የሀያላን የእርስ በእርስ ፍጥጫ የጠነከረባት “እኔ ላንቺ የተሻልኩ ነኝ” በሚል መሸንገያ ቀርበው የሚቦጠቡጥዋት እድለ ቢስዋ ምድር አፍሪካ። እሺታዋ ዋጋ የሚያስከፍላት፤ እንቢታዋ የእጅ አዙር ቁንጥጫ የሚያስከትልባት ሆናለች። ለጥቅማቸው ብዙ ቀርበው ነገር ግን ብዙ ጥቅም የሚያሳጥዋት፤ በእርስዋ ለመገልገል እጅግ ተጠግተው ማንነትዋን እጅጉ የሚቀሟት በራስዋ መቆም ያቃታት ምድር። የይድረሱልኝ ጩኸት መለያዋ የሆነ የእርስ በርስ ፍጥጫና ፍትጊያ የበረከተው አህጉር አፍሪካ።
ስለ ራስዋ በራስ መቆም ተስኗት፤ ስለ ህዝብዋ በራስ መብቃት አቅም አጥታ ዘመናትን የተሻገረች እያላት ያጣች ምድር። አንደኛውን አለም እጅጉን ርቃ፤ ሁለተኛውን ዓለም ከላይ ተሸክማ በግድ በተጋተችው ሳታጣ በተነፈገቸው ለውጥ፤ እያላት ባጣችው እድገት ሶስተኛው አለም የሚል መለያ አጥልቃ ዛሬም በመዳህ ላይ የምትገኝ አህጉር።
እግርዋን ተጠቅማ እንዳትራመድ በብርቱ እጅዋ ሰርታ እንዳትለወጥ በምክንያት ተተብትባ፤ በሰበብ አስባቡ ታጥራ፤ ባበጁላት መንገድ የምትጓዝ ሄጂ ሲልዋት የምትራመድ ቁሚ ሲልዋት የማትቀመጥ የሀያላኑ ትዕዛዝ ተግባሪ፤ ያሻቸውን ተግባር ቀማሪ፤ በእጥፍ ልትመልስ ጥቂት ተበዳሪ የእነሱን ትዕዛዝ አክባሪ ሆና ዛሬ ላይ ደርሳለች አፍሪካ።
ተስፋን አንግባ ጭለማይቱ ምድር የተባለች፤ በውስጥዋ የታመቀ ተንቦግቧጊ ብርሀን መግለጥ ያቃተው አብሪ ትውልድ እንደ እድል እስካሁን ማፍራት ያልቻለች ለምለም ምድር። ያልተነካ ብቻ ሳይሆን ገና ያልተደረሰበት ውስጡ አረንጓዴ መሬት፤ የከበሩ ማዕድናት በማሕጸንዋ አርግዛ ዘመናትን የተሻገረች ተፈጥሮ ኳሽቶ የፈጠራት ልዩ አለም። ባለቤት የሆነው ህዝብዋ የእርስ በእርስ ግጭት መለያው፣ የፖለቲካ ትኩሳት መገኛ፣ ያለ መግባባት መንስዔ የሚፈልቅባት ምድሪቱን ያጨለመ ተስፋን የሚስቆርጥ መተላለቅ የበረከተባት አሳዛኝ ምድር አፍሪካ።
ሀያላኑ የያዘችው በረከት በጥልቀት ያቁታልና እስዋን ጠልቶ የራቀ፤ ይህችን አህጉር ትቶ የተቀመጠ ብረቱ አገር ከቶም የለም። አንድም በውስጥዋ ያለና ያልተነካው የተፈጥሮ ሀብትን ለመቀራመት በሌላ በኩል ደግሞ የበዛ የሰው ሀብትዋ ተጠቅሞ በገፍ የሚያመርተውን ምርት ማራገፊያነት ጥሬ እቃ ወስደው አምርተው መልሰው ለመሸጥ እጅጉን ይፈልጉዋታል።
እነዚህ ያደጉ አገራት አፍሪካ ላይ አይናቸው ማረፉ አፍሪካ ላይ ትኩረት ማድረጉ የፈለጉት በምክንያት ነው። ትንሽ እንቺ ብለው ብዙ ለመውሰድ፤ትንሽ አሳይቶ ብዙ ለመንሳት። አባብለው አልያም አስፈራርተው አንዴም “እኔ ያንቺ ጋሻ ነኝ አይዞኝ” በሌላ ጊዜ “ይህን አታድርጊና ወዬውልሽ” የሚለዋወጥ የለበጣና ማስፈራሪያ ቃላቸው ለሚፈልጉት ማሳኪያ ለሚሹት ማስተግበሪያ ነው።
