ኢትዮጵያ በዘመናዊ የአሳሳል ስልት ሰዓሊ ጥበበ ተርፋ፣ ገብረክርስቶስ ደስታ፣ ታደሰ መስፍን፣ መዝገቡ ተሰማ፣ ጌታሁን አሰፋ፤ እሸቱ ጥሩነህን ጨምሮ ሌሎችም ታላላቅ ሰዎችን ለጥበብ አፍቃሪያን አስተዋውቃለች:: አሁንም ቢሆን በስነ ጥበብ ዳርቻ ከጥልቁ ባህር እየወጡ የመንፈስ ጥማትን የሚያረኩ ወጣትና ባለ ተሰጦ የስነጥበብ ባለሙያዎችን በየጊዜው ማየታችን አልቀረም::
ከሁለት ሳምንት በፊት በዚሁ የኪነ ጥበብ አምዳችን ላይ የአንጋፋውን ሰዓሊ ሉልሰገድ ረታ የስእል ስራዎች እና የፍልስፍና መንገድ በስፋት መዳሰሳችን ይታወሳል:: እኚህ አንጋፋ አርቲስት ሌኒንግራድ የሥነ ጥበብ ትምህርት አካዳሚ በማቅናት በ1986 ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ አገራቸው መመለሳቸውን፤ የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት፣በአገር ፍቅር ቲያትር ቤት እንዲሁም ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን በስቱዲዮ አርቲስትነት እየሰሩ መሆናቸውን አንስተን ነበር::
በወቅቱ በአዲስ ፋይን አርት ጋለሪ ተገኝተን ለእይታ የቀረቡትን ስራዎች ከመዳሰሳችን ባለፈ ሌሎች ጉዳዮችን ለመቃኘት ጥረት አድርገን ነበር:: በዚህም አንጋፋ ሰዓሊያን ለጥበብ ቤተሰቡ ከሚያቀርቡት አስደናቂ ስራዎቻቸው በተጨማሪ አዳዲስ ትውልድ ወደ ሰፊው የስነ ጥበብ ዓለም እንዲቀላቀሉ መነቃቃትን እየፈጠሩ መሆኑን ተረድተናል:: ተምሳሌታዊ ስራ እየሰሩ መሆኑን ተመልክተናል:: ይህን እንድንል ያስቻለን ደግሞ ወጣት ሰዓሊ ቴዎድሮስ አበባው ነበር:: ከዚሁ ወጣትና ተስፋ የተጣለበት ሰዓሊ እና የወደፊት ትልሞቹ ጋር ካደረግነው ጭውውት ላይ ቀንጨብ አድርገን ልናስዳስሳችሁ ወደድን::
ወጣት ቴዎድሮስ ከሁለት ዓመት በፊት በስነ ጥበብ በቀለም ቅብ በዲፕሎማ ተመርቋል:: ከትምህርቱ በኋላ በተለያዩ የቡድን አውደ ርዕዮች ላይ ስራዎቹን አቅርቧል:: በተለይ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ እውቅ አውደ ርዕዮች ውስጥ ቀዳሚውን ስፍራ በሚይዘውና አንጋፋ እና ወጣት ሰዓሊያን በሚሳተፉበት ‹‹አርት ኦፍ ኢትዮጵያ›› ላይ ለሁለት ጊዜያት ተወዳጅ ስራዎቹን አቅርቦ የጥበብ ደጃፍን በስኬት መርገጥ ችሏል:: በበርካታ ሰአሊያን እና የጥበብ አፍቃሪዎች ዘንድ ተስፋ የተሰነቀበት ወጣቱ የስነ ጥበብ ሰው ከአንድ ዓመት በፊት የውጭ ትምህርት እድል አግኝቶ ወደ ሩሲያ አቅንቷል:: አሁን ላይ በአንጋፋው የስቱዲዮ አርቲስት ባለሙያ ሰዓሊ ሉልሰገድ ረታ የቅርብ ክትትል እና የሙያ ምክር እየተደረገለት ይገኛል::
