎች በየአካባቢው ተደራሽ በመሆናቸው ከወሊድ ጋር በተያያዘ ጤና እክል የሚሞቱት እናቶች ቁጥር ከአንድ ሺህ ወደ 300 ሊቀንስ ችሏል ብለዋል::
በአሜሪካ የሚገኘው የሚችጋን ዩኒቨርሲቲ የማህጸንና ጽንስ ህክምና ባለሙያዎችን በማሰልጠን ረገድ ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ፕሮፌሰሯ ገልጸዋል::
የመጀመሪያው ብሔራዊ የሥነ ተዋልዶ ጤና ሲምፖዚየም አዘጋጅ የቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ በተቋሙ የሥነ ተዋልዶ ጤና የልህቀት ማዕከል በማቋቋም እያከናወነ ያለውን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል፡፡ በኢትዮጵያ በሥነ-ተዋልዶ ጤና ላይ እየተሰሩ ባሉ ሥራዎችና የማህበረሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ በተከናወኑ ተግባራት ለውጦች እየተመዘገቡ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
በየጤና ተቋማቱ የሥነ-ተዋልዶ ጤናና ንጽህናውን የጠበቀ የጽንስ ማቋረጥ የህክምና አገልግሎት የሚሰጠው የእናቶችን፣ የወጣቶችን፣ የሕፃናትን ጤንነትና ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል መሆኑ ታውቋል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 22/2012
ጌትነት ምህረቴ