በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ግብርና የማይተካ ሚናውን እየተጫወተ ይገኛል። በዘንድሮው የምርት ዘመንም እንደ አገር 406 ሚሊዮን ኩንታል ምርት የማግኘት እቅድ ተቀምጦ እየተሰራ ይገኛል። ለአገራዊ እቅድ መሳካት የአንበሳውን ድርሻ ከሚወጡ አካባቢዎች መካከል ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ቀዳሚው ሲሆን፤ ክልሉ 169 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት እቅድ አስቀምጧል። ለመሆኑ ይሄን ግብ ከማሳካት አኳያ ምን ተከናውኗል፤ ያሉ ስጋቶችና የተወሰዱ እርምጃዎችስ ምን ይመስላሉ፤ እቅዱን ከማሳካት አኳያስ በቀጣይ ምን መሰራት ይኖርበታል፤ በሚሉትና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የክልሉ የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳባ ደበሌን አነጋግረን የሰጡንን ምላሽ በሚከተለው መልኩ አቅርበነዋል።
ዝግጅት፣ ሂደትና ግምት
በክልሉ የዘንድሮ ምርት ዘመን ሰብል ልማት ሥራ ስድስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት አርሶ በዘር ለመሸፈን ታቅዶ የተሰራ ሲሆን፤ ከቅድመ ዘር እስከ ድህረ ዘር በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል። በዚህም መሠረት አምስት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ሄክታር መሬት ማረስና በዘር መሸፈን ተችሏል። ከአረም፣ ከበሽታ፣ ተባይና መሰል ምርታማነትን ከሚቀንሱ ነገሮች ሰብሎችን ነፃ ከማድረግ አኳያም በሰውም ሆነ በቴክኖሎጂ በመታገዝ ሥራዎች ተከናውነዋል። ክልሉ ደጋ፣ ወይና ደጋና ቆላማ አካባቢዎች ያሉት እንደመሆኑ ይሄንኑ መሠረት ያደረጉ ሥራዎችም ተሰርተዋል። የአርሶአደሩ ትጋትና ቁርጠኝነትም ምርታማነትን ከማሳደግ አኳያ የጎላ ድርሻ እንዳለው ታምኖበት ሰፊ አቅሙን የመገንባት ሰፊ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
አሁን ባለው ሁኔታም የሰብሎች ይዞታ ጥሩ እንደመሆኑ የታቀደውን 169 ሚሊዮን ኩንታል ምርት በሙሉ ይሳካል የሚል እምነት ያለ ቢሆንም፤ የቅድመ ምርት ትንበያ ጥናት እየተከናወነ ይገኛል። እቅዱን ማሳካት ይቻላል መባሉም ከድቅመ ዝግጅት ሥራው ጀምሮ ያሉ ተግባራትን ታሳቢ ያደረገ ሲሆን፤ ምርታማነትን ከማሳደግ አኳያም ከግብዓትና ምርጥ ዘር አቅርቦት ጭምር እድገት የታየበት ዘመን ነው።
ለምሳሌ፣ በዘንድሮው የምርት ዘመን የምርጥ ዘር አቅርቦት በ28 በመቶ፤ እንዲሁም የማዳበሪያ አቅርቦት በ25 በመቶ አድጓል። በተጓዳኝ ለዚህ ሥራ አቅም የሚሆኑ ባለሙያዎችን የማሰልጠንና የማዘጋጀት፤ አርሶአደሩም ግንዛቤ ይዞ በተሻለ መነሳሳት ወደሥራ እንዲገባ ተደርጓል። በተመሳሳይ በሁሉም ቦታዎች ጥሩ የአየር ሁኔታ መኖሩ ለተሰሩ የምርት ማሳደግ ሥራዎች ተደማሪ አቅም ይሆናል። ከዚህ አኳያ ሲታይ በምርት ዘመኑ ከእቅድ በላይ ትርፍ ምርት ይመረታል የሚል እምነት ተይዟል።
ስጋቶችና ርምጃዎች
በዚህ መልኩ በመሰራቱ የሰብል ልማት ሥራው ጥሩ በሚባል ደረጃ ላይ ይገኛል። ሆኖም ምርታማነቱን ሊቀንሱ የሚችሉ ነገሮች መታየታቸው አልቀረም። ለምሳሌ፣ የበረሃ አምበጣ በክልሉ በሁለት ዞኖች (ምሥራቅና ምዕራብ ሐረርጌ) በ12 ወረዳዎች ላይ የታየ ሲሆን፤ ይሄንን ለመከላከል የክልሉ የግብርና ቢሮ እስከታች ያሉ ባለሙያዎችን ይዞ ከግብርና ሚኒስቴር ባለሙያዎች ጋር በመተባበር ለሥራው የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በጋራ በማቀናጀት ተሰርቷል። በዚህም 12ቱም ወረዳዎች ላይ የበረሃ አምበጣን ማስወገድ ተችሏል። አሁንም አልፎ አልፎ የተቀሩ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ካልሆነ በስተቀር በዘመናዊ መንገድ የተለያዩ መድኃኒት የሚረጩ አውሮፕላኖችን በመጠቀም እና በባህላዊ መከላከያ መንገድ (በሚረብሹ ድምጾችና ጭስ በመታገዝ) ኅብረተሰቡ ባደረገው ሰፊ ርብርብ ክልሉ ከበረሃ አምበጣ ነፃ እንዲሆን ተደርጓል።