ሰዓሊ ሉልሰገድ ‹‹የቴዎድሮስን ስራዎች እና ጅምር ጥረቶች ከሚከታተሉና በቅርብ ሙያዊ ምክረ ሃሳብ ከሚሰጡት›› ውስጥ መሆናቸውን ይናገራሉ:: የአንድ ሰዓሊ ስራ የአገር መስታወት መሆኑን በመግለፅም ይህን አይነት ክህሎት ይዞ እንዲወጣ እርሳቸው ያሳለፉትን ሙያዊ የህይወት ውጣ ውረድ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ያጋሩታል:: እንደ አጋጣሚ ሆኖ እርሳቸው ከበርካታ ዓመታት በፊት በተማሩበት ተመሳሳይ የስነ ጥበብ ትምህርት ቤት እድል በማግኘቱ በዚያ የሚገጥሙትን ፈተናዎች ጨምሮ ሊቀስማቸው የሚገቡ የስነ ጥበብ ክህሎቶችን በፈርጅ በፈርጁ በማስቀመጥ ስኬት ጫፍ ላይ እንዲደርስ የሙያ አባት እየሆኑት ነው::
ወጣት ቴዎድሮስ ከስምንት ዓመት በፊት ወደ ስነ ጥበብ ዘርፍ ተቀላቅሏል:: በትምህርትም ክህሎቱን አዳብሯል:: ወደ ስነ ጥበቡ ዓለም የተቀላቀው በታዳጊነቱ የጓደኛውን ፈለግ በመከተል ነበር:: ይህ የአቻ ግፊት አንደርድሮ በጥልቁ የጥበብ ባህር ውስጥ እንዲሰጥም አድርጎታል:: እይታው የሰላ እምቅ እውቀቱ የጎመራ እንዲሆን ደግሞ በግል ጥረት የጥበብ አድባር ከበረከተባት አገር የትምህርት እድል አግኝቷል:: ዛሬ ከሙያ አባቶቹ እና ከታላላቅ የትምህትርት ተቋማት የሚያገኘው እውቀት የተዋጣለትና ‹‹አንቱ›› የተባለ የቀለም ቅብ ሰዓሊ እንደሚያደርገው ያምናል:: ነገን ተስፋ ያደርጋል::
ለዚህም ነው ቴዎድሮስን በቅርብ የታዘቡት አንጋፋው አርቲስት ሰዓሊ ሉልሰገድ እርሱ ‹‹በራሱ የቆመ፣ መልካም ስነ ምግባር የተላበሰና ጥረት የሚያደርግ›› በማለት ይጠሩታል:: የወደፊቷ ኢትዮጵያ የስነ ጥበብ ሙያን እንደሚወክልም በሙሉ ልባቸው ይናገራሉ:: እርሱን መሰል ሌሎች ስድስት ወጣት ሰዓሊያንን እንደሚያውቁ ገልፀው፤ በቻሉት ሁሉ ከጎኑ እንደሚቆሙ ይገልፃሉ::
ቴዎድሮስ በሩሲያ ለአንድ ዓመት ቆይታ አድርጓል:: እዛ ከመሄዱ በፊት በራሱ ጥረት ሌኒንግራድ የሥነ ጥበብ ትምህርት አካዳሚ በመፃፃፍ እና ስራዎቹን በማቅረብ እድሉን ሊያገኝ ቻለ:: ሰዓሊ ሉልሰገድም በትምህርት ቤቱ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸውን ተፅዕኖ ፈጣሪነት በመጠቀም የወደፊት ተስፋው የለመለመውን ወጣት በጥበብ ኮትኩተው እንዲያንፁት ድጋፋቸውን ሰጡት::
የትምህርት እድሉን ቢያገኝም ከተለያዩ 28 አገራት ከመጡ 280 የሚደርሱ ተማሪዎች ጋር የተግባር ፈተና መውሰድ እና በውድድር ማለፍ ነበረበት:: በፈተናው ማለፍ የሚችለው አራት ሰዎች ብቻ ነበሩ:: ይህን ጠንካራ ውድድር በሚገባ ተወጥቶ አፍሪካን ወክሎ ከአራቱ አንዱ መሆን ቻለ:: ከተግባር ፈተናው ውጪም በዚህ ትምህርት ቤት ከፍተኛ የትምህርት እድል ለማግኘት የአገሪቷን ቋንቋ እና የኑሮ ሁኔታ ያገናዘበ ፈተናንም ማለፍ ነበረበት::