ሀያላኑ አገራት በተለይ ቀዳሚዎቹ አሜሪካ፤ቻይናና ራሺያ በዚህች አህጉር የበላይነት ለመያዝ በአህጉሪቱ ውስጥ ያሉ መንግስታትን ወደራሳቸው ለመሳብ የማያደርጉት ፉክክር፤ የማያቀርቡት መደለያና ሰበብ ማግኘት ያስቸግራል። ለጥቅማቸው የሚቀርቧት ለማግኛቸው የሚያገብዋት መሻታቸው ሲሟላ የሚፈትዋት ባይተዋርዋ አህጉር አፍሪካ።
በአሁን ወቅት የአለም የበላይነት ለመቆጣጠር ባላቸው የእርስ በርስ ፉክክር አንዱ ይህ ገፅታቸው ነው። መሮጫ ሜዳቸው አፍሪካ የመፎካከሪያ ካርዳቸው የአፍሪካ እና የተቀረው ሶስተኛ አለም ህዝብ አድርገውታል። አንዱ ወደራሱ በአንድ መንገድ ሲያቀርብ ሌላኛው በተለየ ሁናቴ ወዳጅነቱን ማጠናከሪያ ሲያበጅ መጠቀሚያ ዘዴውን ሲቀምር ፉክክሩ ቀጥሏል።
የሀያላኑ አይኖች አፍሪካ ላይ ማተኮራቸው በምክንያት፤ እዚህች አህጉር ላይ መረባረባቸው በስሌት መሆኑ የአደባባይ ሀቅ ነው። እርግጥም በሚፈልጉት መልኩ ቀርበው ያሻቸውን በእጅ አዙር ይከውናሉ። ሀያላኑ ባላቸው የማይነጥፍ የጥቅም ፍላጎት ማሳኪያ ባሻቸው መልክ ይሰርዋታል፤ በተመቻቸው መልክ ያኖርዋታል። አህጉሪቱ እምቢኝ እንዳትል የማትችል አድረገው በብዙ ወጥመድ ሸክፈው ከዚያም ካፈነገጠች በእጅ አዙር ኮርኩመው ባሻቸው መንገድ እንዳሻቸው ያስጉዙዋታል።
በዚህ ዘመን ሁለንተናዊ ፉክክራቸው የጠነከረው የሀያላኑ አገራት አፍሪካን የግላቸው ለማድረግ የሚያደርጉት የእርስ በርስ ፉክክር ጠንክሯል። ቀርቦ ለመጠቀም የሚደርጉት ጥረት ቀጥሏል። የአፍሪካን መሪዎች አባብሎ የራሳቸው ጥቅም ለማስጠበቅና ቀድመው ወዳጅ ሆነው ቋሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያደርጉት የእርስ በእርስ ፉክክር በአሁኑ ወቅት በርክቷል። ውሎ አድሮ የድብቅ ፉክክሩ አደባባይ አውጥተውት ቃላት መወራወር ከጀመሩ ውለው አድረዋል።
የሀገራቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት አንደኛቸው ሌላኛቸውን ሲወርፉ በዚህች አህጉር ጉዳይ ከአንተ ይልቅ እኔ ያገባኛ ማለት አደባባይ ላይ ጀምረዋል። ከወራት በፊት ቢቢሲ በዘገባው እንዳተተው ከሀያላኑ ሀገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት መካከል ጠንከር ያለ ሀሳብ የሰጡት የአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት አማካሪ የነበሩት ጆን ቦልተን (አሁን ከስልጣናቸው ተነስተዋል) “ሁለቱ ሃገራት” አሉ ቻይናና ራሺያ ማለታቸው ነው “በአፍሪካ አህጉር ውስጥ ከአሜሪካ አንጻር በኢኮኖሚ ረገድ የበላይነትን ለመያዝ ሆን ብለው ሌት ተቀን ጥረት እያደረጉ ነው።” በማለት የሁለቱ ሀገራት የወቅቱን የአፍሪካ አገራት ላይ ትኩረት ማድረጋቸው ማመላከቻ ሀሳብና የአሜሪካ በጉዳዩ ላይ ያላት ቅራኔ አመላክተዋል።
ጆን ቦልተን “አሜሪካ ወደ ኋላ ቀረች ሌሎቹ የመቅደም ስራ እየሰሩ ነው።“ ባሉበት ንግግራቸው ውስጥ “የእኛ አፍሪካ መቅረብ ለአፍሪካ የሚበጅ፤ የሌሎች ግን ከዚህ የተለየ አላማ ያለው ነው።” በማለት የእራሳቸው አገር አሜሪካ ለአፍሪካ ያዘጋጀው አዲስ ዕቅድ በንግድና ሽብርተኝነትን በመዋጋት ላይ ትኩረትን የሚያደርግ እንደሆነ በማብራራት ሌሎቹን ተፎካካሪዎች ለመንቀፍና አፍሪካዊያን ደግሞ ለማባበል ሞክረዋል።