ከዚህ አኳያ ሲታይ በአንበጣ መንጋው አልፎ አልፎ አንዳንድ (ወደ 1 ሺ700 ሄክታር የሚሆን) ማሳዎች ላይ የደረሰ መጠነኛ ጉዳት ከመኖሩ ባለፈ፤ ባለው ሁኔታ ከፍተኛ ጉዳት አላደረሰም። ምናልባት የሚመለስ ወይም ተንጠባጥቦ የቀረ ካለ የማጽዳት ሥራ እየተሰራ ነው።
የግሪሳ ወፍን በተመለከተም፤ በስምጥ ሸለቆ አካባቢ ስጋት የነበረ ቢሆንም፤ በዚህም ላይ አውሮ ፕላንን ጨምሮ የተለያዩ የመከላከያ ዘዴዎች ተግባራዊ በማድረግ ሰፊ ሥራ የተሰራ ሲሆን፤ በሰብል ምርታማነት ላይ ችግር እንዳይፈጥር ማስወገድ ተችሏል።
ከዋግና መሰል የሰብል በሽታዎች ጋር በተያያዘም ችግሩ ሊፈጠር እንደሚችል ታሳቢ በማድረግ ቅድመ ዝግጅት የተደረገ ሲሆን፤ የመድኃኒት ዝግጅትና አቅርቦትም ተከናውኗል። ተከስቶ ሲገኝም ለመከላከል ጥረት ተደርጓል። አሁን ላይ ችግሩ ሊከሰት የሚችለው ባሌ አካባቢ ሲሆን፤ ይሄን ታሳቢ በማድረግም አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል፤ መድኃኒት ተዘጋጅቶም በየቦታው ሰፊ ክትትል እየተደረገ ይገኛል።
ትኩረት የሚሹ ሥራዎች
አሁን ላይ በአንዳንድ ቦታዎች አልፎ አልፎ በተለይም በአርሲ ወይና ደጋ አካባቢዎች እንዲሁም በሸዋ ዞኖች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እየተከሰተባቸው መሆኑ ተስተውሏል። በመሆኑም የደረሰው ሰብል ሳይበላሽ ወቅቱን ጠብቆ መሰብሰብ ላይ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ሆኖም ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብና ከምርት አሰባሰብ ጋር በተያያዘ የሰብል መባከን እንዳይፈጠር ኅብረተሰቡ ጥንቃቄ መውሰድ አለበት።
በዚህም አንደኛ፣ በዝናብ እንዳይበላሽ በሚል የሚከናወነው የሰብል ስብሰባ ሂደት የምርቱን ለመሰብሰብ መድረሱን ከግምት ያስገባ መሆን ይኖርበታል። ሁለተኛም፣ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በተከሰተባቸው በአርሲም ሆነ በሸዋ አካባቢዎች እንደ ኮምባይነር ዓይነት ዘመናዊ የሰብል መሰብሰቢያ ቴክኖሎጂን መጠቀም የጀመሩ አካባቢዎች እንደመሆናቸው ይሄንኑ ተጠቅሞ ምርቱን ቶሎ መሰብሰብ ይገባል። ቴክኖሎጂ ያልደረሰባቸው አካባቢዎች ላይ ደግሞ በደቦ ማከናወን፤ ከቤተሰብ እስከ ተማሪዎች የሚሳተፉበት አሠራር ዘርግቶም በተደራጀ መንገድ ምርቱን መሰብሰብ አለባቸው።
መልዕክት
የተቀመጠው እቅድ የሚሳካው በማሳ ላይ ባለው የሰብል ይዞታ ብቻ ሳይሆን ውጤታማ የምርት ስብሰባ ሂደት ሲኖር ነው። በመሆኑም አመራሩ፣ ባለሙያዎች እንዲሁም መላው አርሶአደርና ሕዝብ ይሄን ተገንዝበው መስራት ይጠበቅባቸዋል። ከዚህ አኳያ ባለሙያዎችና አመራሩ በምርት አሰባሰብ ሂደት ላይ ሕዝቡን ማንቀሳቀስ፤ አርሶአደሮችም ቴክኖሎጂን ተጠቅመው በቅልጥፍና እንዲሰበስቡ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ሕዝቡ (ወጣቶች፣ አርሶ አደሮች፣ በቤተሰብ ደረጃ ጭምር) በተደራጀና በተቀናጀ መንገድ ወደ ምርት ስብሰባ ሂደት ገብተው የራሳቸውን ሚና መወጣት ይኖርባቸዋል።
አዲስ ዘመን ኅዳር 15/2012
ወንድወሰን ሽመልስ