‹‹የአንድ ዓመት ቆይታዬ የዝግጅት ጊዜ ነው›› የሚለው ቴዎድሮስ የትምህርት ሥርዓቱን እና ለቀጣይ ስድስት ዓመታት የሚኖረውን ቆይታ መሰረት የጣለበት እንደሆነ ይናገራል:: ከዚህ በኋላ በሚኖሩት ቀሪዎቹ ዓመታትም በመረጠው የቀለም ቅብ ሙያ በታላላቅ ዓለም አቀፍ ምሁራን ጥልቅ እውቀት እንደሚገበይ ይናገራል::
ሰዓሊ ሉልሰገድ ረታ ቴዎድሮስ በአጭር ጊዜ ውስጥ ስኬታማ ከሚሆኑ አርቲስቶች መካከል አንዱ እንደሚሆን በሙሉ ልብ ነው የሚናገሩት:: ይህን ሲሉ ግን በርካታ መሰናክሎችን ማለፍ እንዳለበት ሳይዘነጉ ነው:: ‹‹ቁጭት ከሌለህ ዋጋ የለህም›› ይሉታል:: በስነ ጥበብ ውስጥ ቁልፉ የስኬት መክፈቻ እርሱ መሆኑን እያሳሰቡት:: ‹‹ስነ ጥበብ ብዙ ሰው ጋር አይገኝም፤ ሰዓሊ የሚለውን ስም ይውሰዱ እንጂ ሰዓሊዎች ጋርም ላይኖር ይችላል›› የሚል ጠንካራ እይታቸውን ያጋሩታል:: እርሱን አሸናፊ ሆኖ እንዲወጣ በራሱ መሰናክሎችን አልፎ የልቡ ከፍታ ላይ መድረስ እንዳለበት ካሳለፉት የዘመን ውጣ ውረድ ልምዳቸው ቀንጭበው የጠራ አባታዊ ተግሳፅ ይለግሱታል:: ‹‹መጠበቅ ትልቁ ጠላታችን ነው፤ ይሄን ማድረግ እችላለሁ፤ እኔ ትልቅ አርቲስት እሆናለሁ›› ማለት እንዳለበት እየነገሩት እራሱን እንዲያሸንፍ የሞራል ስንቅ ይቋጥሩለታል:: ከስኬት በኋላ እናቱንና አገሩን መርሳት እንደሌለበት፤ የኢትዮጵያን ባህል ሃይማኖት ብሎም የአኗኗር ፍልስፍና የሚያንፀባርቅ ስራ እንዲሰራ አደራ ይሉታል:: ምክንያቱም ነገ ታላቅ እንደሚሆን ልቦናቸው ያውቀዋል::
ወጣቱ የስነ ጥበብ ባለሙያው ቴዎድሮስም እራሱን ከስድስት ዓመት በኋላ አሻግሮ ይመለከታል:: በሩሲያ ሌኒን ግራንድ የስነ ጥበብ ትምህርት ክፍል በርካታ እውቀቶችን እንደሚገበይ ልቦናው ይነግረዋል:: ‹‹ነገ የህይወት እይታዬና ፍልስፍናዬ ሊቀየር ይችላል:: ሰው ዛሬ አስቦና ነገ ደርሶ የሚሆነው የተለያየ ነው›› ይላል:: ሆኖም በእርግጠኝነት አገሩና ኢትዮጵያዊነቱ ከውስጡ እንደማይወጡ ያምናል:: ‹‹ታሪኬን ባህሌን በፍፁም አልረሳም›› እያለ በስራዎቹ ውስጥ ቀዳሚውን ስፍራ እንደሚይዙ በሙሉ ልብ ይገልፃል:: ኢትዮጵያ በእርሱ ተስላ ሌላው ዓለም ባላያት ጎን እንደሚያስተዋውቃት በሙሉ እምነት ይናገራል::
‹‹የምወደውን ሁሌም የሚሰማኝን ነገር መልቀቅ ወይም መጣል አልፈልግም›› ይላል:: ቴዎድሮስ በዚህ መስመር ከተጓዘ የፈለገበት የስኬት ጫፍ ላይ እንደሚደርስ እርግጠኛ መሆኑን እያመነ:: በዚህ መሰረት እርሱ አሸንፎ የደረሰበት ደረጃ ለመድረስ ሁሉም የራሱን እውነት ፈልጎ ያግኝ ይላል:: በቀጣዮቹ ስድስት ዓመታት ውስጥ እነዚህን ያቆጠቆጡ እውነቶቹን ዋርካ አድርጎ ለማሳደግ ከወዲሁ ለራሱ ቃል ገብቷል:: እንደሚያሳካውም እርግጠኛ ነው::
አዲስ ዘመን ኅዳር 14/2012
ዳግም ከበደ