“እኛ” አሉ አማካሪው አሜሪካ ማለታቸው ነው “እያንዳንዱ ውሳኔዎች፣ የምንከተላቸው ሁሉም ፖሊሲዎች እና ለእርዳታ የምናወጣው ዶላር አሜሪካን በአህጉሪቱ ቅድሚያ የምትሰጣቸውን ጉዳዮች የሚያሳኩ ይሆናሉ” በማለት ሀገራቸው ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት በጎነት አጉልተው ነበር። በአንፃሩ ደግሞ አሉ ቻይናን “ጉቦ በመስጠት፣ ግልጽነት በሌላቸው ስምምነቶችና ብድሮች ሀገራቱን ለፍላጎትዋና ለጥያቄዎቿ ተገዢ እንዲሆኑ ማስገደጃ አድርጋለች” በማለት የቻይናን ተግባር ኮንነዋል። እኛ ለአፍሪካ ብቸኛ ጠቃሚና ተቆርቋሪ ነን ባዩ ጆን ቦልተን ቻይናን ብቻ ሳይሆን ሩሲያን ከአፍሪካ ጋር ያላትን ቁርኝት ለማጣጣል ሞክረዋል።
ሩሲያ አሉ ቦልተን ለህግ፣ ለተጠያቂነትና ለግልጽ አስተዳደር ትኩረት በማይሰጥ ሁኔታ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶችን ከአፍሪካ አገራት ጋር በመፍጠር የተፅዕኖ አቅሟን ከፍ ለማድረግ እየጣረች ትገኛለች። አክለውም ሩሲያ በተባበሩት መንግሥታት ውስጥ ለምታገኘው የድምጽ ድጋፍ ስትል የጦር መሳሪያ መሸጥንና የኃይል አቅርቦትን ማቅረብዋና ከአፍሪካ የተፈጥሮ ሃብትን እራሷን በሚጠቅም ሁኔታ እየወሰደች መሆኑ ለማስረዳት ሞክረዋል።
በሌላ በኩል አፍሪካን ጠቅሞ ለመጠቀም እንጂ የምቀርበው እንደ አሜሪካ ማኖ አስነክቶ የራሴን ጎል ለማግባት አይደለም የምትለዋ ቻይና “አፍሪካዊያን ሆይ ቻይና ለአፍሪካ የቅርብ ወዳጅና ታማኝ ጓደኛ ነች”በማለት የተለሳለሰ የአፍሪካ መሪዎችን ቀልብን የሳበ ንግግር የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ዢንፒንግ አንድ ወቅት የአፍሪካ ቻይና የጋራ ጉባኤ መክፈቻ ላይ ተናግረውት የነበረው አይዘነጋም።
ፕሬዚዳንቱ “አፍሪካን እንወዳለን፤ እንደግፋለንም” በማለት ለመሪዎቹ ምቾት የሚሰጡ ቃላትን ለባላንጣና ተፎካካሪያቸው ደግሞ እኛ ከእናንተ ለእርነሱ የተሻልን ነን የሚል ትርጓሜ ያለው ንግግራቸውን አስተጋብተዋል።በእርግጥም የቻይና ሰጥቶ መቀበል መርህ ከሌሎቹ የተሻለ ስለመሆኑን የፖለቲካ ተንታኞችም ሲናገሩ ይሰማል።
የሀያላኑ ሀገራት በአንድም በሌላ መልክ አፍሪካን ትኩረት አድርገው የራስ ለማድረግ መፎካከሩ ተጠናክሮ ቀጥሏል። አፍሪካም ሊጠቅማት ይሁን ሊጎዳት የቀረበ የእውነት ወዳጅ ወይም ሸንጋይዋ ሳትለይ የመጡትን አቤት የሚሄዱትን ሰላም ግቡ ማለትዋን ቀጥላለች። መነጣጠቂያ ሜዳ የሆነችው ይህቺ አህጉር መፃኢ እድልዋ እንዴት ይሆን በጊዜ የሚፈታ መልስ ነው። አበቃሁ ቸር ይግጠመን።
አዲስ ዘመን ኅዳር 19/2012
ተገኝ ብሩ